ቀጥታ, ኢራን በጦርነቱ እስካሁን 270 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት እንደደረሰባት ገለጸች

የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋቴሜህ ሞሃጀራኒ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ40ቀናት በዘለቀው ጥቃታቸው ያደረሱት ውድመት "ቅድመ ግምት" 270 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ቁጥር ግን ሊለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን በጦርነቱ እስካሁን 270 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት እንደደረሰባት ገለጸች

    ኢራን በጦርነቱ ምክንያት የደረሰባትን ውድመት ግምት ውስጥ በማስገባት የካሳ ክፍያን የድርድሩ አካል ለማድረግ በማሰብ የጉዳቱን መጠን ማስላት መጀመሯን ከአብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘገበ።

    የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋቴሜህ ሞሃጀራኒ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ40ቀናት በዘለቀው ጥቃታቸው ያደረሱት ውድመት "ቅድመ ግምት" 270 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ቁጥር ግን ሊለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

    በኢራን የሚገኙ ባለሥልጣናት የደረሰውን ውድመት እያሰሉ መሆኑን የተናገሩት ባለሥልጣኗ ይህም በሕንፃዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና ኢንዱስትሪዎች ሥራ በማቆማቸው ምክንያት የሚደርሰውን ኪሳራ ያካትታል ማለታቸውን ታስኒም ዘግቧል።

    ሞሃጀራኒ ለኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ ኢርና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ውይይት ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ ካሳ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ቀደም ሲል በፓኪስታን በተካሄደው ውይይት ላይ "ጠቃሚ ውይይቶች" እንደተደረጉ ቢናገሩም ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ግን አልተደረሰም።

  2. የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከአሜሪካ ጋር ቀጣይ ንግግር ስለመኖሩ “መረጃ የለም“ አሉ

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ኢርና፣ በአሜሪካ እና በቴህራን መካከል አደራዳሪ በመሆን እያገለገለች ካለችው ፓኪስታን ጋር የመልዕክት ልውውጦች ቢኖሩም ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ግን የተደረሰ ስምምነት ስለመኖሩ “መረጃ የለም” አለ።

    የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሰው የዘገቡት የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያለውጤት ከተጠናቀቀው ድርድር ወዲህ ከፓከሲታን ጋር ያለው የመልዕክት ልውውጥ “አሁን ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ” መሆኑን ገልጸዋል።

    ቀደም ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል አሜሪካ እና ኢራን በዚህ ሳምንት ዳግም በኢዝላማባድ ተገናኝተው ውይይታቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

    ሮይተርስ የጠቀሳቸው ምንጮች ሁለቱ አገራት መቼ ወደ ድርድሩ እንደሚመለሱ በግልጽ ባይናገሩም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ግን ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

    አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን “ቁርጥ ያለ ቀን አልተቀመጠም። ልዑካኑ ከአርብ እስከ እሁድ ያለውን ቀን ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢዝላማባድ የተደረገው የሁለቱ አገራት ውይይት የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው።

    ንግግር ዳግም እንደሚጀመር ለሮይተርስ የተናገሩት የመጀመርያው ምንጭ ለሁለቱም አገራት ምክረሃሳቦች የያዘ ሰነድ መሰጠቱን እና ልዑካኖቻቸውን ዳግም ልከው ውይይቱ እንዲቀጥል ተነግሯቸዋል ብለዋል።

    ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው የፓኪስታን ምንጮች ደግሞ ኢዝላማባድ ከሁለቱም አገራት ጋር ቀጣዩ ውይይት መቼ መደረግ እንዳለበት እየተነጋገረች መሆኑን ገልጸዋል።

    አክለውም በሳምንቱ መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ከፍተኛ የፓኪስታን ባለሥልጣን “ኢራንን አነጋግረናል እናም ሁለተኛው ዙር ንግግር ሊደረግበት ስለሚችልበት ሁኔታ በጎ ምላሽ አግኝተናል”

    በፓኪስታን የሚገኘው የኢራን ኤምባሲም ስለ ሁለተኛ ዙር ድርድር ውይይቶች መደረጋቸውን ለሮይተርስ አረጋግጧል።

    ዋይት ሐውስ ግን በጉዳዮ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

  3. ጣሊያን ከእስራኤል ጋር ያላትን ወታደራዊ ስምምነት አቋረጠች

    ጣሊያን ከእስራኤል ጋር የገባችውን ወታደራዊ ስምምነት እንደማታድስ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጆርጂያ ሜሎኒ ተናገሩ።

