በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚመረምረው የተመድ ኮሚሽን ድጋፍ እንዲሰጥ ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እና ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማጣራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለተቋቋመው ኮሚሽን፣ የመርማሪ ቡድን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ሂውማን ራይትስ ዋች ጠየቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ተፈጽሟል በሚል ሪፖርት ማውጣቷን የጠቀሰው ተቋሙ ይህም ለመርማሪ ቡድኑ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን ሊሄድ ይገባል ብሏል።
አሜሪካ ጥሰቶቹን በተመለከተ የደረሰችበትን ድምዳሜ ብታሳውቅም የመርማሪው ቡድኑ የሥራ ዘመን በመጪው መስከረም ሲጠናቀቅ ሊታደስ እንደማይችል መጠቆሟንም ነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በመጋቢት 13/2015 ዓ.ም. መግለጫው ያተተው።
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ መጋቢት 12/2015 ዓ.ም. በተካሄደው የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች አገራት የመርማሪ ኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሲያልቅ የማይታደስበት ሁኔታ እንዳለ መጠቆማቸውንም ነው ሂውማን ራይትስ ዋች ያሳወቀው።
ኢትዮጵያው ከምሥረታው ጀምሮ ፖለቲካዊ አካሄድ አለው፣ ሉዓላዊነትን ይጋፋል ስትል ስትቃወመው የነበረው የባለሙያዎች ቡድን ሥራው እንዲቋረጥ እየጠየቀች ትገኛለች።
በጦርነቱ ተፈጸሙ የተባሉ ጥሰቶችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋራ እንደመረመሩት በመግለጽም፣ የቡድኑ የሥራ ጊዜ መቋረጥ ይኖርበታል ብላለች።
ኢትዮጵያ እነዚህን ጥሰቶች ለመርመር እና ተጠያቂነት ለማስፈን የሽግግር ወቅት ፍትሕን እንደ አንድ አማራጭ አቅርባለች።
ሂውማን ራይትስ ዋች በበኩሉ የመርማሪ ኮሚሽኑ የሥራ ዘመን እንዲታደስ በማረጋገጥ ጥልቅ እና ገለልተኛ ምርመራዎች እንዲካሄዱ አሜሪካ ልትሰራ ይገባል ብሏል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ እርምጃዎችን በማበረታታት ተዓማኒት ያለው ምርመራ፣ ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባም ነው ሂውማን ራይትስ ዋች የጠየቀው።
“የአሜሪካ መንግሥት እነዚህን ጥሰቶች በስማቸው ጠርቷቸዋል” ያሉት የሂውማን ራይትስ ዋሽንግተን ዳይሬክተር ሳራ ያገር “ለደረሰው ከፍተኛ ሰቆቃ እና ስቃይ ይፋዊ ዕውቅና መስጠት ለተጎጂዎች በጣም አስፈላጊ ነው አሁን ደግሞ ፍትህን ይሻሉ” ብለዋል።
አሜሪካ በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን ከሰሞኑ አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር፣ የህወሓት ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ከጦር ወንጀሎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች ግድያዎችን፣ መድፈር እና አስገዳጅ ማፈናቀልን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአማራ ኃይሎች አባላት በምዕራብ ትግራይ አስገዳጅ ማፈናቀል እና የዘር ማጽዳት ወንጀል መፈጸማቸውንም ነው ብሊንከን ያሳወቁት።
በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት ብሊንከን “እነዚህ ወንጀሎች ብዙዎቹ በዘፈቀደ ወይም በጦርነት ውስጥ የተከሰቱ ሳይሆን ሆን ተብለው ታስበው የተፈጸሙ ናቸው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የደረሰበት ድምዳሜ አንድን ወገን ነጻ የሚያወጣ፣ ወገንተኛ፣ ጊዜውን ያልጠበቀ፣ ከፋፋይ እና አቀጣጣይ ነው ስትል ወቅሳለች።
ሆኖም የአሜሪካ ድምዳሜ ሁሉንም ጥሰቶች አላካተተም ብሏል ሂውማን ራይትስ ዋች።
በምሳሌነት የጠቀሰውም “በትግራይ ለ16 ወራት የዘለቀውን ከበባ ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግን በግልጽ የሚጥስ ቢሆንም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አልጠቀሰውም” ሲል ሂውማን ራይትስ ዋች ገልጿል።
የተመድ መርማሪ ኮሚሽን 19 ገጾችን የያዘው ሪፖርት የኢትዮጵያ ኃይሎች “ሆን ብለው ረሃብን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅመውበታል” ሲል ማውጣቱንም ነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የጠቀሰው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የመርማሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት ያልተቀበለው ሲሆን ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚለውንም ውድቅ አድርጎታል።
“የጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች የተፈጸሙ መጠነ ሰፊ ጥሰቶችን በሚክዱበት ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢዘገይም ይፋዊ ዕውቅና መስጠቱ ድምጻቸውን ለተነጠቁ ተጎጂዎች ተስፋ ይሰጣል እንዲሁም ጥሰቶቹን የፈጸሙትም አንድ ቀን ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው” ብሏል።
የመርማሪ ኮሚሽኑ ሥራ እንዲቋረጥ የሚጠቁሙ መግለጫዎች የተጠያቂነት ሂደት እንደሚያኮላሹም ተቋሙ ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጀምሮ ያሉ ዓለም አቀፍ ጥሰቶችን መመርመር፣ ተጠያቂዎችን መለየት፣ ማስረጃን መጠበቅ እና በተጠያቂነት እና በሸግግር ፍትህ ላይ መመሪያ መስጠት ዋነኛ ኃላፊነቱ እንደሆነም ተጠቅሷል።
አሜሪካም ሆነ ሌሎች ለጋሽ አገራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የሚያደርጓቸው የመረጃ ስብስብም ሆነ ማጣራት መርማሪ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ላይ እያካሄደ ያለውን ወሳኝ የምርመራ ሥራ የሚተካ አይደለም ብሏል።
አሜሪካ እና ሌሎች አገራት በትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍል ያለውን አሁናዊ ሂደት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እና የመብት ይዞታ ሁኔታዎችን በጥብቅ በመገምገም የመርማሪ ኮሚሽኑን የሥራ ዘመን እንዲራዘም ሊያረጋግጡ ይገባል ብሏል።
