ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሆርሙዝን እንቅስቃሴ ያገዱት ኢራን እንድትስማማ ለማስገደድ መሆኑ ገለጹ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን የዘጉት ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እና ጦርነቱን ለመቋጨት የሚደረስ ስምምነትን እንድትቀበል ለማስገደድ መሆኑን ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሀውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ኢራን ክፉኛ ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት መንግሥታት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም አለ

    የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት፤ ማንም አገር ለዓለም አቀፍ ትራንዚት ጥቅም ላይ በሚውለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን የማገድ ሕጋዊ መብት እንደሌለው ገለጹ።

    የዓለም አቀፉ የባሕር ጉዞ ተቋም ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ ከቢቢሲ ራዲዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ ጉዞ መታገዱ አደገኛ ምሳሌን የሚያስቀምጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

    “ግጭት እየተካሄደ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለዓለም አቀፍ ጉዞ ጥቅም ላይ የሚውልን ማንኛውም ወሽመጥ ለማገድ የሚወሰድ እርምጃ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕጋዊ መሠረት የለውም” ብለዋል።

    ዋና ጸሐፊው ዶሚንጌዝ፤ “ተጨማሪ የአጸፋ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር፤ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ ያጡት 20 ሺህ ባሕርተኞች እና በዓለም ዙሪያ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የበረታባቸው ሰዎች ስጋት ይጨምራል” ሲሉም ተናግረዋል።

    “ለረጅም ጊዜ በቆየ ቁጥር ተጽዕኖው በሁላችንም ላይ ለተራዘመ ጊዜ ይቆያል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ 20 በመቶው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋት የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    ለእዚህ የኢራን እርምጃ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን ከትናንት ጀምሮ አግደዋል።

  2. ሆርሙዝ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተዘጋ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት የቻይና መርከብ ማለፉ ተዘገበ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን ካገደ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት አንድ የቻይና ነዳጅ ጫኝ መርከብ በወሽመጡ በኩል ማለፉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    መዳረሻው ቻይና የሆነው ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የበረው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ ላይ እንደነበረ ቢቢሲ የተመለከታቸው መረጃዎች አሳይተዋል።

    “ሪች ስቴሪ” የተሰኘው ይህ ነዳጅ ጫኝ የአሜሪካ እገዳ ትናንት 11 ሰዓት ላይ ከተጀመረ በኋላ በወሽመጡ በኩል በማለፍ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ቀዝፎ የሄደ መርከብ መሆኑን የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጾች አሳይተዋል ተብሏል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ የመርከቡ ባለቤት “ሻንዳይ ዡአንረን ሺፒንግ” የተባለ እና ከኢራን ጋር በሚፈጽመው ንግድ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ኩባንያ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት “ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት ወይም ከዚያ ለመውጣት የሚሞክር ማንኛውም እና ሁሉም መርከቦች” በአሜሪካ ባሕር ኃይል እንደሚታገዱ ገልጸው ነበር።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ እገዳው የሚተገበረው “ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ” መርከቦች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝም በተመሳሳይ “ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚደረጉ ሁሉም የባሕር ላይ ጉዞዎች” እንደሚታገዱ አስታውቋል።

    ይሁን እንጂ "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ብሏል።

    ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እገዳው ሰኞ 11 ሰዓት ላይ ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ አስቀድሞ ባሉት ሰዓታት አራት መርከቦች በወሽመጡ በኩል አልፈዋል።

    ‘ማሪን ትራፊክ’ የተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያሳየው አራቱም የጭነት መርከቦች ናቸው። ምናልባትም ነዳጅ፣ ጋዝ ወይም ኬሚካል ጭነው እንደሚሆን ተገምቷል።

    ማክሰኞ ዕለት ጉዞ ያደረገው ብቸኛ መርከብ ‘ሪች ስቴሪ’ ነው። ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የነበረው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ እንደሆነ እና መዳረሻውን ቻይና እንዳደረገ የ‘ማሪን ትራፊክ’ መረጃ ያሳያል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ በዚህ መርከብ ላይ ያሉት የቻይና የባሕር ሠራተኞች ናቸው።

    በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ሌላ መርከብም ወደ ወሽመጡ ማምራቱን የዜና ወኪሉ ‘ኤልኤስኢጂ’ ከተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መመልከቱን ጠቅሷል።

