ካለሁበት 19፡ እንጀራ ማግኘት የማይታሰብባት ከተማ - ሌጎስ

የፎቶው ባለመብት, Bethelehem Berihane
ቤቴልሔም ብርሃኔ እባላለሁ። ናይጄሪያ-ሌጎስ ነው የምኖረው። የምሰራበት መስሪያ ቤት ጄነራል ኤሌትሪክስ ይባላል። መስሪያ ቤቱ የሁለት ዓመት የድህረ ምረቃ ፕሮግራም አለው። በየስድስት ወሩ ከሃገር ሀገር እየተዘዋወርኩ ነው የምሰራው።
ይህ የናይጄሪያ ቆይታዬ አራተኛው ሀገር ነው። ባለፈው ነሐሴ ወር ስለሆነ ወደዚህ የመጣሁት በዚህ በጥር ወር መጨረሻ የስድስት ወር ቆይታዬ ይጠናቀቃል።
ወደ ሌጎስ ከመምጣቴ በፊት ለስድስት ወር እየቆየሁ የሰራሁባቸው ከተሞች በ2016 ናይሮቢ - ኬንያ፣ ከዚያ ጆሃንስበርግ - ደቡብ አፍሪካ፣ ቀጥሎ ደግሞ ቡዳፔስት - ሐንጋሪ ነበር። ከዚህ ቀጥሎ አዲስ አበባ የምመለስ ይመስለኛል።

የፎቶው ባለመብት, Bethlehem Berhane
ሌጎስ እና አዲስ አበባ
በሌጎስ ብዙ ነገሮችን በኢንተርኔት መገበያየት ይቻላል። ለሀገሩ አዲስ ለሰዉ እንግዳ በሆንኩባቸው ሀገራት ውስጥ ምግብ ለማዘዝ እና ሌሎች ነገሮች ለመግዛት የኢንተርኔት ግብይት መኖሩ ሕይወቴን ቅልጥፍ አድርጎልኛል።
በባንክ ካርዴ የምፈልገውን ማዘዝና መግዛት መቻሌ ሌጎስ ከአዲስ አበባ የተለየች እንደሆነች እንዲሰማኝ አድርጓል።
ከተማዋም ብትሆን የምዕራባውያን ስሜት ይታይባታል። ምናልባት በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ የራሳቸው ባህል የሚንፀባረቅበት ቦታም አለ ግን ምዕራባዊነት ግን ገኖ ይታያል።
ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነው የምለው እንጀራ ነው። ከሄድኩባቸው በርካታ ቦታዎች በተለየ እንጀራ ማግኘት የማይታሰብ የሆነባት ከተማ ሌጎስ ናት። እንጀራ ሳልበላ ለረጅም ጊዜ የቆየሁበት ሀገር ይህ ነው።
በዚህ የተነሳም የእነሱን ምግብ መልመድ ፈተና ሆኖብኝ ቆይቷል። በጣዕምም ሆነ በሽታው ከእኛ ፈፅሞ ይለያል።
በሌጎስ ቆይታዬ ፍላጎቴ ተከፍቶልኝ የምበላቸው የባህል ምግባቸው ከሩዝ የሚሰራውን ጆሎፍ፣ ከሙዝ ዝርያ የሚሰራውን ፕላንቴይን እና ደረቅ ያለ ጥብስ ሆኖ እነሱ ሱያ የሚሉትን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Bethlehem Birhane
ትዝ አለኝ ሀገሬ
ከኢትዮጵያ የሚናፍቀኝ ምግቡ ነው። እዚህ ባለሁበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያን ከሚያስታውሰኝ ነገራቸው መካከል የባህል ልብሳቸው ነው።
አርብ አርብ የባህል ልብስ ይለብሳሉ፤ በሠርግ ወቅትም እንዲሁ። ምንም እንኳ የባህል ልብሱ የኢትዮጵያውያን ጋር ባይመሳሰልም ሀገሬን ግን ያስታውሰኛል።
ከቤቴ መስኮት ወዲያ ማዶ አሻግሬ ስመለከት ደስ የሚለኝ በውቅያኖሱ ላይ የሚያልፈው በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ድልድይ ይታየኛል። ይህ ማራኪ እይታ መንፈሴን ያድሰዋል።
ወደ ሌጎስ ከተማ ከመምጣቴ በፊት ሰምቼ ጠንቃቃ እንድሆን ካደረጉኝ መረጃዎች መካከል በከተማዋ የዕገታ ወንጀል መኖሩን መስማቴ ነው።
ከመምጣቴ በፊት ይህንን መስማቴ እዚህ እንደደረሰኩ ወጥቼ ከተማዋን እንዳላያት አድርጎኝ ነበር። ቀስ በቀስ ግን እየለመድኩት ስመጣ እንደሚወራው እንዳልሆነ አየሁ። በእርግጥ በቴሌቪዥን ሰዎችን በእንዲህ አይነት ተግባር ማስደንገጥ (ፕራንክ) ያደርጋሉ።
ስለሌጎስ ሲወራ ወንጀል እና ዕገታ እንደሚበዛ ነው የሰማሁት። ነገር ግን ሁሉን ስለምደው የሚወራውን ያህል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። እኔም ላይ እስካሁን ምንም ነገር አልደረሰም።

የፎቶው ባለመብት, Bethlehem Birhane
ሌጎስን መቀየር ቢቻል
ከሌጎስ ጋር ሲነፃፀር አዲስ አበባ በጣም የተረጋጋች ከተማ ናት። ሌጎስ ግን ሁሉ ነገሯ ወከባ ነው። መኪና መንዳት ቀርቶ ጭራሽ ማሰቡ በጣም ይከብዳል። ብችል የኢትዮጵያዊያንን መረጋጋት ባጋባባቸው ደስ ይለኛል።
ሌላው እኔ በራሴ ተንቀሳቅሼ የምፈልገውን ገበይቼ ወደ ቤቴ መመለስ እፈልግ ነበር። ወጣ ብዬም በእግሬ መንሸራሸርና አየር መቀበል የስደስተኝ ነበር።
ነገር ግን የወንጀል ስጋቱ ከፍ ያለ በመሆኑ በመኪና የሚያደርሰኝን ሾፌር መጠበቅ የግድ ስለሆነ ይጨንቀኛል። አየሩም በጣም ስለሚሞቅ በእግሬ መንሸራሸር ባለመቻሌ ምቾት አይሰማኝም።
አሁን ቢሆንልኝ የምመኘው ነገር ቢኖር፤ ድንገት ተነስቼ ቤተሰቦቼ መካከል በመገኘት አብሬያቸው ማዕድ ብቋደስ እና በተለይ የገና በዓልን ከቤተሰቦቼ ጋር ባሳልፍ ደስ ይለኝ ነበር።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦













