ስፔን በሴት ሚኒስትሮች ቁጥር አዲስ ታሪክ አስመዘገበች

(ከግራ ወደ ቀኝ) የምጣኔ ሐብት ሚኒስትሯ ናዲያ ካልቪኖ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካርመን ካልቮ እና የገንዘብ ሚኒስትሯ ማሪያ ጄሱስ ሞንቴሮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, (ከግራ ወደ ቀኝ) የምጣኔ ሐብት ሚኒስትሯ ናዲያ ካልቪኖ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካርመን ካልቮ እና የገንዘብ ሚኒስትሯ ማሪያ ጄሱስ ሞንቴሮ

ሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት ማሳተፍ ባልተለመደበት ዓለም ስፔን አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች።

በስፔን ካቢኔ የሴት ሚኒስትሮች ቁጥር ከወንዶቹ መብለጡ መገናኛ ብዙኃንን አነጋግሯል። የሴት መብት ተቆርቋሪዎች ክስተቱን አወድሰውታል።

የስፔን ሶሻሊስት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንሼዝ ከ17 የሚኒስትር ወንበሮች ውስጥ አስራ አንዱን ለሴቶች ሰጥተዋል። ይህ ቁጥር ከየትኛውም የአውሮፓ አገር ካቢኔ የበለጠ ነው ተብሏል።

የሴቶች መብት ተቆርቋሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሳንሼዝ በተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመን ወንዶች ተቆጣጥረውት የነበረውን ካቢኔ ፐውዘውታል።

በአገሪቱ ሴት ሚኒስትሮች በቁጥር ከወንድ ሚኒስትሮች መብለጣቸው ብቻ ሳይሆን በካቢኔ ውስጥ እጅግ ቁልፍ የሚባሉትን እንደ መከላከያ፣ ምጣኔ ሐብት፣ ገንዘብና ፋይናንስ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትርነቱን ቦታ ሴቶች መያዛቸው በአገሪቱ አዲስ ዓይነት ተስፋን ጭሯል።

ከዚህም ባሻገር የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ሴት ናቸው።

አንዳንድ ሚዲያዎች ይህንን ካቢኔ "የሴቶች ካቢኔ" ሲሉ ጠርተውታል።

የሴቶች ጉዳይ እጅጉኑ ግድ የሚላቸው ተራማጁ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት በስፔን ማርች 8 የተደረገው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍና ያነሳቸውን ቁልፍ የእኩልነት ጥያቄዎቸ አዲሶቹ ሚኒስትሮች ያሳኩታል ብለው ያምናሉ።

የሴቶች ቀን በተከበረበት ማርች 8 በቁጥር ከ5 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ወደ አደባባይ በመውጣት የጾታ ጥቃትና ያልተመጣጠነ ክፍያን ተቃውመው ነበር።