    ከዚህ ቀደም የሩሲያ እና የኢራን ነዳጅን በማጓጓዝ የሚታወቀው ይህ ሁለተኛ መርከብ፤ ሐሙስ ዕለት ኢራቅ ደርሶ ነዳጅ እንደሚጭን ይጠበቃል ተብሏል።

  3. የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷ "ከባድ" የሉዓዊነት “ጥሰት” ነው አሉ

    በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷን የቴህራን ሉዓላዊነት ላይ የተፈፀመ “ከባድ ጥሰት” ሲሉ አወገዙ።

    አምባሳደር አሚር ሳይድ ኦራቫኒ ለተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፃፉት ደብዳቤ “ሕገ ወጥ” የሆነው እግድ “የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረታዊ መርህዎች ላይ ከባድ ጥሰት የሚፈፅም” ነው ብለዋል።

    ጉቴሬዝ “ሁሉም ወገኖች” ለዓለም የነዳጅ ዝውውር ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የመርከቦችን ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በፓኪስታን የተደረገው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ከትናንት ሠኞ ጀምሮ የኢራን ወደቦችን ዘግቷል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እግዱ “ያለ ልዩነት” ወደ ኢራን ወደቦች ወይም የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በሚገቡ እና በሚወጡ የሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቋል።

    ሆኖም ጦሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንደማይከለክል ገልጿል።

  4. እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ በአሜሪካ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ

    የእስራኤል እና የሊባኖስ አምባሳደሮች ልዩ የተባለ የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ ያደርጋሉ።

    ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለሥልጣናት ለቀጥታ ንግግር ፊት ለፊት ሲገናኙ በአስርት ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ልዩ በሆነው የቀጥታ ንግግር እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    የሁለቱ ጎረቤት አገራት ንግግር አሜሪካ እና ኢራን የመካከለናውን ምሥራቅ ቶርነት ለመቋጨት ያደረጉት ስምምነት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሚደረግ ነው።

    መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአገራቱ መካከል የከፍተኛ ባለሥልጣናት የቀጥታ ንግግር ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይም ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የሊባኖስ ሹማምንት በመጀመሪያ እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የከፈተችው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የማስማማት ፍላጎት አላቸው።

    ይሁን እንጂ እስራኤል በኢራን የሚደገፈው ቡድን ትጥቁን መፍታት አለበት በሚል ሀሳቡን ውድቅ አድርጋዋለች።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ የሁለቱ አገራትን ንግግር ውድቅ በማድረግ ስምምነት ለሚደረስበት ማንኛውም ጉዳይ እንደማይገዛ አስታውቋል።

    የአሁኑ የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ግጭት ለሊባኖስ አውዳሚ ሆኗል። 500 ሴቶችን፣ ሕፃናትን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ2,000 ሠዎች በላይ ሠዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

  5. የተመድ ዋና ጸሐፊ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ እንደሚቋጭ ተስፋ በማድረግ በድጋሚ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ።

    ጉቴሬዝ፤ ጦርነቱን ለማብቃት የሚያስችል “ወታደራዊ አማራጭ እንደሌለ ግልጽ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ሁለቱ አገራት ለሁለት ሳምንት የደረሱበት የተኩስ አቁም “ፍጹም መጠበቅ እንዳለበት” ያሳሰቡት ዋና ጸሐፊው፤ “ሁሉም” የስምምነቱ “ጥሰቶች ሊቆሙ እንደሚገባ” ገልጸዋል።

    “ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አክለውም ሁሉም አገራት “በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገውን ጨምሮ የመርከቦች የጉዞ ነጻነትን ማክበር እንዳለባቸው” አስታውሰዋል።

    ጉቴሬዝ ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የወሰደችውን እርምጃ በመድገም ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን ካገዱ በኋላ ነው። ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ለማስገደድ መሆኑን ተናግረዋል።

  6. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢራንን "በኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት" ከሰሱ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የኢራን መንግሥት የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዘጋት “የኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት” ተግባር እየፈፀመ ነው ሲሉ ክስ አቀረቡ።

    ጄዲ ቫንስ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጨዋታውን ሁለቱም አገራት መጫወት እንደሚችሉ አሳይተዋል ሲሉ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ የወሰዱትን የእግድ እርምጃ አንስተዋል።