    ሜሎኒ በየአምስት ዓመቱ ይታደስ የነበረውን የሁለቱን አገራት ወታደራዊ ስምምነት ለማዘግየት የወሰኑት “አሁን ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት” እንደሆነ ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስለጉዳዩ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

    ነገር ግን ሮም እና ቴል አቪቭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ንፋስ ገብቶታል።

    በሊባኖስ የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ጣሊያናውያን ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከተተኮሰባቸው እና አንድ መኪና ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ባለፈው ሳምንት ጣሊያን በሮም የሚገኙትን የእስራኤል አምባሳደርን ጠርታ አነጋግራለች።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እስራኤል በሊባኖስ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “ተቀባይነት የሌለው” ካሉ በኋላ “እንደ ጋዛ ያለ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ ቢሆን መቆም አለበት” ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ እስራኤል የጣሊያን አምባሳደርን በመጥራት አነጋግራለች።

    ሌሎች የአውሮፓ አገራት በተመሳሳይ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የጦር መሣሪያ ውጭ ንግድ ገድበዋል ወይንም ለጊዜው አቁመዋል።

    የጣሊያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለረዠም ጊዜ አገራቸው ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ ሲወተውቱ ነበር።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጣሊያናውያን እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    ሠልፈኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ የፍልስጤም ነጻ አገርነትን እንደ ሌሎች ለመቀበል ዳተኛ በመሆን ተችተዋቸዋል።

    ጣሊያን ከእስራኤል ጦር መሣሪያ ከሚገዙ ሦስት ቀዳሚ አገራት መካከል አንዷ ናት።

    ከፊት ያሉት ሁለት አገራት አሜሪካ እና ጀርመን ናቸው።

  4. የኢራን ፕሬዝዳንት ወታደራዊ እርምጃ አሜሪካ “ራሷ የፈጠረችውን ችግር” ያባብሳል አሉ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዝሽኪያን ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ቴህራን የሰላም ንግግሮችን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን እና ግጭቶችን ለመፍታት የምትመርጠው ዲፕሎማሲያዊ መንገድን እንደሆነ መናገራቸውን የኢራን የዜና አውታሮች ዘገቡ።

    ፕሬዝዳንቱ ለማክሮን ዛቻዎች፣ ጫናዎች እና ወታደራዊ እርምጃዎች ችግሮችን ለመፍታት “አያግዙም” በማለት ተናግረዋል። አሜሪካ “ራሷ የፈጠረችውን ችግር” የሚያባብስ እንደሚሆንም አሳስበዋል

    ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን አሜሪካ ለዓለም አቀፍ ሕግ እና መመሪያ ተገዢ እንድትሆን አውሮፓ ማበረታታት አለበት ሲሉም አክለዋል።

  5. ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት መርከቦች ከአሜሪካ እገዳ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ አለፉ

    አሜሪካ በሆርሙዝ ላይ የጣለችው እገዳ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ቢነገረም ከኢራን ጋር ግንኙነተ ያላቸው አራት መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፋቸውን ቢቢሲ ቬሪፋይ የተነተነው የመርከቦች ጉዞ የትክክል መረጃ አሳየ።

    ‘ማሪን ትራፊክ’ የተሰኘው መርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚመለክተው ከአራቱ ውስጥ ሁለቱ መርከቦች የኢራን ወደቦችን ጎብኝተው ነበር።

    'ክርስቲያና' የተሰኘችው የጭነት መርከብ ወደ ኢራን ባንዳር ኢማን ኮሜኒ ወደብ ተጉዛ የነበረ ሲሆን ሰኞ ዕለት አሜሪካ እገዳ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ደግሞ በወሽመጡ በኩል ማለፏን መረጃው ያሳያል።

    ከኢራን ጋር በሚያደርገው የንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ‘ሪች ስቴሪ’ የተባለ ሌላ መርከብ ደግሞ ትናንት ሌሊት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሻርጃ በመነሳት በሆርሙዝ በኩል ተጉዟል። መርከቡ መዳረሻው ቻይና እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።

