የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ባህርዳር ሊያቀኑ ነው ተባለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የአማራ ክልል ኮምንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስቡክ ገጻቸው እንደገለጹት፤ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ እንዲጓዝ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲያቀና ተስማምተዋል።

በአቶ ንጉሱ ጥላሁን የሚመራ የልዑካን ቡድን በአስመራ ይገኛል።

የልዑካን ቡድኑ በቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ የኤርትራውያንንና የኢትዮጵያውያንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረትም በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ የሚጓዝ ሲሆን፤ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ የልዑካን ቡድን ደግሞ ወደ አማራ ክልል እንዲያቀና መስማማታቸውን አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።

ኃላፊው የልዑካን ቡድኑ በኤርትራ ቆይታው፤ መቀመጫውን ኤርትራ ያደረገው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ ወደ አማራ ክልል ገብቶ በሰላማዊ ትግል የሚሳተፍበት ሁኔታ ላይ በመወያየት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።

ከአመራሮቹ ጋር በተደረገው ውይይት፤ የአማራ ህዝብን መብትና ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ ሁኔታ ለመታገል የሚያስችል ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታ መፈጠሩን በመገንዘብ፤ በሰላማዊ መድረክ ለመታገል ስምምነት ላይ መደረሱን ጨምረው ተናግረዋል።