528 እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ከሁለት ቀናት የተሃድሶ ስልጠና በኋላ ይፈታሉ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ

የፎቶው ባለመብት, የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ

የምስሉ መግለጫ, የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ 528 እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ይለቀቃሉ ብለዋል። ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ክሳቸው የሚቋረጠው እና ይቅርታ የሚደረግለቸው በጸረ-ሽብር ህጉ የተከሰሱትንም ይጨምራል ብለዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠው መመሪያ ለማስፍጸም ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ ይህ ግብረ ኃይል የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅዶችን አውጥቷል።

በዚህም መሰረት በአጭር ጊዜ እቅዱ የተፈረደባቸውን እስረኞችን በምህረት መልቀቅ እና ክስ የተመሰረተባቸውን ደግሞ ክሳቸውን ውድቅ ማስደረግ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን ተናግረው ከዚህ በተጨማሪ እሰረኞች/ተጠርጣሪዎች በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች የሚያዙበትን አያያዝ ማሻሻል ነው ብለዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህጉ የሚፈቱት እሰረኞች የሚከተሉትን መስፈርቶች ያሟሉ ናቸው ብለዋል።

  • ህገ-መንግሥቱን ወይም ህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን የመናድ እንቅስቃሴ ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ
  • በከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ
  • የሰው ህይወት ያላጠፉ ወይም በአካል ላይ ከባድ ጉዳት ያላደረሱ እንዲሁም
  • በስርዓቱ ተጠቃሚ ሆነው ሳለ በሌሎች ገፋፊነት ወደ ሁከት እና ብጥብጥ የገቡ

ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ያሟሉ እስረኞች ከሁለት ቀናት የተሃድሶ ስልጠና በኋላ ይፈታሉ ተብሏል።

ከሚፈቱት እስረኞች መካከል 115 በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሥር የሚገኙ ሲሆን በክልል ደረጃ የሚገኙትን ደግሞ ክልሉ በሚወስነው መሰረት ተግባራዊ ይሆናል። እሰካሁን ድረስም የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ክልል ብቻ 413 የሚሆኑ የእስረኞችን ስም ዝርዝር አቅርቦ ክሳቸውን ለማቋረጥ ወስኗል ብለዋል።

ክሳቸው ተቋርጦ ከሚፈቱ እሰረኞች መካከል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሚገኙበት አንደሆነ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፤ ''በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ስም ዝርዝራቸው ይፋ ሲደረግ የምንመለከተው ይሆናል'' ያሉ ሲሆን፤ አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የለም በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው በተለመዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራውን የምርመራ ማዕከል ዘግቶ ወደ ሙዝየምንት የመቀየሩን ሥራ የሚሰራው ሌላ ግብረ ኃይል ነው ብለዋል።