    ኢራናዊያን “ኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት የሚፈፅሙ” ከሆነ አሜሪካ “ምንም የኢራን መርከቦች እንዳይወጡ የማድረግ” መርኅን ትከተላለች ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ እርሳቸው የተሳተፉበት እና በፓኪስታን ኢስላማባድ ባለፈው ቅዳሜ የተደረገው ድርድር ትልቅ ለውጦች የታዩበት እንደሆነም አንስተዋል።

    “ኳሱ ኢራን ሜዳ ውስጥ ነው” ብለዋል። ኢራን ለውጥ በማድረግ “በወሳኝ ጉዳዮች” ላይ የአሜሪካን ፍላጎት መቀበል እንዳለባት ተናግረዋል።

    አሜሪካ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም መቆጣጠር እና ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማታለማ ማረጋገጫ ማግኘት ትፈልጋለች።

  7. ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ለአምስት ዓመት እንዲታገድ የሚያደርግ የስምምነት እቅድ ማቅረቧ ተዘገበ

    ኢራን የቅዳሜ ዕለቱ ንግግር ያለ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ዩራኒየም የማበልጸግ ተግባሯን ለአምስት ዓመት እንደምታግድ የሚገልጽ እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ።

    የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የሚደረገው እገዳ ለ20 ዓመታት እንዲቆይ በድርድሩ ወቅት የጠየቀችው አሜሪካ የቴህራንን እቅድ ውድቅ ማደረጓንም ዘገባው አመልክቷል።

    የኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናትን የጠቀሰው የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ፤ ቴህራን ይህንን እቅድ ለትራምፕ አስተዳደር ያቀረበችው ሰኞ ዕለት እንደነበር ይገልጻል።

    አሜሪካ ከእገዳው በተጨማሪ እጅግ የተበለጸገው የኢራን ዩራኒየም ከአገሪቱ እንዲወጣ ጠይቃ እንደነበር እና ቴህራን ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓ ተዘግቧል።

    ይሁን እንጂ ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟን ለኒውክሌር ጦር መሣሪያነት እንዳይውል ለማድረግ በከፍተኛ መጠን ለመበረዝ አማራጭ ማቅረቧ ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን በተካሄደው ድርድር የሰላም አማራጮቻቸውን አቅርበው ስምምነት ላይ አልደረሱም። ይሁን እንጁ ሁለተኛ ዙር የፊት ለፊት ንግግር ሊካሄድ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው።

    የኢራን የኒውክሌር ፍላጎት ሁለቱን አካላት ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት እንደሆነ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሆርሙዝን እንቅስቃሴ ያገዱት ኢራን እንድትስማማ ለማስገደድ መሆኑ ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን የዘጉት ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እና ጦርነቱን ለመቋጨት የሚደረስ ስምምነትን እንድትቀበል ለማስገደድ መሆኑን ተናገሩ፥

    ፕሬዝዳንቱ፤ ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ አለመቀየራቸውም ገልጸዋል። ትራምፕ ትናንት በዋይት ሀውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ኢራን ክፉኛ ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ከትናንት 11 ሰዓት ጀምሮ ወደ ኢራን ወደቦች መግባት እና ከወደቦቹ መውጣት ተከልክሏል። ግዙፉን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ጨምሮ ሦስት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ መጠጋታቸው በሳተላይት ምስሎች ተረጋግጧል።

    ትራምፕ በትናንቱ መግለጫቸው ላይ ስለዚህ ጉዳይ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አንድ አገር ዓለምን እንዲያስፈራራ ወይም እንዲያሰቃይ መፍቀድ አንችልም፤ ምክንያቱም እነሱ እያደረጉት ያሉት ይህንን ነው” ሲሉ እገዳውን ያደረጉበትን ምክንያት ጠቅሰዋል።

    በአሁኑ ሰዓት ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለ “ምንም ዓይነት ውጊያ አለመኖሩን" ጠቀሱት ትራምፕ፤ “እገዳ ጥለናል፤ ምንም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፓኪስታን ውስጥ ያደረጉት ድርድር የተጠናቀቀው ያለ ስምምነት ነበር። እንደ ትራምፕ ገለጻ ሁለቱን አገራት ያላስማማው የኒውክሌር ጉዳይ ነው።