    በወሽመጡ በኩል ያለፈው ሌላኛው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ‘ሙርሊኪሻን’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው። ይህም መርከብ ከኢራን ጋር ባለው ንግድ ምክንያት አሜሪካ ማዕቀብ ጥላበታለች።

    መርከቡ ከቻይና ላንሻን እንደተነሳ እና ሌሊቱን በሆርሙዝ በኩል እንዳለፈ መረጃው አሳይቷል። እንደ ማሪን ትራፊክ ከሆነ፤ መርከቡ የታየበት የመጨረሻው ስፍራ ከኢራን ቃሽም ደሴት በስተምስራቅ ያለ አካባቢ ነው።

    ‘ኤልፒስ’ የተባለ ሌላ ነዳጅ ጫኝ መርከብም ማክሰኞ ዕለት ከኢራኑ ቡሼህር ወደብ ተነስቶ በወሽመጡ በኩል ማለፉን የጉዞ መከታተያው ድረ ገጽ መረጃ ይጠቁማል። መዳረሻው ያልታወቀው ይህ መርከብም በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎበታል።

    እነዚህ መርከቦች አድራሻቸውን ለመደበቅ ሲሉ የሚገኙበትን ቦታ በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

    የአሜሪካ ጦር ከትናንት ሰኞ 11 ሰዓት ጀምሮ “ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን በሙሉ” እንደሚያግድ አስታውቆ ነበር።

    "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን" ግን እንደማያስቆም ገልጾ ነበር።

  6. ቻይና “አደገኛው እና ኃላፊነት የጎደለው” የአሜሪካ እገዳ “ውጥረቱን ያባብሳል” ስትል አስጠነቀቀች

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረችውን ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ የጉዞ እገዳ “አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው” በማለት አወገዘ።

    ውጤት ያልተገኘበት የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር ፓኪስታን ውስጥ ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ኢራን ወደቦች ጉዞ እንዳይደረግ ዘግቷል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን፤ እገዳው “ውጥረቱን ከማባባስ እና ቀድሞውንም ደካማ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመሸርሸር” ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው አስጠንቅቀዋል።

    “ይሄ አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ባሕሪ ነው” ሲሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም ቻይና ለኢራን አዲስ የአየር መከላከያ ስርዓት እያዘጋጀች ነው የሚሉ ዘገባዎች “ሙሉ በሙሉ ፈጠራ ናቸው” ሲሉ አስተባብለዋል።

    ይህ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቻይና ለኢራን ወታደራዊ እገዛ የምታደርግ ከሆነ በምርቶቿ ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።

    “አሜሪካ በቻይና ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ለመጣል ይህንን እንደ ምክንያት የምትጠቀም ከሆነ፤ ቻይና በእርግጠኝነት ቆራጥ የአጸፋ እርምጃዎችን ትወስዳለች” ብለዋል።

  7. የተባበሩት መንግሥታት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም አለ

    የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት፤ ማንም አገር ለዓለም አቀፍ ትራንዚት ጥቅም ላይ በሚውለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን የማገድ ሕጋዊ መብት እንደሌለው ገለጹ።

    የዓለም አቀፉ የባሕር ጉዞ ተቋም ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ ከቢቢሲ ራዲዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ ጉዞ መታገዱ አደገኛ ምሳሌን የሚያስቀምጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

    “ግጭት እየተካሄደ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለዓለም አቀፍ ጉዞ ጥቅም ላይ የሚውልን ማንኛውም ወሽመጥ ለማገድ የሚወሰድ እርምጃ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕጋዊ መሠረት የለውም” ብለዋል።

    ዋና ጸሐፊው ዶሚንጌዝ፤ “ተጨማሪ የአጸፋ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር፤ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ ያጡት 20 ሺህ ባሕርተኞች እና በዓለም ዙሪያ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የበረታባቸው ሰዎች ስጋት ይጨምራል” ሲሉም ተናግረዋል።

    “ለረጅም ጊዜ በቆየ ቁጥር ተጽዕኖው በሁላችንም ላይ ለተራዘመ ጊዜ ይቆያል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ 20 በመቶው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋት የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    ለእዚህ የኢራን እርምጃ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን ከትናንት ጀምሮ አግደዋል።

