ትራምፕ ሬክስ ቲለርሰንን ከስልጣን አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሬክስ ቲለርሰንን ከስልጣን አባረው በምትካቸው የሲአይኤ ሃላፊውን ማይክ ፖምፒዮን አምጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ነው ሹም ሽሩን ይፋ ያደረጉት። ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ቲለርሰንን ላበረከቱት ግልጋሎት አመስግነው፤ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ በተመደቡበት ሥራ "ድንቅ ነገር እንደሚያከናውኑ" ገልፀዋል።
የኤክሶንሞቢል ኩባንያ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ቲለርሰን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ የቆዩት ከአንድ ዓመት ብዙም ያለፈ አይደለም።
ትራምፕ በተጨማሪም ወደቲለርሰን ስልጣን የተዘዋወሩትን የማይክ ፖምፒዮን ቦታ የመጀመሪያዋ የስለላ ተቋሙ ሲአይኤ ሴት ሃላፊ እንዲሆኑ ጊና ሃስፔልን በእጩነት አቅርበዋል።
አንድ ከፍተኛ የዋይት ሃውስ ባለስልጣን ሹም ሽሩ የተካሄደበትን ወቅት በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በቀጣይ ከሰሜን ኮሪያ ጋርና ከተለያዩ ሀገራት ጋር ለሚደረጉ የተለያዩ የንግድ ድርድሮች አዲሶቹን ባለስልጣናት ቀድሞ ለማዘጋጀት የታሰበ እንደሆነ ተናግረዋል።"
ቲለርሰን የአሜሪካንን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት መንበርን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከአለቃቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር እንደማይስማሙ ይነገራል።
በተለይ ደግሞ የሰሜን ኮሪያን ጉዳይ በተመለከተ በዩናይትድ ስቴትስ በኩል ያለው አያያዝ ዋነኛው ያለመግባባቱ ምንጭ ነው ተብሏል።
የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዳለው ቲለርሰን ስለመሰናበታቸው ከፕሬዝዳንቱ ጋር አለመነጋገራቸውንና የመባረራቸው ምክንያት ምን እንደሆነ አያውቁም።
ምክትላቸው ስቲቭ ጎልድስታይን እንደተናገሩት "በሃገር ውስጥ ደህንነት ጉዳይ ላይ ወሳኝ እርምጃዎች እየታዩ በመሆናቸው ቲለርሰን በቦታቸው ላይ የመቆየት ፍላጎት ነበራቸው።"
ዛሬ ከዋይት ሃውስ ውጪ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት ከቲለርሰን ጋር ያሏቸው ልዩነቶች ወደ ግለሰባዊ ያለመጣጣም ደረጃ መድረሳቸውን ገልፀዋል።
በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያለመስማማት ቢኖሯቸውም በደንብ ተግባብተው ይሰሩ እንደነበር ትራምፕ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት አንደኛው ያለተግባቡበት ጉዳይ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት ነው።
"ስምምነቱ ለእኔ መጥፎ ነው። ስገምት ለቲለርሰን ግን ችግር የለውም። ስምምነቱን ውድቅ ማድረግ ወይም ሌላ ነገር ማድረግ እፈልግ ነበር። ነገር ግን የቲለርሰን አመለካከት የተለየ ነው። ይህም ተመሳሳይ አመለካከት እንደሌለን ያሳያል።"
ነገር ግን ቲለርሰን መልካም ሰው እንደሆኑና እንደሚወዷቸው ተናግረዋል።
አዲስ የሾሟቸውን ማይክ ፖምፒዮን በተመለከተም ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ፤ ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንዳላቸውና ተስማምተው መስራት እንደሚችሉ ገልፀዋል።












