ፕሬዚደንት ትራምፕን በመቃወም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ ሠልፍ ተካሄደ

የተቃውሞ ሠልፈኞች መፈክር እና ባንዲራ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን የሚቃወሙ ሠልፎች ተካሄዱ።

የተቃውሞ ሠልፉ የተዘጋጀው "ኖ ኪንግስ" በተባለ ቡድን አማካኝነት ነው።

ሠልፎቹ የተካሄዱት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ያዘጋጁትን ወታደራዊ ትርዒት በመቃወም መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ሠልፍ የተካሄደው በሎስ አንጀለስ እና በሌሎችም አካባቢዎች የፕሬዚደንቱ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ ከቀናት በኋላ ነው።

የሕግ አውጭዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች እና አክቲቪስቶች በኒውዮርክ፣ ፊላዴልፊያ እና ሂዩስተንን ጨምሮ የአሜሪካን ባንዲራ እና ትራምፕን የሚተቹ መፈክሮችን ለያዙ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ንግግር አድርገዋል።

ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የተካሄደው ወታደራዊ ትርዒት፣ የትራምፕ የልደት በዓልም ነበር፣ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት 250ኛ ዓመትን ለማክበር ያለመ ነበር።

ትራምፕ ትርዒቱን በመቃወም የሚካሄድ ማንኛውም ሠልፍ "ከባድ እርምጃ" እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።

አስተባባሪዎቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሠልፎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ በፊላደልፊያ በላቭ ፓርክ በመሰባሰብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የ61 ዓመቷ ነርስ ካረን ቫን ትራይስቴ ለአሶሼትድ ፕሬስ "ዲሞክራሲያችንን መከላከል እንዳለብን ይሰማኛል" ብለዋል።

ትራምፕ በሕዝብ ጤና ኤጀንሲዎች ላይ ያደረጉት የሠራተኞች ቅነሳ በሠልፉ ላይ እንድትሳተፍት ካደረጓት ምክንያቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግራለች።

ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፍ ተሳታፊ ከታየባቸው አንዱ ሎስ አንጀለስ ነው።

በከተማዋ አስተዳደሮች እና የሕግ አስከባሪዎች የሰነድ አልባ ስደተኞችን አፈሳን በመቃወም በተከታታይ የተቃውሞ ሠልፎች መካሄዳቸውን እና የተለያዩ ውድመቶች መድረሳቸውን ተከትሎ በተጠንቀቅ ላይ ነበሩ።

ትራምፕ ከሳምንት በፊት ምንም እንኳ አስተዳዳሪው ጋቪን ኒውሶም እና የአካባቢው ባለስልጣናት ባይፈልጉም በግዛቲቱ ብሔራዊ ዘብ አሰማርተዋል።

ቅዳሜ እለት የብራውን ቤሬትስ የሲቪል መብቶች ቡድን አባል የሆኑት ጆሴ አዜትላ በሎስ አንጀለስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወደ ተቃውሞ ሠልፉ የወጡበት ምክንያት የስደተኞች ጉዳይ ነው።

"ጨካኝ ብቻ ሳይሆን በክፋት የተሞላ ነው፤ ቤተሰብ መለያየት አያስፈልግም" ሲሉ ተናግረዋል።

በሎስ አንጀለስ በፌደራል ሕንጻ አካባቢ በተቃዋሚዎች እና በብሔራዊ ዘብ ወታደሮች መካከል ፍጥጫ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን ሕዝቡን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተተኩሷል።

ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ሕንጻዎችን አለፍ ብሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሠልፈኞች በሰላማዊ መንገድ ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ ከፍተኛው የተቃውሞ ሠልፎች ቢካሄዱም፣ የሕዝብ አስተያየት ግን የስደተኛ ፖሊሲያቸው በስፋት ተወዳጅነት እንዳለው ያሳያል።

"ንጉሦች አንፈልግም" በሚል መሪቃል አደባባይ የወጡት ተቃዋሚዎች ትራምፕ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ገደብ አልፈዋል የሚለውን ትችት ያቀርባሉ።

በወታደራዊ ትርዒት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች፣ ታንኮች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በወታደራዊ ባንድ ታጅበው ሲያልፉ ፕሬዝዳንቱ ተነስተው ወታደራዊ ሠላምታ ሰጥተዋል።

ፕሬዚደንቱ የአገሪቱ ጦር ለሰጠው አገልግሎት ባደረጉት አጭር ንግግር አመስግነዋል።

አክለውም "ወታደሮቻችን ተስፋ አይቆርጡም። አይማረኩም እንዲሁም በጭራሽ አያቋርጡም። ይዋጋሉ፣ ይዋጋሉ፣ይዋጋሉ። እናም ያሸንፋሉ፣ ያሸንፋሉ፣ ያሸንፋሉ" ብለዋል።

በአሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ትርዒት የተካሄደው በፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤችደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው ያካሄዳቸውን ጦርነት ድል ለማክበር በሚል እአአ ሰኔ 1991 ነበር።

በወቅቱ በትርዒቱ ላይ 200,000 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የርችት ማብራት ስነ ስርዓቱን ደግሞ 800,000 ሰዎች መመልከታቸውን ኤልኤ ታይምስ ዘግቧል።

በቅዳሜው ዝግጅት ላይ አየሩ እርጥበታማ ስለነበር እና ዝናብ ይዘንባል የሚል ትንበያ በመኖሩ የታደሙት ሠዎች ቁጥር ከዚያ በታች ነበር።