  8. ሆርሙዝ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተዘጋ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት የቻይና መርከብ ማለፉ ተዘገበ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን ካገደ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት አንድ የቻይና ነዳጅ ጫኝ መርከብ በወሽመጡ በኩል ማለፉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    መዳረሻው ቻይና የሆነው ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የበረው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ ላይ እንደነበረ ቢቢሲ የተመለከታቸው መረጃዎች አሳይተዋል።

    “ሪች ስቴሪ” የተሰኘው ይህ ነዳጅ ጫኝ የአሜሪካ እገዳ ትናንት 11 ሰዓት ላይ ከተጀመረ በኋላ በወሽመጡ በኩል በማለፍ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ቀዝፎ የሄደ መርከብ መሆኑን የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጾች አሳይተዋል ተብሏል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ የመርከቡ ባለቤት “ሻንዳይ ዡአንረን ሺፒንግ” የተባለ እና ከኢራን ጋር በሚፈጽመው ንግድ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ኩባንያ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት “ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት ወይም ከዚያ ለመውጣት የሚሞክር ማንኛውም እና ሁሉም መርከቦች” በአሜሪካ ባሕር ኃይል እንደሚታገዱ ገልጸው ነበር።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ እገዳው የሚተገበረው “ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ” መርከቦች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝም በተመሳሳይ “ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚደረጉ ሁሉም የባሕር ላይ ጉዞዎች” እንደሚታገዱ አስታውቋል።

    ይሁን እንጂ "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ብሏል።

    ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እገዳው ሰኞ 11 ሰዓት ላይ ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ አስቀድሞ ባሉት ሰዓታት አራት መርከቦች በወሽመጡ በኩል አልፈዋል።

    ‘ማሪን ትራፊክ’ የተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያሳየው አራቱም የጭነት መርከቦች ናቸው። ምናልባትም ነዳጅ፣ ጋዝ ወይም ኬሚካል ጭነው እንደሚሆን ተገምቷል።

    ማክሰኞ ዕለት ጉዞ ያደረገው ብቸኛ መርከብ ‘ሪች ስቴሪ’ ነው። ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የነበረው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ እንደሆነ እና መዳረሻውን ቻይና እንዳደረገ የ‘ማሪን ትራፊክ’ መረጃ ያሳያል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ በዚህ መርከብ ላይ ያሉት የቻይና የባሕር ሠራተኞች ናቸው።

    በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ሌላ መርከብም ወደ ወሽመጡ ማምራቱን የዜና ወኪሉ ‘ኤልኤስኢጂ’ ከተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መመልከቱን ጠቅሷል።

    ከዚህ ቀደም የሩሲያ እና የኢራን ነዳጅን በማጓጓዝ የሚታወቀው ይህ ሁለተኛ መርከብ፤ ሐሙስ ዕለት ኢራቅ ደርሶ ነዳጅ እንደሚጭን ይጠበቃል ተብሏል።

  9. የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷ "ከባድ" የሉዓዊነት “ጥሰት” ነው አሉ

    በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷን የቴህራን ሉዓላዊነት ላይ የተፈፀመ “ከባድ ጥሰት” ሲሉ አወገዙ።

    አምባሳደር አሚር ሳይድ ኦራቫኒ ለተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፃፉት ደብዳቤ “ሕገ ወጥ” የሆነው እግድ “የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረታዊ መርህዎች ላይ ከባድ ጥሰት የሚፈፅም” ነው ብለዋል።

    ጉቴሬዝ “ሁሉም ወገኖች” ለዓለም የነዳጅ ዝውውር ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የመርከቦችን ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በፓኪስታን የተደረገው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ከትናንት ሠኞ ጀምሮ የኢራን ወደቦችን ዘግቷል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እግዱ “ያለ ልዩነት” ወደ ኢራን ወደቦች ወይም የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በሚገቡ እና በሚወጡ የሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቋል።

    ሆኖም ጦሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንደማይከለክል ገልጿል።

  10. እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ በአሜሪካ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ

    የእስራኤል እና የሊባኖስ አምባሳደሮች ልዩ የተባለ የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ ያደርጋሉ።

    ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለሥልጣናት ለቀጥታ ንግግር ፊት ለፊት ሲገናኙ በአስርት ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ልዩ በሆነው የቀጥታ ንግግር እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    የሁለቱ ጎረቤት አገራት ንግግር አሜሪካ እና ኢራን የመካከለናውን ምሥራቅ ቶርነት ለመቋጨት ያደረጉት ስምምነት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሚደረግ ነው።

    መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአገራቱ መካከል የከፍተኛ ባለሥልጣናት የቀጥታ ንግግር ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይም ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የሊባኖስ ሹማምንት በመጀመሪያ እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የከፈተችው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የማስማማት ፍላጎት አላቸው።

    ይሁን እንጂ እስራኤል በኢራን የሚደገፈው ቡድን ትጥቁን መፍታት አለበት በሚል ሀሳቡን ውድቅ አድርጋዋለች።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ የሁለቱ አገራትን ንግግር ውድቅ በማድረግ ስምምነት ለሚደረስበት ማንኛውም ጉዳይ እንደማይገዛ አስታውቋል።

    የአሁኑ የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ግጭት ለሊባኖስ አውዳሚ ሆኗል። 500 ሴቶችን፣ ሕፃናትን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ2,000 ሠዎች በላይ ሠዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

  11. የተመድ ዋና ጸሐፊ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ እንደሚቋጭ ተስፋ በማድረግ በድጋሚ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ።

    ጉቴሬዝ፤ ጦርነቱን ለማብቃት የሚያስችል “ወታደራዊ አማራጭ እንደሌለ ግልጽ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ሁለቱ አገራት ለሁለት ሳምንት የደረሱበት የተኩስ አቁም “ፍጹም መጠበቅ እንዳለበት” ያሳሰቡት ዋና ጸሐፊው፤ “ሁሉም” የስምምነቱ “ጥሰቶች ሊቆሙ እንደሚገባ” ገልጸዋል።

    “ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አክለውም ሁሉም አገራት “በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገውን ጨምሮ የመርከቦች የጉዞ ነጻነትን ማክበር እንዳለባቸው” አስታውሰዋል።

    ጉቴሬዝ ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የወሰደችውን እርምጃ በመድገም ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን ካገዱ በኋላ ነው። ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ለማስገደድ መሆኑን ተናግረዋል።

  12. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢራንን "በኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት" ከሰሱ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የኢራን መንግሥት የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዘጋት “የኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት” ተግባር እየፈፀመ ነው ሲሉ ክስ አቀረቡ።

    ጄዲ ቫንስ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጨዋታውን ሁለቱም አገራት መጫወት እንደሚችሉ አሳይተዋል ሲሉ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ የወሰዱትን የእግድ እርምጃ አንስተዋል።

    ኢራናዊያን “ኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት የሚፈፅሙ” ከሆነ አሜሪካ “ምንም የኢራን መርከቦች እንዳይወጡ የማድረግ” መርኅን ትከተላለች ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ እርሳቸው የተሳተፉበት እና በፓኪስታን ኢስላማባድ ባለፈው ቅዳሜ የተደረገው ድርድር ትልቅ ለውጦች የታዩበት እንደሆነም አንስተዋል።

    “ኳሱ ኢራን ሜዳ ውስጥ ነው” ብለዋል። ኢራን ለውጥ በማድረግ “በወሳኝ ጉዳዮች” ላይ የአሜሪካን ፍላጎት መቀበል እንዳለባት ተናግረዋል።

    አሜሪካ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም መቆጣጠር እና ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማታለማ ማረጋገጫ ማግኘት ትፈልጋለች።

  13. ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ለአምስት ዓመት እንዲታገድ የሚያደርግ የስምምነት እቅድ ማቅረቧ ተዘገበ

    ኢራን የቅዳሜ ዕለቱ ንግግር ያለ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ዩራኒየም የማበልጸግ ተግባሯን ለአምስት ዓመት እንደምታግድ የሚገልጽ እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ።

    የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የሚደረገው እገዳ ለ20 ዓመታት እንዲቆይ በድርድሩ ወቅት የጠየቀችው አሜሪካ የቴህራንን እቅድ ውድቅ ማደረጓንም ዘገባው አመልክቷል።

    የኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናትን የጠቀሰው የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ፤ ቴህራን ይህንን እቅድ ለትራምፕ አስተዳደር ያቀረበችው ሰኞ ዕለት እንደነበር ይገልጻል።

