የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ እና አካባቢው የመብት ጥሰት ተፈጽሟል አለ

የፎቶው ባለመብት, የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ)
ሰመጉ በወልዲያ እና አካባቢው የመብት ጥሰት ተፈጽሟል አለ። የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሃሙስ ነሐሴ 3 ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ እና አካባቢዋ የመብት ጥሰት መፈጸሙን ጥቁሟል።
ሪፖርቱ እንደሚለው ሕገ-መንግሥታዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ በአማራ ክልል፤ የሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ላይ ግድያ ተፈጽሟል።
የሟቾችን ስም እና ዕድሜ በመዘርዘር ከህዳር እስከ የካቲት 2010 ዓ.ም. ድረስ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች 17 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም የአካል ጉዳየት የደረሰባቸውን ዜጎች ዝርዝርም ይዞ ወጥቷል።
ሰመጉ እንደሚለው የዚህ መግለጫ አቢይ አላማ፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በበቂ ማስረጃ አስደግፎ በማቅረብ መፍትሄ እንዲሰጣቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ ለማሳሰብ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንዲሰጣቸውና ድርጊቱን የፈጸሙና ያስፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንዲሁም የአሰራር ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ለመጠየቅ ነው ብሏል።
በዚህ መግለጫ ውስጥ የተካተቱት የሞትና የአካል ጉዳት ማስረጃዎች በአብዛኛው የተገኙት ከሆስፒታሎችና ከጤና ጣቢያዎች ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ግን የሰመጉ መርማሪዎች የመብት ጥሰት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር ከሟች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች እንዲሁም ከአይን እማኞች ያገኛቸው እንደሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ሰመጉ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጉባኤው በውስን አቅሙ ለማጣራት የቻለው የመብት ጥሰት ብቻ በሪፖርት ውስጥ ማንጸባረቁን ገልጿል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔው እንደሚለው ከሆነ የደረሱትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት እና የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ መረጃዎች እንዲሰጡት ቢጠይቅም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ሰመጉ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ፤ መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በቂ ትኩረት በመስጠትና በማዳመጥ፣ ለግጭቶቹ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑትን ምንጮች በማጥናት እንዲሁም ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችን በመውሰድ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ እጃቸው ያለበት አካላትን ተጠያቂ በማድረግ፣ ዜጎችን በሀገራቸው በእኩልነትና በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲያመቻች በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።














