አፕል ከሳተላይት ጋር መገናኘት የሚያስችለውን አይፎን 14 ስልኩን ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Apple
አፕል ድንገተኛ የሳተላይት ግንኙነት እና የመኪና አደጋን የመለየት ቴክኖሎጂ የተገጠመለትን አይፎን 14ን በአሜሪካ በነበረው ዝግጅት ላይ ይፋ አደረገ።
ኩባንያው አራት አይነት የአይፎን 14 አዳዲስ ስልኮቹን በዋና መቀመጫው ኩፐርቲኖ ያስተዋወቀ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ታዳሚዎች በአካል ተገኝተዋል።
በተጨማሪም በተለይም ለስፖርተኞች የሚሆነውን አልትራ የተባለውን ሰዓቱንም አሳይቷል።
በዚህ ዝግጅት ላይ በቴክኖሎጂ የላቁትን ቀጣዮቹን የአይፎን ስልኮች፣ ሰዓት እንዲሁም የማዳመጫ ምርቶቹን አሳይቷል።
ኩባንያው መጠናቸው የተለያየ አይፎን 14 እና አይፎን 14 ፕላስን ለገበያ ይቀርባሉ ብሏል።
አዲሶቹ የተንቀሳቃሽ ስልኮች የአደጋ ጊዜ ጥሪ በሳተላይት መላክ የሚችሉ ናቸው።
ስልኮቹ የሚያልፉ ሳተላይቶች የት እንዳሉ የሚያሳዩ ሲሆን በነሱም ላይ እንዴት በትክክል መጠቆም እንደሚቻል የሚያሳይ ቴክኖሎጂ ተገጥሞላቸዋል።
መልእክት ለመላክ ከ15 ሰኮንድ እስከ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው የሚወስድባቸው።

የፎቶው ባለመብት, Apple
“የሳተላይት ግንኙነት እንዲፈጥሩ ተደርገው የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኢንቨስትመንቱ ዝቅ ሊደረግ አይገባም” ሲሉ የሲኤኤስ ኢንሳይት ዋና ተንታኝ ቤን ውድ ገልጸዋል።
"ከሳተላይት አቅራቢው ግሎባልስታር ጋር የተደረገ የንግድ ስምምነት እና ለድንገተኛ አገልግሎት መልእክቶችን ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን መገንባትን ጨምሮ ስልኮቹን ለመገጣጠም አፕል ዓመታት ሳይወስድበት አይቀርም።" ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ተንታኝ ፓኦሎ ፔስካቶሬ በበኩላቸው ፈጠራው "ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች" ለሚኖሩ ተጠቃሚዎች ጥሩ ዜና ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"የስልክ አምራቾች ስለ ሳተላይት አጠቃቀም ከፍ ያለ ስፍራ ሰጥተው እንዲህ የሳተላይት ግንኙነት ሲጀምሩ ማየት አበረታች ነው። በመጨረሻም አስተማማኝ እና ጠንካራ ግንኙነት አሁንም በሁሉም ተጠቃሚዎች ዘንድ በጣም ተፈላጊ ነው" ብለዋል ።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አዲሶቹ አይፎኖች ባለ 12 ሜጋ ፒክስል ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን ፈጣን እንቅስቃሴ ያላቸውን ቁሶች ፎቶ ማንሳት ጨምሮ በዝቅተኛ ብርሃን ፎቶ በማንሳት ረገድ 49 በመቶ ማሻሻያ አድርጌባቸዋሁ ብሏል።
አፕል እንዳለው የአይፎን ተጠቃሚዎች ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከሶስት ትሪሊዮን በላይ ፎቶዎችን አንስተዋል።
የአይፎን 14 ዋጋ 799 ዶላር ሲሆን የአይፎን ፕሮ ደግሞ 999 ዶላር ነው።
ሌላኛው አፕል ያስተዋወቀው ሲሪየስ 8 የተሰኘው ሰዓት የመኪና አደጋ መለየት፣ የወር አበባ ዑደቶችን መከታተል እንዲሁም እንቁላል የሚመረትበትን ውጻት (ኦቩሌሽን) ወቅትን የሰውነትን ሙቀት በመለካት ክትትል ማድረግን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይዟል።












