ሰሜን ኮሪያ አዲስ ሚሳኤል እየገነባች ነው

የሰሜን ኮሪኣ ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, KCNA

ሰሜን ኮሪያ አዲስ ሚሳኤል በመንባት ላይ መሆኗን አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ለዋሽንግተን ፖስት አሳወቁ።

ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለስልጣን ሰሜን ኮሪያ አዲስ ሚሳኤል ግንባታ ላይ ስለመሆኗ በሳተላይት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ሮይተርስ እንደሚለው ግንባታው ምን ደረጀ ላይ እንደሚገኝ እስከአሁን ባይታወቅም ግንባታው እየተካሄደ ነው በተባለበት አካባቢ መኪና ሲዘዋወር ታይቷል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡንና የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ባደጉት ውይይት ሰሜን ኮሪያ ቀጠናዋን ከኒውክሌር ለማጽዳት መስማማቷ ይታወሳል።

ትራምፕም ውይይታቸውን ተከትለው "ሰሜን ኮሪያ ከእንግዲህ የኒውክሌር ስጋት አትሆንም" ቢሉም ስለእውነትነቱ ማገራገጫ ሳያገኙ ይህን ማለታቸው አስተችቷቸው ነበር።

ዋሽንግተን ፖስት እንዳስነበበው ሰሜን ኮሪያ በመዲናዋ ፒዮንግያንግ አቅራቢያ በሚገኘው ሳኑሙዶግ ሁለት በውሀ የሚዘወሩ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች (ኢንተርኮንቲነንታል ብላስቲክ ሚሳኤልስ) በመገንባት ላይ ትገኛለች።

ስለግንባታው የተናገሩት ኃላፊ አንዳሉት ከሆነ በውሀ የሚዘወር ሚሳኤልን ለመሙላት ጊዜ ስለሚወስድ የሚሳኤል ግንባታው ብዙም አያሰጋም።

ሰሜን ኮሪያ በአጠቃላይ ስድስት የኒውክሌር ሙከራ አድርጋለች። ያለፉት ሁለት ዓመታት በዘርፉ ልቀት ያሳየችበትም ነበር።

ሆኖም የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡንና የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሲንጋፖር በተወያዩበት ወቅት ሰሜን ኮሪያ ከኒውክሌር ነጻ እንደምትሆን ከስምምነት ደርሰው ነበር።

"ሙሉ በሙሉ ከኒውክሌር ነጻ" የሚለው ስምምነት ምን እንደሚያካትት በግልጽ የተባለ ነገር አልነበረም።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ ለምን ኑክሊዬርን መረጠች?