    “በብዙ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናል፤ እዚያ ጉዳይ ላይ ግን አልተስማሙም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ አይኖራትም” ሲሉም አቋማቸውን አረጋግጠዋል።

    ይሁን እንጂ በመጨሻም ከኢራን ጋ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ “እርግጠኛ” መሆናቸውን ገልጸዋል። “የማይስማሙ ከሆነ፣ ስምምነት አይኖርም” ብለዋል።

    አክለውም ግን ኢራን መሪዎች ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ እና “ከተገቢዎቹ ሰዎች” የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

  9. የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱን ለማስቆም አሁንም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ

    የቅዳሜ ዕለቱን ድርድር ያስተናገዱት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ተናገሩ።

    የሁለቱ አገራት ልዑኮች ከትናንት በስቲያ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ተገኝተው ለ21 ሰዓታት የዘለቀ ድርድር ቢያደርጉም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ተለያይተዋል።

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት “ጉዳዩን ለመፍታት ሙሉ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    “የተኩስ አቁሙ አሁንም ዘልቋል፤ አሁን የተናገርኩ ባለሁበት ሰዓት ቀሪ ጉዳዮችን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ሲሉ ለካቢኔያቸው መናገራቸውን የዜና ወኪሊ አጃንስ ፍራንስ ፕረስ (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።

  10. ትራምፕ ወደ አሜሪካ እገዳ የሚጠጉ የኢራን መርከቦች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው አስጠነቀቁ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መድረሱን ተከትሎ፤ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ጣለውን እገዳ የሚጠጉ የኢራን “የጥቃት መርከቦች ይወገዳሉ” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ እስካሁን ኢራን ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት “ፈጣን አጥቂ” ሲሉ የጠሯቸው የኢራን መርከቦች በአሜሪካ አለመመታታቸውን ገልጸዋል።

    “የኢራን ባሕር ኃይል የባሕሩ ወለል ላይ ተኝቷል፤ ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል፤ 158 መርከቦች ወድመዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

    “ያልመታናቸው ‘ፈጣን አጥቂ መርከቦች’ ብለው የሚጠሯቸውን ነው፤ ምክንያቱም እምብዛም ስጋት ናቸው ብለን አንቆጥራቸውም” ብለዋል።

    አክለውም፤ “ከእነዚህ መርከቦች የትኛውም ወደ ጣልነው እገዳ የሚመጣ ከሆነ፤ ባሕር ላይ በነበሩ የአደንዛዥ እፅ ሻጮች ጀልባዎች ላይ የተጠቀምነው የግድያ ስርዓት በመጠቀም ወዲያውኑ ይወገዳል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ከመስከረም አንስቶ በካረቢያን ባሕር እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በርካታ ገዳይ ጥቃቶችን ፈጽሟል። በእነዚህ ጥቃቶች አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ናቸው የተባሉ 130 ሰዎች ተገድለዋል።

  11. የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚን ጨምሮ ሦስት የጦር መርከቦች በኦማን ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ ታዩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ እና ከወደቦቹ የሚወጡ መርከቦችን እንቅስቃሴ ለማገድ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ 11 ሰዓት ላይ ተጀምሯል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም የፕሬዝዳንቱ እገዳ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመረዳት ሲሞክር ቆይቷል።

    ቅዳሜ ዕለት የተነሱ ሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ግዙፉ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ምሥራቃዊ ጫፍ በኩል ይገኛል።

    ግዙፉ የጦር መርከብ ያለበት ርቀት ከኢራን የባሕር ዳርቻዎች ያለው ርቀት 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ይህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀ መርከብ በዚህ ልክ ወደ ባሕረ ሰላጤው ቀርቦ ታይቶ አይታወቅም።

    በሳተላይት ምስሉ ላይ የሚታዩት በቅርብ ያሉ ሌሎች መርከቦች ያላቸው ቅርጽ እና ግዝፈት ከአሜሪካ ባሕር ኃይል የሚሳዔል አውዳሚ መርከቦች ጋር ተመሳሳይ ነው።

    እነዚህ መርከቦች ከአውሮፕላን ጫኙ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ ጋር በአንድነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይገመታል። ይሁን እንጂ ምስሉ ላይ የሚታዩት የትኛዎቹ መርከቦች እንደሆኑ በትክክል መለየት አልተቻለም

  12. ትንታኔ፡ አሜሪካን የበለጠ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከትተው የሆርሙዝ ወሽመጥ እገዳ