    አሜሪካ ከእገዳው በተጨማሪ እጅግ የተበለጸገው የኢራን ዩራኒየም ከአገሪቱ እንዲወጣ ጠይቃ እንደነበር እና ቴህራን ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓ ተዘግቧል።

    ይሁን እንጂ ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟን ለኒውክሌር ጦር መሣሪያነት እንዳይውል ለማድረግ በከፍተኛ መጠን ለመበረዝ አማራጭ ማቅረቧ ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን በተካሄደው ድርድር የሰላም አማራጮቻቸውን አቅርበው ስምምነት ላይ አልደረሱም። ይሁን እንጁ ሁለተኛ ዙር የፊት ለፊት ንግግር ሊካሄድ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው።

    የኢራን የኒውክሌር ፍላጎት ሁለቱን አካላት ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት እንደሆነ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

  14. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሆርሙዝን እንቅስቃሴ ያገዱት ኢራን እንድትስማማ ለማስገደድ መሆኑ ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን የዘጉት ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እና ጦርነቱን ለመቋጨት የሚደረስ ስምምነትን እንድትቀበል ለማስገደድ መሆኑን ተናገሩ፥

    ፕሬዝዳንቱ፤ ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ አለመቀየራቸውም ገልጸዋል። ትራምፕ ትናንት በዋይት ሀውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ኢራን ክፉኛ ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ከትናንት 11 ሰዓት ጀምሮ ወደ ኢራን ወደቦች መግባት እና ከወደቦቹ መውጣት ተከልክሏል። ግዙፉን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ጨምሮ ሦስት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ መጠጋታቸው በሳተላይት ምስሎች ተረጋግጧል።

    ትራምፕ በትናንቱ መግለጫቸው ላይ ስለዚህ ጉዳይ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አንድ አገር ዓለምን እንዲያስፈራራ ወይም እንዲያሰቃይ መፍቀድ አንችልም፤ ምክንያቱም እነሱ እያደረጉት ያሉት ይህንን ነው” ሲሉ እገዳውን ያደረጉበትን ምክንያት ጠቅሰዋል።

    በአሁኑ ሰዓት ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለ “ምንም ዓይነት ውጊያ አለመኖሩን" ጠቀሱት ትራምፕ፤ “እገዳ ጥለናል፤ ምንም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፓኪስታን ውስጥ ያደረጉት ድርድር የተጠናቀቀው ያለ ስምምነት ነበር። እንደ ትራምፕ ገለጻ ሁለቱን አገራት ያላስማማው የኒውክሌር ጉዳይ ነው።

    “በብዙ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናል፤ እዚያ ጉዳይ ላይ ግን አልተስማሙም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ አይኖራትም” ሲሉም አቋማቸውን አረጋግጠዋል።

    ይሁን እንጂ በመጨሻም ከኢራን ጋ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ “እርግጠኛ” መሆናቸውን ገልጸዋል። “የማይስማሙ ከሆነ፣ ስምምነት አይኖርም” ብለዋል።

    አክለውም ግን ኢራን መሪዎች ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ እና “ከተገቢዎቹ ሰዎች” የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

  15. የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱን ለማስቆም አሁንም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ

    የቅዳሜ ዕለቱን ድርድር ያስተናገዱት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ተናገሩ።

    የሁለቱ አገራት ልዑኮች ከትናንት በስቲያ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ተገኝተው ለ21 ሰዓታት የዘለቀ ድርድር ቢያደርጉም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ተለያይተዋል።

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት “ጉዳዩን ለመፍታት ሙሉ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    “የተኩስ አቁሙ አሁንም ዘልቋል፤ አሁን የተናገርኩ ባለሁበት ሰዓት ቀሪ ጉዳዮችን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ሲሉ ለካቢኔያቸው መናገራቸውን የዜና ወኪሊ አጃንስ ፍራንስ ፕረስ (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።

  16. ትራምፕ ወደ አሜሪካ እገዳ የሚጠጉ የኢራን መርከቦች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው አስጠነቀቁ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መድረሱን ተከትሎ፤ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ጣለውን እገዳ የሚጠጉ የኢራን “የጥቃት መርከቦች ይወገዳሉ” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ እስካሁን ኢራን ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት “ፈጣን አጥቂ” ሲሉ የጠሯቸው የኢራን መርከቦች በአሜሪካ አለመመታታቸውን ገልጸዋል።

