ሬሳ ማቀዝቀዣ ክፍል ውስጥ እየተነፈሰች የተገኘችው ሴት

ሬሳ ማቀዝቀዣ ክፍል ውስጥ እየተነፈሰች የተገኘችው ሴት

የፎቶው ባለመብት, SHUTTERSTOCK

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ሴት ሞታለች ተብላ ከተገነዘችበት የሬሳ ማቀዝቀዣ ክፍል በሕይወት ተገኝታለች። አሁን ላይ የህክምና እርዳታ እየተደረገላት እንደሆነም ታውቋል።

በደቡብ አፍሪቃዋ ጉዋቴንግ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ይህች ሴት በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሞታለች ተብሎ በባለሙያዎች ከታወጀ በኋላ ነው ወደ ሬሳ ማቀዝቀዣ ክፍል የተወሰደችው።

በአደጋው ወቅት እርዳታ ሲሰጥ የነበረ የአምቡላንስ ኩባንያ "እስትንፋሷ እንዳላለፈ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ምልክት አልነበራትም" ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

ነገር ግን የሬሳ ክፍል ሠራተኛ የሆነ ሰው ትንፋሽ ወደማይደመጥበት ክፍል ሲገባ ያጋጠመው ሌላ ነው፤ ተአምረኛዋ ሴት ትንፋሽ ዘርታ።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልተፈለገው ይህች ሴት አሁን ላይ ጆሃንስበርግ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላት እንደሆነ ታውቋል።

የግለሰቧ ቤተሰቦች ሁኔታው እንዲጣራላቸው በጠየቁት መሠረት ምርመራ እየተከናወነ እንደሆነ ቢቢሲ ተገንዝቧል።

"እኛ ስለዚህ ጉዳይ ከፖሊስ፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተⶉችና የሬሳ ክፍል ሠራተኞች እውቅና ውጭ የምንለው ነገር የለንም። ምላሽ ግን እንፈልጋለን" ሲሉ የቤተሰቡ ተወካይ የሆኑ ሰው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክስተቱ የቤተሰቡ 'ቆሌ እንደተገፈፈ' ግን ተወካዩ አልሸሸጉም።

የሕክምና ባለሙያዎቹ ግን ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልፈፀሙ ነው እየተናገሩ ያሉት።

ከሞት ክፍል በሕይወት የወጣችውን ግለሰብ ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በተጎዱበት የትራፊክ አደጋ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ወርሃ መስከረም ላይ አንድ ስፔናዊ ግለሰብ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ሞቱን እንዲያጣሩ የተመደቡ ባለሙያዎች በሕይወት እንዳገኙት የሚዘነጋ አይደለም።

በዚህች የጉድ ሃገር ደቡብ አፍሪቃ አንድ የ50 ዓመት ጎልማሳ ከሬሳ ማቀዝቀዣ ከፍል ውስጥ እየጮኸ መውጣቱም ይታወሳል።