ትራምፕ መማገጣቸውን ለመደበቅ ከጠበቃቸው ጋር ሲመካከሩ የሚያሳይ መረጃ ይፋ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሲኤንኤን ይፋ ያደረገው የድምጽ ቅጂ ዶናልድ ትራምፕ ከጠበቃቸው ማይክል ኮህን ጋር በመሆን ኬረን መክዱጋል የተባለች ሞዴል ከትራምፕ ጋር ስለነበራት ግንኙነት እንዳትናገር በገንዘብ ለመደለል ሲመካከሩ ያስደምጣል።
ድምጹ የተቀዳው እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ማለትም የአሜሪካ ምርጫ ሁለት ወራት ሲቀሩት ነበር። ትራምፕ ከሞዴሏ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባለው ደግሞ በ2006 ነበር።
የቀድሞ የትራምፕ ጠበቃ ማይክል ኮሀን ግግራቸውን በድብቅ መቅረጸ ድምጽ ቀድተውት ነበር።
ፕሬዚዳንቱን በአሁን ወቅት እየተከራከሩላቸው ያሉ ጠበቃ ሩዲ ጊውሊያኒ በትዊተር ገጻቸው የቀድሞው የትራምፕ ጠበቃ በሚስጥር መያዝ ያለበትን ንግግር መቅዳታቸው ከጥብቅና ሙያዊ ስነ ምግባር ጋር ይጻረራል ሲሉ ተችተዋል።
ድምጹ ወንጀል ስለመሰራቱ ማስረጃ አይሆንም ብለውም መደለያ ገንዘብ አለመከፈሉንም አስረግጠዋል።
የጠበቃው ማይክል ኮሀን ጠበቃ ሌኒ ዴቪስ በምላሹ "ሪቻርድ ኒክሰን ትምህርት እንደወሰደው ሁሉ የድምጽ መረጃ ሀሰተኛ ሊሆን አይችልም" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው መሪማሪ ተቋም ኤፍቢአይ የማይክል ኮሀንን ቤት ሲበረብር ከተነኙ መረጃዎች አንዱ የድምጽ ቅጂው ነበር።
ሲኤንኤን ካሰራጨው ቅጂ በተጨማሪ ሌሎችም መረጃዎች ተገኝተዋል።
በድምጽ ቅጂው ምን ይደመጣል?
በድምጽ ቅጂው ሞዴሏ ኬረን መክዱጋል ናሽናል ኢንኳየር ለተባለ መጽሔት ታሪኳን ካካፈለች በኃላ ትራምፕ የታሪኳ ባለ መብት ለመሆን የሚያስችላቸው ገንዘብ ለመክፈል ከማይክል ኮሀን ጋር ሲመካከሩ ይደመጣል።
በድምጽ ቅጂው ማይክል ኮሀን "ለወዳጃችን ዴቪድ ገንዘብ የማስተላልፍበት ተቋም መክፈት አለብኝ" ሲሉ ይሰማል። ዴቪድ ናሽናል ኢንኳየር የተባለ መጽሔት ፕሬዘዳንት ናቸው።
ትራምፕ በምላሹ "ለዚህ መክፈል ያለብን ምን ያህል ነው? መቶ ሀምሳ ያህል?" ብለዋል። ከንግግራቸው በኃላ ለሞዴሏ ኬረን መክዱጋል 150,000 ዶላር ተከፍሏታል ተብሏል።
በድምጽ ቅጂው ጥሬ ገንዘብ ይከፈል ወይስ በቼክ በሚል ሲወያዩም መስማት ይቻላል።
ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮሀን መቼም እንደማይከዳቸው የሚጠቁም ትዊት ማስነበባቸው ይታወሳል።
ሆኖም ማይክል ኮሀን እጁ ላይ ያሉትን መረጃዎች ለመገናኛ ብዙሀን ማቀበሉን ተያይዘውታል። ከትራምፕ ጋር ለገቡበት ጦርነት መከታ ያደረጉት ደግሞ ጠበቃቸው ሌኒ ዴቪስን ነው።
የአሜሪካው ዲፓርትመንት ኦፍ ጀስቲስ እንደ ሞዴሏ ሁሉ መረጃ እንዳያወጡ በገንዘብ የተደለሉ ሴቶች ላይ ለመድረስ ምርመራ መጀመሩ ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, CBS
ኬረን መክዱጋል ማናት?
ሞዴሏ ኬረን መክዱጋል ከትራም ጋር የ10 ወር ግንኙነት ነበራት ተብሏል። በወቅቱ ከአሁኗ ባለቤታቸው ሜላንያ ትራምፕ ጋር ትዳር መስርተው ነበር።
ናሽናል ኮንከረር የተባለው መጽሔት 150,000 ዶላር ከፍሏት ታሪኳን ለማካፈል ተስማምታ ነበር። በስምምነቱ መሰረት ከትራም ጋር ስለነበራት ግንኙነት በአደባባይ ማውራት አትችልም።
ትራምፕ በበኩላቸው ከሞዷሏ ጋር ግንኙነት አልነበረኝም ብለዋል።

