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን የማገድ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷ በሕጋዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ገብታበት የማታውቀው አደገኛ ቀጣና ውስጥ ያስገባታል ይላል የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢው ፍራንክ ጋርድነር።

    እንደ ጋርድነር ትንተና፤ አሜሪካ እገዳውን ማስፈጸም ብትችልም የተወሰነ ስጋት ይጋረጥባታል።

    አሁን የአሜሪካ ባህር ኃይል ጦር መርከቦች እንቅስቃሴ እንደ ሴይ፣ ባንዳር አባስ እና ጃስክ ባሉ ወደቦች አቅራቢያ በማንዣበብ ብቻ አያበቃም። ይህ ደግሞ በድሮን፣ በሚሳዔል ወይም በአጥፍቶ ጠፊ ‘ካሚካዚ’ ፈጣን ጀልባዎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል።

    የአሜሪካ ጦርን የመካከለኛው ምሥራቅ እንቅስቃሴን የሚሸፍነው ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ የትኛዎቹ መርከቦች የኢራን እንደሆኑ እና የትኛዎቹ ከኢራን ወደቦች እንደተነሱ ለማረጋገጥ የሳተላይት ምስል እና ሌሎች የስለላ መረጃዎችን ሊጠቀም ይችላል።

    መርከቦቹ፤ ጉዟቸውን ለመከታተል የሚያስችለውን የመለያ ስርዓት (AIS - automatic identification system) ቢያጠፉም እንኳ፤ ልክ የኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ እንደገቡ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የአሜሪካ ጦር መርከቦች መገኘታቸው እና መያዛቸው አይቀርም።

    ኢራን ይህንን የአሜሪካ ዛቻ የባሕር ላይ ውንብድና ስትል ጠርታዋለች። ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ስትዘጋ ተመሳሳይ አይነት ክስ ቀርቦባት ነበር።

    እስላማዊው ሪፐብሊክ በባሕረ ሰላጤው አገራት ወደቦች ላይ አጸፋ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

    የኢራን አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ ነገር ሌላኛው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። በእርግጥ አሜሪካ ንብረትነቱ የቻይና የሆነ መርከብ ወይም ጭነት ላይ ወታደሮቿ እንዲወጡ ለማድረግ ወይም መርከቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዝግጁ ነች?

    ብዙም ሳይርቅ ጅቡቲ ውስጥ ወታደራዊ ሠፈር ያላት ቻይና፤ መርከቦቿን በታጠቀ የባሕር ኃይሏ ለማጀብ ከወሰነችስ ምን ይፈጠራል?

  13. የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝ እገዳን ጥሰው የሚጓዙ መርከቦች “እንደሚጠለፉ” አስጠነቀቀ

    የአሜሪካ ጦር፤ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተምሥራቅ በሚገኘው የአረቢያን ባሕር ላይ የተጣለውን እገዳ ለማስፈጸም መዘጋጀቱን እንዲሁም እርምጃው መርከቦች ያነገቡትን ባንዲራ ሳይለይ በሁሉም ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማስታወቁ ተዘገበ።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ይህንን ያለው ከአንድ ሰዓት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው ዕገዳ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለባሕርተኞች በላከው መልዕክት እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጿል።

    ሮይተርስ የተመለከተው የዕዙ ማስታወሻ፤ “ፈቃድ ሳያገኝ ዕገዳ ወደተጣለበት አካባቢ የሚገባ ወይም ከዚያ የሚወጣ ማንኛውም መርከብ ለጠለፋ፣ አቅጣጫ ማስቀየር እና በቁጥጥር ስር መዋል እርምጃዎች ይዳረጋል” ይላል።

    "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ሲልም ያብራራል።

    የኮንትሮባንድ ጭነት መኖር እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል ገለልተኛ መርከቦች ፍተሻ ሊደረግባቸው እንደሚችል ለባሕርተኞች የተላከው ማስታወሻ ገልጿል።

    እንደ ምግብ፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ያሉ ሰብአዊ ጭነቶች ፍተሻ ተደርጎባቸው ጉዞ እንዲያደርጉ እንደሚፈቀድላቸው መግለጹንም ዘገባው ያመለክታል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ይተገበራል ያሉት እገዳ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው 11 ሰዓት ላይ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ በላከው ማስታወሻ፤ እገዳው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎችን ጨምሮ መላው "የኢራን የባህር ዳርቻን" እንደሚያካትት አስታውቋል። ሆኖም እርምጃው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎች ላይ “ብቻ እንደማይወሰን” ገልጿል።

