ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት መግቢያው የሸንገን ቪዛ ቀውስ የፈጠረው ጥቁር ገበያ

ያዘን አምና ከረዥም ጊዜ በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመገናኘት የጣልያንን ቪዛ በጉጉት ሲጠብቅ ነበር።

ሶርያዊው ያዘን 20 ዓመቱ ነው። ለንደን እየተማረ ይገኛል።

ወደ አውሮፓዊቷ አገር ለመሄድ የቪዛ ቀጠሮ ማግኘት አልቻለም።

“ሁለት ወር ሙሉ ሞከርኩ” ይላል። ሌሊት ላይ ሳይቀር የቪዛ ቀጠሮ ለማግኘት ድረ ገጹን ያስስ ነበር።

“ሌሊት ዘጠኝ እና አሥር ሰዓት እሞክር ነበር። አልተሳካም” ሲል ይገልጻል።

ያዘን በስተመጨረሻ ተስፋ ቆረጠ። ቤተሰቡን ማነጋገር የቻለው በቪድዮ ጥሪ ብቻ ነበር።

የቪዛ ቀጠሮ ለማግኘት የሚሞክረው ያዘን ብቻ አይደለም። የሸንገን ቪዛ ለማግኘት ከተለያየ አገር የሚሞክሩ ሰዎችን ቢቢሲ አነጋግሯል።

የበይነ መረብ ምክር

አንዳንዶች ምክር ፍለጋ ፊታቸውን ወደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም እና ኮራ ቡድኖች አዙረዋል።

ምክሩን “በክፍያ” የሚሰጡም አሉ።

በዚህ ውስጥ የቪዛ ቀጠሮ ጥቁር ገበያ ተጧጡፏል። በፍጥነት ቀጠሮ ለማስያዝ ወይም የቀጠሮ ሰዓት ለማስመዝገብ ነው ጥቁር ገበያው የተጀመረው።

ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ መተግበሪያዎችን የሠሩም አሉ።

ወደ 29ኙ የሸንገን አገራት ለመጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች ቪዛ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለዋል።

ቪዛው ከአውሮፓ ኅብረት ውጪ ላሉ አገራት ዜጎች የሚሰጥ ሲሆን፣ በአንድ ወይም ከአንድ በላይ የሸንገን አገር ውስጥ እስከ 90 ቀን መቆየት ያስችላል።

ድኅረ ኮቪድ ቪዛ

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ዓለም አቀፍ ጉዞ ወደ ቀድሞ ገጽታው ተመልሷል።

በ2020 የአውሮፓ ኅብረት 10 ሚሊዮን ሸንገን ቪዛ ሰጥቷል። በ2022 የሰጠው 7.3 ሚሊዮን ነበር።

የአውሮፓ ኅብረት ቱሪዝም እንደሚለው በ2024 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 285 ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደ አሀጉሪቱ ተጉዘዋል።

በ2023 በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 20 በመቶ ይበልጣል።

የሸንገን ቪዛ ጥያቄን የሚያስተናግዱ ተቋማት ኃላፊነቱን ተረክበዋል። የአውሮፓ አገራትን ወክለው ጥያቄውን ያስተናግዳሉ።

ተቋማቱ ቀጠሮ ያስይዛሉ፣ ሰነድ ተረክበው ያስገባሉ፣ አሻራ ይወስዳሉ።

ሁለት ዋነኛ ሥራውን የሚያከናውኑ ተቋማት ቲኤልኤስኮንታክት እና ቪኤፍኤስ ግሎባል ናቸው። በድረ ገጻቸው ላይ ቀጠሮ ማስያዝ ይቻላል። ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ያለው ሂደት ቪዛ የተጠየቀበት አገር ኃላፊነት ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ክርስቲያን ዊንጋንድ እንደሚሉት፣ ኮቪድ አንዳንድ አገራት ለቪዛ ጥያቄ የወከሏቸውን ተቋማት የሠራተኛ ቁጥር እንዲቀንሱ አስገድዷል።