    “የኢራን ባሕር ኃይል የባሕሩ ወለል ላይ ተኝቷል፤ ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል፤ 158 መርከቦች ወድመዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

    “ያልመታናቸው ‘ፈጣን አጥቂ መርከቦች’ ብለው የሚጠሯቸውን ነው፤ ምክንያቱም እምብዛም ስጋት ናቸው ብለን አንቆጥራቸውም” ብለዋል።

    አክለውም፤ “ከእነዚህ መርከቦች የትኛውም ወደ ጣልነው እገዳ የሚመጣ ከሆነ፤ ባሕር ላይ በነበሩ የአደንዛዥ እፅ ሻጮች ጀልባዎች ላይ የተጠቀምነው የግድያ ስርዓት በመጠቀም ወዲያውኑ ይወገዳል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ከመስከረም አንስቶ በካረቢያን ባሕር እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በርካታ ገዳይ ጥቃቶችን ፈጽሟል። በእነዚህ ጥቃቶች አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ናቸው የተባሉ 130 ሰዎች ተገድለዋል።

  17. የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚን ጨምሮ ሦስት የጦር መርከቦች በኦማን ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ ታዩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ እና ከወደቦቹ የሚወጡ መርከቦችን እንቅስቃሴ ለማገድ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ 11 ሰዓት ላይ ተጀምሯል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም የፕሬዝዳንቱ እገዳ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመረዳት ሲሞክር ቆይቷል።

    ቅዳሜ ዕለት የተነሱ ሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ግዙፉ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ምሥራቃዊ ጫፍ በኩል ይገኛል።

    ግዙፉ የጦር መርከብ ያለበት ርቀት ከኢራን የባሕር ዳርቻዎች ያለው ርቀት 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ይህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀ መርከብ በዚህ ልክ ወደ ባሕረ ሰላጤው ቀርቦ ታይቶ አይታወቅም።

    በሳተላይት ምስሉ ላይ የሚታዩት በቅርብ ያሉ ሌሎች መርከቦች ያላቸው ቅርጽ እና ግዝፈት ከአሜሪካ ባሕር ኃይል የሚሳዔል አውዳሚ መርከቦች ጋር ተመሳሳይ ነው።

    እነዚህ መርከቦች ከአውሮፕላን ጫኙ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ ጋር በአንድነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይገመታል። ይሁን እንጂ ምስሉ ላይ የሚታዩት የትኛዎቹ መርከቦች እንደሆኑ በትክክል መለየት አልተቻለም

  18. ትንታኔ፡ አሜሪካን የበለጠ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከትተው የሆርሙዝ ወሽመጥ እገዳ

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን የማገድ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷ በሕጋዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ገብታበት የማታውቀው አደገኛ ቀጣና ውስጥ ያስገባታል ይላል የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢው ፍራንክ ጋርድነር።

    እንደ ጋርድነር ትንተና፤ አሜሪካ እገዳውን ማስፈጸም ብትችልም የተወሰነ ስጋት ይጋረጥባታል።

    አሁን የአሜሪካ ባህር ኃይል ጦር መርከቦች እንቅስቃሴ እንደ ሴይ፣ ባንዳር አባስ እና ጃስክ ባሉ ወደቦች አቅራቢያ በማንዣበብ ብቻ አያበቃም። ይህ ደግሞ በድሮን፣ በሚሳዔል ወይም በአጥፍቶ ጠፊ ‘ካሚካዚ’ ፈጣን ጀልባዎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል።

    የአሜሪካ ጦርን የመካከለኛው ምሥራቅ እንቅስቃሴን የሚሸፍነው ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ የትኛዎቹ መርከቦች የኢራን እንደሆኑ እና የትኛዎቹ ከኢራን ወደቦች እንደተነሱ ለማረጋገጥ የሳተላይት ምስል እና ሌሎች የስለላ መረጃዎችን ሊጠቀም ይችላል።

    መርከቦቹ፤ ጉዟቸውን ለመከታተል የሚያስችለውን የመለያ ስርዓት (AIS - automatic identification system) ቢያጠፉም እንኳ፤ ልክ የኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ እንደገቡ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የአሜሪካ ጦር መርከቦች መገኘታቸው እና መያዛቸው አይቀርም።