የመርማሪ ቡድኑ አባላት በተጨማሪም ጦርነቱ የተከተሰተባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን እንዲጎበኙና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩላቸው በፌደራል እና በክልል ባለሥልጣናት ላይ ግፊት ማድረግ አለባቸው ብሏል።
የተመድ መርማሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ
ባለፈው ዓመት 19 ገጾች ያሉትን የመጀመሪያ ግኝቱን አቅርቦ የነበረው ኮሚሽኑ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችንም ሆነ ሌሎች የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ገብቶ ምርመራ እንዲያካሂድ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም እንደተከለከለ ገልጿል።
በጄኔቫ በተካሄደው የተመድ የሰብዓዊ ምክር ቤቶች ላይ የመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሃመድ ቻንዴ ኦትማን በጦርነቱ ተፈፅመዋል የተባሉ ጥሰቶችን ምርመራ በርቀት እያካሄዱ እንደሆኑ ገልጸው፣ መንግሥት ከኮሚሽኑ ጋር ላለመተባበር ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደገና ሊያጤነው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥቱ ግጭት የማቆም ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፣ ከሰላም ስምምነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችን መመርመር አሁንም ቀዳሚ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት የደረሰበትን ሪፖረት ሲያቀርብ ለአምስት ወራት የዘለቀው የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሶ ጦርነቱ ባገረሸበት ወቅት ነበር።
በአሁኑ ወቅት በሰላም ስምምነቱ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እንደተሻሻለና ስምምነቱንም ሆነ አተገባበሩን በበጎ እንደሚያዩት ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱ የአገር ውስጥ የሽግግር የፍትህ ሂደት መጀመሩንም አስታውሰዋል።
የሽግግር የፍትህ ሂደቱን ለመገምገም ጊዜው ገና ቢሆንም አገራዊ ሂደቶች ሁሉን አቀፍ፣ ሥርዓተ ጾታን ያካተተ፣ ተጎጂዎችን እና ሰለባዎች ያማከለ ለተጠያቂነት፣ ለእርቅ እና ለእውነት እንዲሁም ድጋሚ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ፖሊሲዎችን ያወጣል የሚል ተስፋም እንዳሳደሩ ተናግረዋል።
“ሆኖም እነዚህ አዎንታዊ ለውጦች እና የተሻሻለ የፀጥታ ሁኔታ ቢኖርም ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶች ክብደት እና መጠነ ሰፊነት ሊዘነጋ አይገባም” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን በሪፖርቱ ያካተተ ሲሆን፣ እነዚህን ጥሰቶች ጨምሮ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ ደረሱ የተባሉትንም እየመረመረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ መደፈር፣ የሰብዓዊ እርዳታ ክልከላና ሌሎች ጥሰቶችን እየመረመረ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም በኤርትራ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉትንም እንደሚያካትት ተጠቅሷል። ሆኖም ምርመራውን በአገር ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ከልክሏኛል ብሏል።
ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አቶ ፀጋ አብ ክበበው በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት ላይ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ጦርነቱን አቁሟል፣ የሰብዓዊ እርዳታ እየገባ እንዲሁም የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችን መገንባት እና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታትን ጨምሮ ተግባራዊነቱን አስረድተዋል።
ስምምነቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የተጠያቂነት ፖሊሲ ማውጣትን ጨምሮ እርቅ እና እውነት ላይ መድረስ እንዲሁም ለተጎጂዎች ፍትህ ለማምጣት የሽግግር የፍትህ እርምጃዎችን ማውጣቱን ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመንግሥት ጥያቄ በሽግግር ፍትህ ላይ በአገር ደረጃ የሚደረጉ ምክክሮችን እየደገፉ ይገኛሉ ብለዋል።
“የሰላም ስምምነቱን የሚያናጉ አቀጣጣይ መረጃዎች ለኢትዮጵያ በተቋቋመው የመርማሪ ኮሚሽን እንዳይደገም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ለማጣራት እና ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም አለው ሲሉም ተናግረዋል።
በባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በመሰነድ ላይ እንደሆነ የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉን አቀፍ ተጎጂዎችን ያማከለ የሽግግር ፍትህ እንዲኖር በአግባቡ ተቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶችን እንዲደግፉ እና እንዲያስተባብሩ አሳስቧል።
ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ ምሥረታ ፖለቲካዊ ነው በማለት ስታቃወመው የቆየች ሲሆን፣ ከተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር የሚኖራትም ግንኙነት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለባት ስትል ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ከተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ተባብራ መሥራት መደገፍ እንጂ እጅ በመጠምዘዝ የሚደረግ የክትትል ዘዴ እንደማይሳካም ገልጻለች።
መርማሪ ኮሚሽኑ የተቋቋመው ከኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ውጪ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን ጉዳይ የበለጠ እንደሚያወሳስብ የቻይናው ተወካይ ተናግረዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መርማሪ ኮሚሽኑን ለማቋቋም ባለፈው ዓመት የውሳኔ ሃሳብ ባቀረበበት ወቅት፤ ቻይናን ጨምሮ 15 አገራት ተቃውመውት ነበር።