በዚህ ምክንያት ካለው ከፍተኛ ፍላጎት ጋር የሚሄድ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም። የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የቪዛ ቀጠሮ ጊዜን ለመቀነስ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነም አስረድተዋል።

ይህም የቪዛ ክፍያ ላይ 10 ዩሮ በመጨመር ተጨማሪ ሠራተኞችን መቅጠርን ያካትታል።

‘የቪዛ ገበያ’

ተጓዦች ከሚጓዙበት አገር ወይም በሸንገን ቪዛ ከሚገቡባቸወ አገራት አብዛኛውን ቀን ከሚያሳልፉበት አገር ቪዛውን ይጠይቃሉ።

አንዳንድ አገራት ከፍተኛ መጨናነቅ ስለገጠማቸው ተጓዦች ቪዛ ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ነው።

በዚህም ‘የቪዛ ገበያ’ የተባለ ሂደት ውስጥ ለመግባትም ተገደዋል።

የሕንድ የጉዞ ወኪሎች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አኒል ካልሲ እንደሚሉት፣ ተጓዦች ቪዛ ለማግኘት አጭር ጊዜ የሚወስድ አገር መምረጥ ግዴታቸው ሆኗል።

አንዳንድ ተጓዦች የአውሮፓ ኅብረትን ሕግ ለማክበር ሲሉ ተጨማሪ ገንዘብ አውጥተው የተሻለ የቪዛ ቀጠሮ ያለውን አገር መጎብኘትን እንደ አማራጭ ይወስዳሉ።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ክርስቲያን ዊንጋንድ እንደሚሉት፣ ተጓዦች ይህን አማራጭ የሚወስዱት የቪዛ ቀጠሮ ለማግኘት ስለሚቸገሩ ቢሆንም፣ ይህ መንገድ ተጨማሪ የቪዛ ቀጠሮዎች እንዲከማቹም አድርጓል።

ለንደን ያለው የፈረንሳይ ኤምባሲ ስለ ረዥም የቪዛ ቀጠሮ ከቢቢሲ አምና ለቀረበለት ጥያቄ፣ አቅርቦቱ ከፍ ሲል የቪዛ ገበያን እንደሚያበረታታ ገልጾ ነበር።

ሆኖም ግን የቪዛ ገበያ ለብዙዎች ከአቅማቸው በላይ ነው። ጊዜም ይወስዳል። ለጥቁር ገበያ ነጋዴዎች መንገድም ከፍቷል።

ነጋዴዎቹ ተጓዦች ወደመረጡት አገር ለመሄድ አጭር የቪዛ ቀጠሮ እንደሚያገኙላቸው ቃል ይገባሉ።

ጥቁር ገበያ

የ37 ዓመቷ ኒርቫና ግብፃዊ ናት። የምትኖረው ለንደን ነው።

100 ዮሮ በጥቁር ገበያ ከፍላ የጣልያን የቪዛ ቀጠሮ አግኝታለች። ጣልያን የእህቷን ሰርግ ለመታደም ነበር መሄድ የፈለገችው።

“ብዙ የሙሽራዋ ዘመዶች እና ጓደኞች በፈለጉት ጊዜ የቪዛ ቀጠሮ ማግኘት ስላልቻሉ ሰርጉን አልታደሙም” ትላለች።

ጓደኛዋ በሰጠቻት ጥቆማ መሠረት በክፍያ በበይነ መረብ ቀጠሮ የሚያስይዝ አማራጭ ነው የወሰደችው።

ይህ ‘ቦት’ ወይም ሮቦት ራሱን እንደ ሰው በማስመሰል ከሰዎች በላቀ ፍጥነት ይንቀሳቀሳል። ቀጠሮ ሲለቀቅ በፍጥነት ለመያዝ ይውላል።

