አሜሪካ በኢራን ላይ የኒውክሌር መሣሪያ የምትጠቀም ከሆነ ቴህራን የአጸፋ ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ አንድ የፓርላማ አባል ተናገሩ
አሜሪካ በኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የምትጠቀም ከሆነ ቴህራን በዓይነት ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ የአገሪቱ የፓርላማ አባል ተናገሩ።
የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ኮሚሽን አባል የሆኑት ፋዳ ሆሴይን ማሌኪ ይህንን አስተያየት የሰጡት፥ ከኢራኑ የዜና አውታር 'ካባር ኦንላይን' ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ነው።
አሜሪካ በኢራን ላይ የኒውክሌር ጥቃት የመሰንዘሯ ዕድል ምን ያህል እንደሆነ የተጠየቁት ማሌኪ” ትራምፕ በቂ ጥንቃቄ ያልተደረገበት እርምጃ ሊወስዱ አይችሉም ብዬ በድፍረት አልናገርም። ነገር ግን እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ ይደፍራሉ ብዬም አላስብም፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት እርምጃ ዓለምን ወደ አደገኛ ጦርነት ሊከት ይችላል” ብለዋል።
“እንዲህ ዓይነት እርምጃ ከተወሰደ፣ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክም ምላሽ ይሰጣል፤ ምላሹም በኢራን ላይ ጥቅም ላይ ከዋለው የጦር መሣሪያ ዓይነት ጋር ተመጣጣኝ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ብትጠቀም ኢራንም የኒክሌር ጦር መሳሪያ ትጠቀማለች ማለት ስለመሆኑ የተጠየቁት ማሌኪ "አሜሪካ ማንኛውም ነገር ብትጠቀም፣ ኢራን ምላሽ ትሰጣለች” ብለዋል።
ማሌክ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪኣ አላት ብለው አልተናገሩም።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለ ንግግር አለመኖሩን እንዲሁም የተያዘ ቀጠሮም እንደሌለ ተናግረዋል።
አማቻቸው እና የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ኢራን ለአሜሪካ “ስሜት የሚሰጥ” መደረደሪያ ስላላቀረበች ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “ፍላጎት አላሳየችም” ብለዋል።
አሜሪካ እና ኢራን ስድስት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት ጦርነት ውስጥ ከስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉ ሲሆን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመቆጣጠር ረገድም እሰጥ አገባ ውስጥ ናቸው።
ማሌኪ አሜሪካ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ኢራን “በርካታ አማራጮች” እንዳሏት በመግለጽ “ተመጣጣኝ እና ከዚያም የከፋ ምላሽ” እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።
ማሌኪ እንደተናገሩ “የኢራን በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ አቅሞች እስካሁን ይፋ አልተደረጉም።”
እንዲሁም ኢራን ከነበረችበት የመከላከል አቋም ወደ “የማጥቃት አቅም” መሸጋገሯን ገልጸዋል።
ቴህራን እና ዋሺንግተን ከስምምነት ላይ ሊደርሱ አለመቻላቸውን በተመለከተም፥ ትራምፕ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የሰፈሩ ግዴታዎችን ባለማክበራቸው የተነሳ መሆኑን ማሌኪ ተናግረዋል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም የፈረመቻቸውን ግዴታዎች ሳታከብር ወደ ድርድር አንመለስም ያሉት ማሌኪ የሆርሙዝ ወሽመጥም ሳይከፈት ይቀራል ብለዋል።
አገራቸው ከኦማን ጋር የምታደርገው ንግግር የተናጠል መሆኑን እና የአሜሪካ ተሳትፎን እንደማትፈልግም ተናግረዋል።