በሰሜን ወሎ መርሳ የሚገኙ ባለሃብቶች የምርት ቦታቸው እንደወደመባቸው ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Yasin Demeke
በፍራፍሬ ምርቷ በምትታወቀው የሰሜን ወሎዋ መርሳ ከሰሞኑ በግብርና ዘርፍ በተሰማሩ ባለሃብቶችና በአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ግጭቱን ተከትሎም የባለሃብቶቹ ይዞታ የሆኑ የደረሱ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም የከብት መኖ ወድሟል።
በመርሳ ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ የሆነው ወጣት ያሲን ደመቀ እንደተናገረው ጨቆርሳ ዳውጋ በሚባለው ቦታ ወጣቶች ተደራጅተው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የከብት መኖ ያመርታሉ።
የእርሱ ይዞታ ከዚህ አካባቢ አሻግሮ የሚገኝ ሲሆን መሬቱ ከቀድሞውም የግሉ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዳለው ይናገራል።
ይሁን እንጂ ለከብቶቻችን የግጦሽ መሬት አጣን በሚል በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ያሰሙ የነበሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለጥያቄያችን ምላሽ አላገኘንም በሚል በመጥረቢያ አትክልቶቹን በመቆራረጥ፣ ቤቶችን በማፍረስና የሳር ክምሮችን በማቃጠል ውድመት ማድረሳቸውን ተናግሯል።
"የደረሰ የማንጎ ዛፍ ከስሩ እየቆረጡና ፍሬውን እየለቀሙ በጆንያ እየከተቱ ወስደዋል። አፕል እንዲሁም በሰው ቁመት ልክ የሚሆን ኤለፋንት ግራስ የተባለ የከብት መኖ ሙሉ በሙሉ ወድሞብኛል" ይላል።
ያሲን በግምት ቁጥራቸው 50 የሚደርሱ አርሶ አደሮች ወደ ቦታው በማምራት አትክልቶቹን ማውደም ሲጀምሩ "ሌት ከቀን የቆፈርኩበት አፈር የበላውንና ደም የቋጠረውን እጄን እዩት። እባካችሁ!" ብሎ ቢለምናቸውም ከተግባራቸው እንዳልተቆጠቡ ይናገራል።
ሰሚ ሲያጣ ትቷቸው ወደ ቤቱ ከማምራት ውጪ አማራጭ አልነበረውም።
በጥቃቱ ወደ 200 የሚጠጋ የማንጎ ዛፍ ፣ በዓመት እስከ 200,000 ብር የሚገመት በ 2.5 ሄክታር መሬት ላይ የበቀለ የከብት መኖ ወድሞብኛል ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
ስለጉዳዩን ያነጋገርናቸው የሀብሩ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ስለሽ ማርዬ እንደሚሉት የወረዳው የአካባቢ ጥበቃ መሬቱ ነፃ መሆኑን አረጋግጦና የዞኑ ህግና ደንብ በሚያዘው መሰረት ጨረታ በማውጣት በግብርና ሙያ ላይ ላሉ ወጣቶች መሬቱን ሰጥቷል።
አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው ከይዞታቸው ታልፎ የግጦሽ መሬታቸው እንደታጠረባቸው ይናገራሉ።
ይህንንም ተከትሎ ሐምሌ 10፣ 2010 ዓ. ም. ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ከብቶቻቸውን ወረዳው አስተዳደር ድረስ ነድተው በመምጣት 'የምናበላቸው አጣን' ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተው እንደነበር አቶ ስለሽ ማርዬ ያስታውሳሉ።
በወቅቱም የወረዳው አስተዳዳሪ ሰብስቦ ያነጋገራቸው ሲሆን አለመግባባቱ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ከባለሃብቶቹ ጋር ያላቸውን አምባጓሮ እንዲያቆሙ ጠይቋቸዋል። ለጊዜው ባላሃብቶቹ እንዲታገዱ የወረዳው አስተዳደር ለቀበሌው የእግድ ደብዳቤ ፅፎ ነበር።
ነገር ግን ዞኑ ወረዳው ለባለሃብቶች በሚሰጥ ከ 10 ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ስልጣን የለውም በማለት እግዱን አንስቶታል ይላሉ።
በዚህ መሃል ውዝግቡ ያስቆጣቸው አርሶ አደሮችም ሃይል በመጠቀም ውድመት እንዳደረሱ አስረድተዋል።
ወረዳው አርሶ አደሮችንና ልማታችን ወደመብን ያሉ ባለሃብቶችን የማረጋጋት ስራ እየሰራ ሲሆን የሁለቱን ወገኖች አለመግባባት ለመፍታት እየሰራ እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።