የ26 ዓመቷ ሲሪን ወደ ኔዘርላንድስ ለኮንሰርት መጓዝ ፈልጋ ለሦስት ወራት የቪዛ ቀጠሮ ማግኘት ሳትችል ቆይታለች።

30 ዩሮ ለቦት ከፍላ በቪኤፍኤስ ግሎባል ድረ ገጽ ላይ የቪዛ ቀጠሮ ሲኖር እንዲያሳውቃት አድርጋለች።

የግል መረጃዋን በጥቁር ገበያ ከማቅረብ የተሻለ ብላ ያሰበችው አማራጭ ነው።

ሲሪን እንደምትለው ልክ እንደሷው ሁሉ ሌሎች ሰዎችም ለቦት ከፍለው እየተጠባበቁ ስለሆነ፣ ቦቱ ክፍት የቪዛ ቀጠሮ እንዳለ ገልጾላት ወደ ድረ ገጹ በገባች ቁጥር የቪዛ ቀጠሮው ተወስዶ ታገኘዋለች።

“በጣም የሚያም ሂደት ስለነበር ተስፋ ቆርጬ ተውኩት” ትላለች።

አንድ የቴሌግራም ቡድን ላይ እስከ ሦስት ቀናት ባለ ጊዜ ውስጥ የቪዛ ቀጠሮ የማስያዝ አገልግሎት ይተዋወቃል።

ቀጠሮ የሚያስይዙ ተቋማት ሂደቱን ‘የቀጠሮ ማጭበርበር’ ነው ይሉታል። ለማስቆም እየሞከሩም ነው።

ቲኤልኤስኮንታክት ለቢቢሲ እንዳለው፣ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የይለፍ ቃል በመስጠት የጥቁር ገበያ ነጋዴዎችን ለማስወገድ እየሞከሩ ነው።

ቪኤፍኤስ ግሎባልም ቦት መጠቀምን “በቅርብ እየተከታተልነው ነው” በማለት እንደ ቲኤልኤስኮንታክት ያለ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

ጥቁር ገበያው እንዴት ይሠራል?

ለዚህ ዘገባ አሕመድ የምንለው የጉዞ ወኪል ጥቁር ገበያ ላይ ባይሠራም እንዴት እንደሚከናወን እንደሚያውቅ ይናገራል።

አንዳንድ የጥቁር ገበያ ደላሎች እና የጉዞ ወኪሎች የቪዛ ቀጠሮ ከሚያስይዙ ተቋማት ሠራተኞች ጋር በመሆን እንደሚሠሩ ይናገራል።

ሠራተኞቹ የቪዛ ቀጠሮ መቼ እና ስንት ሰዓት እንዳለ መረጃ ይሰጣሉ።

“የጥቁር ገበያ ደላሎች እና የጉዞ ወኪሎች ባላቸው ስምምነት መሠረት በዚህ ክፍተት ተጠቃሚ ይሆናሉ” ሲል ያስረዳል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበለት ቲኤልኤስኮንታክት፣ የተባለው ሐሰት ነው ሲል አስተባብሏል።

“የጥቁር ገበያ ደላሎች ተዓማኒነት ለማግኘት የፈጠሩት ነው” ብሏል።

የቀጠሮ ማስያዣ ሰንጠረዥን ማግኘት የሚችሉት ውስን እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውንም ያክላል።

“የእነሱም እንቅስቃሴ በአይቲ ክፍል እና የቪዛ ቀጠሮ ለማስያዝ ውክልና በሰጡን አገራት ቁጥጥር ይደረግበታል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የቪኤፍኤስ ግሎባል የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ኃላፊ አሪፕሬሳድ ቪስዋንታን “እንዲህ ስላለ ቅሬታ መረጃው የለንም። ምርመራ ግን እናደርጋለን” ሲሉ መልሰዋል።

‘በግል ቀጠሮ ማስያዝ’ የሚባል አገልግሎት እንደሌላቸው እና የቪዛ ቀጠሮ ሰንጠረዥ ለሁሉም ተጓዦች ዕይታ ክፍት እንደሆነ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ክርስቲያን ዊንጋንድ እንደሚሉት፣ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የቪዛ ሂደትን የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የቪዛ ሂደትን እንዲያሳልጡ ኃላፊነት የሰጧቸው ተቋማት በአውሮፓ ኅብረት የቪዛ መርኅ እየተመሩ ስለመሆኑ እና ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን መከታተል ይኖርባቸዋል።