    ኢራን ይህንን የአሜሪካ ዛቻ የባሕር ላይ ውንብድና ስትል ጠርታዋለች። ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ስትዘጋ ተመሳሳይ አይነት ክስ ቀርቦባት ነበር።

    እስላማዊው ሪፐብሊክ በባሕረ ሰላጤው አገራት ወደቦች ላይ አጸፋ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

    የኢራን አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ ነገር ሌላኛው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። በእርግጥ አሜሪካ ንብረትነቱ የቻይና የሆነ መርከብ ወይም ጭነት ላይ ወታደሮቿ እንዲወጡ ለማድረግ ወይም መርከቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዝግጁ ነች?

    ብዙም ሳይርቅ ጅቡቲ ውስጥ ወታደራዊ ሠፈር ያላት ቻይና፤ መርከቦቿን በታጠቀ የባሕር ኃይሏ ለማጀብ ከወሰነችስ ምን ይፈጠራል?

  19. የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝ እገዳን ጥሰው የሚጓዙ መርከቦች “እንደሚጠለፉ” አስጠነቀቀ

    የአሜሪካ ጦር፤ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተምሥራቅ በሚገኘው የአረቢያን ባሕር ላይ የተጣለውን እገዳ ለማስፈጸም መዘጋጀቱን እንዲሁም እርምጃው መርከቦች ያነገቡትን ባንዲራ ሳይለይ በሁሉም ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማስታወቁ ተዘገበ።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ይህንን ያለው ከአንድ ሰዓት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው ዕገዳ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለባሕርተኞች በላከው መልዕክት እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጿል።

    ሮይተርስ የተመለከተው የዕዙ ማስታወሻ፤ “ፈቃድ ሳያገኝ ዕገዳ ወደተጣለበት አካባቢ የሚገባ ወይም ከዚያ የሚወጣ ማንኛውም መርከብ ለጠለፋ፣ አቅጣጫ ማስቀየር እና በቁጥጥር ስር መዋል እርምጃዎች ይዳረጋል” ይላል።

    "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ሲልም ያብራራል።

    የኮንትሮባንድ ጭነት መኖር እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል ገለልተኛ መርከቦች ፍተሻ ሊደረግባቸው እንደሚችል ለባሕርተኞች የተላከው ማስታወሻ ገልጿል።

    እንደ ምግብ፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ያሉ ሰብአዊ ጭነቶች ፍተሻ ተደርጎባቸው ጉዞ እንዲያደርጉ እንደሚፈቀድላቸው መግለጹንም ዘገባው ያመለክታል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ይተገበራል ያሉት እገዳ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው 11 ሰዓት ላይ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ በላከው ማስታወሻ፤ እገዳው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎችን ጨምሮ መላው "የኢራን የባህር ዳርቻን" እንደሚያካትት አስታውቋል። ሆኖም እርምጃው የኢራንን ወደቦች እና የነዳጅ ማደያ ተርሚናሎች ላይ “ብቻ እንደማይወሰን” ገልጿል።

  20. እስራኤል፤ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን እንደምትደግፍ አስታወቀች

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን ማገዷን እንደሚደግፉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔያቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ የባሕር ጉዟቸው ላይ እገዳ ለመጣል ወስነዋል። በእርግጥም ይህንን ጠንካራ አቋም እንደግፋለን” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ፓኪስታን ውስጥ ካደረጉት ውጤት አልባው ንግግር በኋላ እሁድ ዕለት ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

    ቫንስ “ዋነኛው ጉዳይ ሁሉንም የበለጸጉ [የኒውክሌር] ቁሶች ማስወገድ እና ምንም ተጨማሪ የማበልጸግ ተግባር እንደማይኖር ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር” ሲሉ እንደነገሯቸው በኔትያናሁ በቪዲዮ መልዕክታቸው አንስተዋል።

    እንደ ኔትያናሁ ገለጻ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ከፓኪስታ የተመለሱበት አውሮፕላን ውስጥ ሆነው የደወሉላቸው ሲሆን ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር ደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ አሜሪካ እና እስራኤል ያላቸው ግንኙነት በመካከላቸው መራራቅ እንዳለ ከሚጠቁሙ አስተያየቶች “ፍጹም ተቃራኒ” እንደሆነ ተናግረዋል።