የደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፂ ቡድኑ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

ሪክ ማቻርና ሳልቫ ኪር የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የደቡብ ሱዳን መንግሥት በስልጣን ክፍፍል ላይ ከሀገሪቱ ዋነኛ አማፂ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ተገለፀ።

ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና የአማፂ ቡድኑ መሪ ስምምነቱን የፈረሙት በጎረቤት ሀገር ሱዳን ነው።

ስምምነቱ ማቻር ከአምስቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ ሆነው ወደስልጣን መመለስ የሚያስችላቸው ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውንና ለአምስት አመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆማል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል።

ከዚህ በፊት የተሞከሩ የሰላም ስምምነቶች በሙሉ ሳይሳኩ መቅረታቸው ይታወሳል።

" በመጀመሪያ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በመስማማት ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ለማድረግ ተፈራርመዋል" ሲሉ ስምምነቱ እንዲደረስ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል ዲርዲሪ ሞሐመድ ተናግረዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አርብ ዕለት ይህ ስምምነት እንደሚሰራ ያላቸውን ዕምነት ሲገልፁ እንደሌሎቹ ስምምነቶች "የተጫነብን" ስላልሆነ ይሰራል ነበር ያሉት።

"ይህ ስምምነት አይከሽፍም። የማይከሽፍበት ምክንያት ደግሞ የሱዳን ህዝቦች እራሳቸው በመካከላቸው ሰላም እንዲወርድ በመስማማታቸው ነው " ማለታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።

ደቡብ ሱዳን በ2011 ነፃነቷን ካወጀች በኋላ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች። ከዚያ በኋላም የብሔር ጥቃቶችና በርካታ ውድመቶችን እስከ 2013 ድረስ አስተናግዳለች።

ግጭቱ የተከሰተው በሳልቫኪር እና በማቻር መካከል በተፈጠረው ልዩነት ነበር።

ሳልቫኪር በወቅቱ ምክትላቸው የነበሩትን ማቻርን መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከስልጣን ካሰናበቷቸው በኋላ ሲሆን በወቅቱ ማቻር ውንጀላውን አጣጥለውታል።