  14. እስራኤል፤ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን እንደምትደግፍ አስታወቀች

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን ማገዷን እንደሚደግፉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔያቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ የባሕር ጉዟቸው ላይ እገዳ ለመጣል ወስነዋል። በእርግጥም ይህንን ጠንካራ አቋም እንደግፋለን” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ፓኪስታን ውስጥ ካደረጉት ውጤት አልባው ንግግር በኋላ እሁድ ዕለት ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

    ቫንስ “ዋነኛው ጉዳይ ሁሉንም የበለጸጉ [የኒውክሌር] ቁሶች ማስወገድ እና ምንም ተጨማሪ የማበልጸግ ተግባር እንደማይኖር ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር” ሲሉ እንደነገሯቸው በኔትያናሁ በቪዲዮ መልዕክታቸው አንስተዋል።

    እንደ ኔትያናሁ ገለጻ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ከፓኪስታ የተመለሱበት አውሮፕላን ውስጥ ሆነው የደወሉላቸው ሲሆን ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር ደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ አሜሪካ እና እስራኤል ያላቸው ግንኙነት በመካከላቸው መራራቅ እንዳለ ከሚጠቁሙ አስተያየቶች “ፍጹም ተቃራኒ” እንደሆነ ተናግረዋል።

  15. ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን የተመለከተ ኮንፈረንስ ሊያዘጋጁ ነው

    የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ አገራቸው እና ዩናይትድ ኪንግደም “በመጪዎቹ ቀናት” በሆርሙዝ “ወሽመጥ ላይ የመርከብ ጉዞ ነጻነት መመለስን የተመለከተ” ኮንፈረንስ እንደሚያዘጋጁ አስታወቁ።

    ይህ እርምጃ “የመከላከል ተልዕኮ ብቻ” እንደሆነ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የገለጹት ማክሮን፤ “ከግጭቱ ተዋጊ ወገኖች የተነጠለ” እና “ሁኔታው እንደፈቀደ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደ” መሆኑንም አስረድተዋል።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርም በተመሳሳይ ሁለቱ አገራት በጋራ የሚያስተናግዱት ጉባኤ "ግጭቱ ሲያበቃ ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ፣ ገለልተኛ፣ ዓለም አቀፍ እቅድ ለማዘጋጀት" ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ወይም ከኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደምትዘጋ መግለጿን ተከትሎ በባሕረ ሰላጤው ውጥረቱ አይሏል።

    ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ ልትወስድ ያቀደችውን እርምጃ እንደማትደግፍ አስታውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስታርመር “የኢነርጂ ዋጋ በተቻለ ፍጥነት እንዲቀንስ የምናደርግበት መንገድ ይህ ነው” ሲሉ የሚደግፉት የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን እንደሆነ ገልጸዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ቀደም በወሽመጡ ላይ የጉዞ ነጻነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ግብ ያላቸው ከ40 በላይ አገራት ወኪሎችን ሰብስባ እንደነበር ይታወሳል።

  16. ፖፕ ሊዮ የትራምፕ አስተዳደርን “አልፈራም” ሲሉ ከፕሬዝዳንቱ ለቀረበባቸው ከባድ ትችት ምላሽ ሰጡ

    የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፤ የትራምፕ አስተዳደርን “እንደማይፈሩ” እንዲሁም የኢራን ጦርነትን በተመለከተ በያዙት አቋም ምክንያት ከፕሬዝዳንቱ ያልተለመደ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ግጭቱን መቃወም እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ “ወንጀል ላይ ደካማ፣ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የከፋ” ሲሉ ፖፕ ሊዮን ወቅሰዋል። ቆይተው ደግሞ “አድናቂው አይደለሁም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ወደ አልጄሪያ እየተጓዙ የነበሩት ፖፕ ሊዮ በበኩላቸው ከትራምፕ ጋር ክርክር ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ፤ ነገር ግን ስለ ሰላም መናገራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የኢራን ጦርነት ላይ ብርቱ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ትራምፕ የኢራንን ሥልጣኔ እንደሚያወድሙ በተናገሩ ጊዜም ዛቻውን “ተቀባይነት የሌለው” በማለት ተችተዋል። ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት ሰላማዊ መንገድ እንዲፈልጉም መክረዋል።

    የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከዓለም መሪዎች ለሚሰጡ አስተያየቶች ቀጥታ ምላሽ መስጠታቸው የተለመደ አይደለም።

    ፖፕ ሊዮ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚገልጽ ጽሑፍ እሁድ ዕለት ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ የለጠፉት ትራምፕ፤ “ኒውክሌር መሣሪያ ላይ ደካማ” ነበር ሲሉ አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ያስገባትን ‘ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያ ልትገነባ ነው’ የሚል ክስ ጠቅሰዋል።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነው የተመረጡት “አሜሪካዊ ስለሆነ ነው፤ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ ጋር በተያያዘ መፍትሔ ማግኛው ጥሩ መንገድ ይሄ ነው ብለው አስበው ነበር” ሲሉም ጽፈዋል።

    ወደ አልጄሪያ በሚጓዙበት አውሮፕላን ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ለትራምፕ አስተያየት ምላሽ የሰጡት ፖፕ ሊዮ፤ ራሳቸውን ፖለቲካ ውስጥ ሚና እንዳለው ሰው እንደማይመለከቱ፤ ይልቁንም የሰላም መልዕክትን እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል።

    “የትራምፕ አስተዳደርን ወይም የወንጌል መልዕክትን ከፍ ባለ ድምጽ መናገርን አልፈራም፤ እዚህ ያለሁትም ይህንን ለማድረግ እንደሆነ ነው የማምነው፤ ቤተ ክርስቲያኗም ለዚሁ ነው ያለችው” ብለዋል።

    “ዛሬ በዓለም ላይ እጅግ በርካታ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። እጅግ ብዙ ንጹኃን ሰዎች እየተገደሉ ነው። የሆነ ሰው መነሳት እና ‘ይህንን ለማድረግ የተሻለ መንገድ አለ’ ብሎ መናገር አለበት” ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

  17. የአሜሪካ የባሕር ኃይል እርምጃ ቻይናን ለምን ሊጎዳ ይችላል?

    ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የኢራንን ወደቦችን መዝጋት እንደሚጀምሩ ሲዝቱ የቻይና መንግሥት ሁለቱም ወገኖች እንዲረጋጉ እና እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።

    ቻይና በሳምንቱ መጨረሻ በፓኪስታን በተካሄደው የሰላም ድርድር ላይ ቴህራን እንድትገኝ ለማሳመን ተሳትፎዋ ምን አንደነበር እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።

    ነገር ግን ቤይጂንግ ይህ ጦርነት እንዲቆም እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም።

    ቻይና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም የምትፈልገው የኢራንን ነዳጅ ስለምትፈልግ ብቻ አይደለም።

    ኢራን ለቻይና የምታቀርበው የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የፍላጎቷን 13 በመቶ ብቻ ነው። አስፈላጊ ከሆነ ቤይጂንግ ይህንን ከሌላ ቦታ መሸመት ትችላለች።

    ነገር ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ካሉ ሌሎች የባህረ ሰላጤው አገራት ለምታገኘው የኢነርጂ አቅርቦቶች ቁልፍ የትራንስፖርት መስመር ነው።

    ቤይጂንግ ከዋሽንግተን ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ በገባችባቸው ባለፉት ዓመታት የመካከለኛው ምሥራቅ ለቻይና በጣም ወሳኝ ሆኗል። ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የምታደርገው የውጭ ንግድ በ2025 ወደ ሌላ ዓለም ከምትልከው በእጥፍ እድገት አሳይቷል።

    የቻይና እውነተኛ ፍላጎቶች ያለው እዚህ ላይ ነው። ኢኮኖሚዋ በዓለም ዙሪያ ላሉ አገሮች ምርቶቿን በመሸጥ ላይ በእጅጉ ያተኮረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት ለቤይጂንግ ከባድ ስጋት ይሆናል።

    ፕሬዝዳንት ዢ አሜሪካ እንዲህ ባለ ስትራቴጂካዊ የባሕር ትራንስፖርት መስመር ላይ የተቆጣጣሪነት ምንም አይነት ሚና እንዲኖራት አይፈልጉም።

