የግብፅ ኦርቶዶክስ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን መነኮሳት በግድያ ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግብፅ ኦርቶዶክስ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ሁለት መነኮሳት በግድያ የተከሰሱት የቤተክርስትያኗ የበረሃ ገዳም ሃላፊ ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።
በምእራብ ግብፅ በርሃ የሚገኘው ማካሪየስ ገዳም ሃላፊ ጳጳስ ኢፒፋነስ ሰውነት በደም ተነክሮ የተገኘው እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
አሁን በግድያ የተጠረጠሩት ሁለቱ መነኮሳት ከጳጳሱ ጋር ቀድም ሲል የአቋም ልዩነት ነበራቸው በሚል መነሻ መጠርጠራቸውም ተገልጿል።
ሁኔታው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እጅግ አስደንግጧል።
የግብፅ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ እንዳስታወቀው ከተከሳሾቹ መነኮሳት አንዱ ዋለ አለ ሳድ ጳጳሱን 90 ሴ.ሜ ርዝበት ባለው የቧንቧ ብረት ጭንቅላታቸውን መትተዋቸዋል።
እኚህ መነኩሴ ግድያውን ተከትሎ ከገዳሙ ተባረው የነበረ ሲሆን ቀደም ሲልም ከሃላፊዎች ጋር በመጋጨትና የገዳሙን ህግ በመጣስ ጉዳያቸው ሲታይ መቆየቱ ተጠቁሟል።
መቼ እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም አሁን ሁለቱም መነኮሳት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ይህን ተከትሎ ቤተክርስትያኗ አዳዲስ ህገ ደንቦችን አውጥታለች። ከእነዚህም ለአንድ አመት ያህል አዲስ መነኩሴ አለመቀበል ፣ ቀሳውስት ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙና መነኮሳት ያለ ፍቃድ ከገዳም እንዳይወጡ የሚሉት ይገኙበታል።












