ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኩዌት ሉዓላዊ ግዛት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እሁድ ዕለት ኢራን በኩዌት ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ከኩዌት ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ሳባህ ኻሊድ አል ሀማድ አል ሳባህ ጋር በስልክ መወያየታቸው ተገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኩዌቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ባደረጉት ውይይት በአገሪቱ ሉዓላዊ ግዛት እና የአየር ክልል ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በጽኑ ማውገዛቸውን የኩዌት የዜና ወኪል ዘግቧል።
ዐቢይ፤ ድርጊቱ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ጥሰት ነው ማለታቸውን ዘገባው ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከልዑል አልጋ ወራሹ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ወቅት የኩዌት ዜጎች እና ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማውገዛቸው ተገልጿል።
ዘገባው እንደሚያመለክተው ዐቢይ፤ በኩዌት የሲቪል ተቋማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።
ዐቢይ ኢትዮጵያ፣ የኩዌት መንግሥት እና አመራር የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ መረጋጋት እና ደኅንነት ለመጠበቅ በሚወስደው ማንኛውም እርምጃ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ኢራን በትናንትናው ዕለት በመካከለኛው ምሥራቅ በፈጸመችው ጥቃት በኩዌት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።
ኢራን በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ ዛሬም ጥቃት የፈጸመች ሲሆን በባህሬን፣ ዱባይ እንዲሁም በኩዌት የአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የኩዌት ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ሳባህ ኻሊድ አል ሀማድ አል ሳባህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ስላሳዩት ድጋፍ እንዳመሰገኑም የዜና ወኪሉ ዘግቧል። የዓለም መንግሥታት በኢራን ላይ ስለደረሰው ጥቃት ምን አሉ?