    ይህ ቤይጂንግ ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስድ ጫና ሊያሳድርባት ይችላል። ነገር ግን ቻይና ለረዥም ጊዜ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲ ያላት ሲሆን እስካሁን ድረስ ለኢራን የረዥም ጊዜ ደህንነት ዋስትና ለመስጠት ፍላጎት አላሳየችም።

  18. ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ ሸጣለች መባሉን አስተባበለች

    ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ አቅርባለች ወይንም ለማቅረብ ታስባለች የሚለው ውንጀላ መሠረተ ቢስ ነው ስትል አጣጣለች።

    ሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው ለኢራን የጦር መሣሪያ አቅርባለች ወይም ለማቅረብ አቅዳ ነበር የሚለውን ዘገባ “መሠረተ ቢስ ውንጀላ” ሲሉ አጣጥለውታል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የደህንነት ምንጮችን በመጥቀስ ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ ታቀርባለች ሲሉ መዘገባቸውን ተከትሎ ስጋት ተፈጥሯል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቤይጂንግ ለቴህራን ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች በሚል 50 በመቶ አዲስ ታሪፍ እንደሚጣልባት ዝተው ነበር።

    ቻይና የፕሬዚዳንቱን ውንጀላ ያስተባበለችው ሲኤንኤን ሦስት የአሜሪካ የደህንነት ምንጭ ጠቅሶ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለኢራን አዲስ የአየር መቃወሚያ ስርዓት ልታቀርብ ነው ሲል መዘገቡን ተከትሎ ነው።

    በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ እንዲሁ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ቤጂንግ ትከሻ ላይ ተደርጎ የሚተኮስ ሚሳዔል ሳትልክ አትቀርም ብሏል።

    ቻይና እነዚህን ዘገባዎች በማስተባበል "ወታደራዊ ቁሳቁሶች ወደ ሌሎች አገራት በሚላክበት ወቅት የአገሪቱን የውጭ ንግድ ቁጥጥር ሕጎች እና ደንቦች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግዴታዎች መሠረት ጥብቅ ቁጥጥሮችን በመተግበር ሁልጊዜ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት የተሞላበት እርምጃ እንወስዳለን” ብላለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን “መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ወይም ይሁነኝ ተብለው የሚደረጉ ማዛመዶችን እንቃወማለን” ሲሉ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።

  19. የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሊባኖስ ላይ ጥቃት ሲፈፅም ሄዝቦላህ ደግሞ እስራል ላይ ሮኬት ተኮሰ

    አሜሪካ የኢራንን ወደቦች እንደምትዘጋ ካሳወቀች በኋላም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቱ ቀጥሏል።

    ዛሬ ሠኞ ሄዝቦላህ ድሮኖችን ተጠቅሞ ሸሎሜ በተባለ ስፍራ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታውቋል። እስራኤል በአካባቢው የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ ዘመቻውን እያስፋፋ መሆኑን አስታውቋል።

    ቢንት ጅቢል በተባለ ስፍራ በፈፀመው ጥቃት 100 የሄዝቦላህ ተዋጊዎች መገደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠር የጦር መሣሪያ በአካባቢው ማግኘቱን ገልጿል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነገ ማክሰኞ ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።

  20. የኢራን ጦር የአሜሪካ እርምጃ ‘የባሕር ላይ ውንብድና’ ነው አለ

    የኢራን ወታደራዊ ኃይል ዋሽንግተን የኢራን ወደቦችን ለመዝጋት ያሳለፈችው ውሳኔ ሕገ ወጥ እና የባሕር ላይ ውንብድና ነው አለ።

    ጦሩ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድም ዝቷል።

    በአገሪቱ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት በኩል በታተመ መግለጫ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯን ትቀጥላለች ያለ ሲሆን፤ ጦርነቱ ቢቋጭ እንኳ ከጠላት ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በኢራን የውሃ ግዛት ላይ የመተላለፍ መብት የላቸውም ብሏል።

    የኢራን ጦር ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራትን በማስጠንቀቅ፤ በቀጣናው የወደቦች ደኅንነት “ለሁሉም አልያም ለማንም አይሆንም” ብሏል።

    የኢራን ወደቦች በአሜሪካ ዒላማ ከሆኑ “በፋርስ ሰላጤ እና በኦማን ባሕር ማንም ደኅና አይሆንም” በማለት አስጠንቅቋል።