ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደብረ ብርሃን ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል አሉ
ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን እየተናገሩ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በዞኑ ወደ 77ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጾ፣ ከእነዚህ መካከል 31 ሺህ የሚሆኑት በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ ስድስት መጠለያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል።
ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች ያለ በቂ የሰብዓዊ እርዳታ እና ተገንብቶ ባልተጠናቀቀ የግለሰብ ፋብሪካ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ተፈናቅለው እንደመጡ የሚናገሩት ግለሰብ፣ ከልጆቻቸው ጋር አገልግሎት መስጠት ባልጀመረው ፋብሪካ ውስጥ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ተፈናቃዮች ጋር ተጠልለው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በመጠለያው ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት ግለሰቡ፣ ከመካከላቸውም በርካታ ሕጻናት የሚገኙ ሲሆን ወላጆቻቸውን ያጡ በርካቶች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ እናት ወይም አባት ብቻ ያላቸው ብዙ ናቸው።
“በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። መጠለያው በጣም ጠባብ ነው። እንኳን የሚተኛበት መቆሚያ እንኳን አይገኝም” ብለዋል።
ይህ ግለሰብ ተጠልለው በሚገኙበት ቦታ የምግብ እርዳታ እያገኙ ያሉት ከግለሰቦች እንጂ ከመንግሥት ጊዜውን የጠበቀ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ብለዋል።
“ሰው ረሃብ ላይ ነው ያለው። ከዚያ በተጨማሪም የሚተኛበት ፍራሽ የለው። የሚለበስ ልብስ የለም። ሰዉ በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለው።”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላኛው ተፈናቃይ ወቅቱ ዝናብ የሚጥልበት በመሆኑ በዝናብ እና በብርድ ምክንያት ክፉኛ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“አሁን እየዘነበ ነው። በዝናብ ምክንያት መተኛ ቦታ አጥተን በጣም እየተቸገርን ነው” ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ ከስድስት ልጆቻቸው ጋር ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙት እናት በበኩላቸው፣ ያለ ድጋፍ “በረሃብ አለንጋ እየተገረፍን ነው” ይላሉ።
“ሁሉም ነገር ችግር ነው። ምንም የተሟለ ነገር የለንም። ረሃብ ብቻ ነው ያለው። ብዙ ሕጻናት ይዘን ነው ያለነው። በረሃብ እየተሰቃየን ነው።” ሲሉም ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙት ከ77ሺህ ተፈናቃዮች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ከኦሮሚያ ክልል የመጡ መሆናቸውን የሚናገሩት የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አበባው መለሰ፣ የተቀሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ አካባቢዎች ቤታቸው ፈርሶባቸው የመጡ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
አሁን ላይም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ወደ ዞኑ እየገባ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አበባው፣ ለተፈናቃዮች በቂ እርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ለተፈናቃዮች አስፈላጊ የእርዳታ አቅርቦት ከፍተኛ ችግር አለ። በመንግሥት ነው የሚቀርበው። በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ ነው የቀረበው። እሱም ለአንድ ወር ብቻ የሚሆን ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ማኅበረሰቡ ነው እየመገበ ያለው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አበባው እንደሚሉት የእርዳታ ድርጅቶች የመጠለያ እና የምግብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የማስተባበር ሥራ እየሰሩ መሆኑን ነው።
“እንደ ሸራ ያሉ ጊዜያዊ መጠለያ ለማግኘት እያስተባበርን ነው። ቢሆንም ግን በጊዜው ባለመድረሱና በአሁኑ ወቅት ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ ተፈናቃዮች በዝናብ እና በብርድ ላይ ይገኛሉ” በማለት ያለውን ሁኔታ ገልጸውታል።
አቶ አበባው እንደሚሉት ለተፈናቃዮቹ ተገቢውን ድጋፍ ከዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ተቋም ማግኘት ያልተቻለው ቀደም ሲል ዞኑ እርዳታ ከሚሹ አካባቢዎች ውስጥ አለመካተቱ ነው።
“ለዚህም በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ድጋፍ ከሚሹ አካባቢዎች ውስጥ ዞኑ ባለመካተቱ ተፈናቃዮች ችግር ላይ ናቸው። ድርጅቱ ቢይዘው ኖሮ ጊዜውን ጠብቆ የምግብ እርዳታ ይቀርብ ነበር” ብለዋል።
የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ያለው ችግር አስከፊ ስለሆነ ከክልል መጠባበቂያ ላይ በቂ ባይሆንም ድጋፍ መደረጉንም ጨምረው ተናግረዋል።