ታዋቂነት እና የቆዳ ቀለም በጥቁሮች እይታ

ቢዮንሴ እና ሪሃና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሪሃና፤ ቢዮንሴ፤ ካርዲ ቢ፤ ሰቴፍሎን ዶን፤ ማያ ጃማ፤ ማቤል እና አዶኣ አቦአህ።

እነዚህ ሴቶች በ2018 በመዝናኛው ዘርፍ ዓለምን የተቆጣጠሩ አርቲስቶች ናቸው። ግን ስኬታቸው ምን ያህል ከቆዳ ቀለማቸው ጋር የተያያዘ ነው?

ጥቂቶች እንደሚሉት ግን ጠይም የቆዳ ቀለም ያላቸው ጥቁር ሴቶች ስኬታማነታቸው የጨመረ ነው። ፈረንጆቹ ''ከለሪዝም'' ይሉታል።

''ከለሪዝም'' ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች ላይ ያለ የተሳሳተ አመለካከት ወይንም ቀላ ቀለም ያላቸውን ሰዎች የተሻሉ አድርጎ ማሰብ ነው።

ታዋቂዋ አርቲስት ላዮነስ

የፎቶው ባለመብት, @sjp_p @kevstakespics

ላዮነስ የተባለችው ሙዚቀኛ ለሰባት አመታት ሙዚቃን አቋርጣ ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ በቆዳዋ ቀለም ምክንያት በደረሰባት ጫና እንደሆነ ትናገራለች።

''ኤ ኤንድ አር'' የተባሉት ታዳጊዎችን ለሙዚቃ የሚመለምሉ ሰዎች የቆዳ ቀለምሽ ትንሽ ፈገግ ያለ ቢሆን ኖሮ ተወዳጅ ልትሆኚ ትችዪ ነበር ብለውኛል ትላለች።

''ያን ጊዜ ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ በቆዳዬ ቀለም ጥቁረነት አፍር ነበር የምትለው ላዮነስ፤ እጅግ የምትወደውን ሙዚቃ እንድትተወው አንደሆነ ትናገራለች።

ጥቁሮችን የማግለሉ ነገር እንደገና ወደ ክርክር የተመለሰው እንግሊዛዊቷ የሬድዮ እና ቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢ ማያ ጃማ በ2012 ጥቁር ቀለም ያላቸው ሴቶችን የሚነካ ቀልድ በትዊተር ገጿ ላይ በመጻፏ ነው።

ብዙ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን የዚህች ዝግጅት አቅራቢ ስኬት የመጣው ባላት ጠይም የቆዳ ቀለም እንደሆነ ይናገራሉ።

የታዋቂዋ አቀንቃኝ ቢዮንሴ አባት ማቲው ኖውልስ እንደሚሉት ስኬታማ ከሆኑት ጥቁር ቀለም ካላቸው ሴቶች፤ አብዛኛዎቹ ቀላ ያሉ ናቸው።

ልጃቸው ቢዮንሴ ኖውልስ እጅግ ስኬታማ የሆነችው ቀላ ያለ የቆዳ ቀለም ስላላት እንደሆነና፤ ባለፉት አስር አመታት ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ስኬታማ የፖፕ ዘርፍ አቀንቃኝ እንዳላዩ ይናገራሉ።

ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2017 በእንግሊዝ ተወዳጅ ከነበሩት 40 ዘፈኖች መካከል አብዛኛዎቹ የጥቁር ዘር ያላቸውና ፈገግ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ነበሩ።

ቢዮንሴ፤ሲዛ፤ራይ፤ ካርዲ ቢ፤ ኤላ አይር፤ ኬሊ ሌዥ፤ስቴፍሎን ዶን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኬሊ ሌይ እንደምትለው እንግሊዝ ውስጥ ጥቁር ቀለም ላላቸው ሴቶች ወደ ሙዚቃው አለም መግባት ከባድ ነው። ማንም ሰው በቆዳ ቀለሙ ሳይሆን በማንነቱ ብቻ ነው መለካት ያለበት ትላለች።

በታዋቂው ፕራይድ ጋዜጣ አርታኢ የሆነችው ኒኮል ቫሴል በመዝናኛው ዘርፍ እውቅና እያገኙ ያሉ ሴቶች የቆዳ ቀለማቸው ቀላ ያለ የሆነበት ምክንያት አለው ትላለች።

የቢዮንሴና የሪሃና ስኬት ምንም እንኳን ከችሎታቸው ጋር ቢያያዝም፤ ፈገግ ያለው የቆዳ ቀለማቸው ግን ትንሽ የማይባል አስተዋጽኦ አለው ትላለች።

የቆዳ ቀለም ላይ መሰረት ያደረገ የሚባለው የሙዚቃው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የፊልሙ ዘርፍም ጭምር ነው።

በ2017 በእንግሊዝ ብዙ ተመልካች ከተመለከታቸው ፊልሞች መካከል ጥቂቶቹ ፈገግ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው እንደ ዞዊ ሳልዳና፤ ሄሊ ቤሪ እና ኤሊስ ኒል ያሉ እንስት ተዋናዮች ተሳትፈውባቸዋል።

ሉፒታ ንዮንግ እና ሌቲሺያ ራይት ብላክ ፓንተር ላይ ሲተውኑ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ኬንያዊቷ የስታር ዋርስ ተዋናኝ ሉፒታ ንዮንግ በጥቁር የቆዳዋ ቀለም ብዙ መገለልና የጥላቻ ስድብ እንዳስተናገደች ትናገራለች።

በየቀኑ ጠዋትም"ምናለ ጠይም እንኳን የቆዳ ቀለም ብትሰጠኝ ብዬ እጸልይ" ነበር ብላለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የመዝናኛው ዘርፍ ትንሽ በማይባል ደረጃ የቆዳ ቀለም ስብጥር እያሳየ እንደሆነ ይነገራል።

ዓለምን ያነጋገረውና ከሰው የተለየ ሃይል ባላቸው አፍሪካውያን ላይ ተመስርቶ በተሰራው ''ብላክ ፓንተር'' በተባለውም ፊልም ላይ የምትተውነው ሉፒታ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ተዋናዮችን ወክላለች ተብሏል።

የአንድ የፊልም አዘጋጅ ድርጅት ሃላፊ የሆነችው ጆርዳን ሚቸል እንደምትለው ከሆነ ግን አሁንም ቢሆን ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ።