ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ቆሻሻ " ከሚለው አስተያየታቸው በኋላ ዘረኛ አይደለሁም ሲሉ አስተባበሉ

ትራምፕ ስለ ስደተኞች በተናገሩት ወቀሳ እየደረሰባቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አፍሪካውያንን፣ ሄይቲ እና ኤልሳልቫዶርን ለመግለፅ "ቆሻሻ" የሚለውን ቃል ከተጠቀሙና ከፍተኛ ተቃውሞ ከደረሰባቸው በኋላ ዘረኛ አይደለሁም ሲሉ አስተባበሉ።

"ዘረኛ አይደለሁም፤ ቃለመጠይቅ ከምታደርጉላቸው ሰዎች መካከል በጣም ዘረኛ ያልሆንኩት እኔ ነኝ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት "ለምንድነው ይህን ሁሉ ሕዝብ ከ'ቆሻሻ' ሃገራት ይዘን የተቀመጥነው?" ብለዋል ተብሎ መዘገቡ ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ ዘረኝነትን በሚመለከት ለሚቀርብባቸው ክስ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መልስ መስጠታቸው ነው።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከዴሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች የተውጣጡ ሕግ አውጪዎች ጋር ስደተኞችን በተመለከተ የጋራ መስማማት ላይ ለመድረስ በተደረገ ውይይት ላይ ነው ይህን ንግግር ያሰሙት።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ የሚኖሩ የበርካታ ሃገራት ዜጎችን በጊዜያዊነት የመኖር ምብታቸውን በማንሳት ላይ ይገኛል።

በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት ወይንም በወረርሽኝ ለተጎዱ ሃገራት ዜጎች ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ከመስጠት አሜሪካ ስደተኞችን ከኖርዌይ መቀበል እንደምትመርጥ ተናግረዋል ተብሎ ነበር።

ዘገባዎች እንደሚያስረዱት በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ከ ኤል ሳልቫዶር ሆንዱራስ እና ሄይቲ መሆናቸው ሲነገራቸው "ሄይታውያን?ተጨማሪ ሄይታውያን ያስፈልጉናል?"ሲሉ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አርብ እለት በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት የተጠቀሙት ቃል "ጠንካራ" ቢሆንም ነገር ግን ዘገባው ላይ የቀረበውን ቃል ግን አልተጠቀምኩም ብለው ነበር።

በተጨማሪም ሄይታውያንን መዝለፋቸውን ክደው ይህ የዲሞክራቶች ሴራ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንቱ ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠይቋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ቃለ አቀባይ የሆኑት ሩፐርት ኮልበቫይል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ደግሞ 'ትራምፕ የተናገሩት እውነት ከሆነ ንግግራቸው አጸያፊ ነው፤ አንድን ሃገር እና አህጉር በደምሳሳው ቆሻሻ ማለት ተገቢ አይደለም" ብለዋል።

በርካታ ዲሞክራቶችም ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወር ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን ላይ ተገኝተው የሚያደርጉት ንግግር ላይ በዚህ ዘረኛ አስተያየታቸው የተነሳ እንደማይገኙ ተናግረዋል።