በሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 2,167 ደረሰ
እስራኤል በሊባኖስ የአየር ድብደባ ማድረግ ከጀመረች ጀምሮ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 2,167 መድረሱን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ። የሟቾች ቁጥር ማክሰኞ ዕለት ከተገለጸው በ43 ሰዎች ከፍ ማለቱ ተገልጿል።
በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም 7,061 ደርሰዋል።
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ሦስት ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ሦስት የሕክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ባለሥልጣናቱ እስራኤል ሆን ብላ የጤና ባለሙያዎችን ዒላማ ታደርጋለች ሲሉ ወንጅለዋታል።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር የመጀመርያዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች የተገደሉት በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ለማንሳት በሚጥሩበት ወቅት ነው ብሏል።
በማስከተልም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ቡድን ሲሄድም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
እስራኤል ሄዝቦላህ አምቡላንስን እና የሕክምና ተቋማትን ለወታደራዊ ዓላማዎች ይጠቀማል ስትል ማስረጃ ሳታቀርብ ትከስሳለች።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ግን ይህንን ውንጀላ ያስተባብላል።
ሚኒስቴሩ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ 91 የሕክምና ባለሙያዎች ሲገደሉ፣ 208 መጎዳታቸውን ገልጿል።
አክሎም በሕክምና ተቋማት እና አምቡላንሶች ላይ ብቻ 120 ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የሚፈጸሙት ጥቃቶች “ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች” ናቸው ብሏል።
"የሕክምና ባለሙያዎች ቀጥተኛ ዒላማዎች ሆነዋል፣ ይህም . . . በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ የተደነገጉትን ሁሉንም ደንቦች እና መርሆዎች ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቷን ያረጋግጣል” ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እስራኤል በሊባኖስ የፈጸመቻቸው አንዳንድ ድርጊቶች እንደ ጦር ወንጀል የሚታዩ ናቸው ብለዋል።