ፖፕ ፍራንሲስ የሮማ ካቶሊክ ቄሶች ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ቡራኬ መስጠት ይችላሉ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሮማ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ ሰጡ።
ዜናው በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።
የሮማን ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን መሪ እንዳሉት የቤተ-ክርስትያኒቱ ቄሶች የተመሳሳይ ፆታ “ያልተለመዱ” ጥንዶችን በአንዳንድ ሁኔታዎች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቅጃለሁ ሲሉ ተሰምተዋል።
ነገር ግን ቫቲካን እንዳለው ይህ የሚሆነው በተለምዶ በቤተክርስትያኗ በሚካሄዱ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ አይደለም።
ቫቲካን አክሎ አሁንም ቢሆን ትዳር በአንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረግ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ነው የምናየው ብሏል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሰኞ ዕለት ነው አዲሱን የቫቲካን መመሪያ የሚያትቱ መዛግብትን ማፀድቃቸውን ያሳወቁት።
ቫቲካን፤ ይህ መልዕክት “ከፈጣሪ የተላከ እሱ ሁሉንም እንደሚቀበል የሚያሳይ ነው” ብሎ በመመሪያው መሠረት ቄሶች ሁኔታውን በዝግታ እያጤኑ እንደሚተገብሩት ጠቁሟል።
መመሪያውን ያስተዋወቁት ካርዲናል ቪክተር ማኑዌል ፈርናንዴዝ አዲሱ ትዕዛዝ “በቀደመው ባሕላዊ የቤተ-ክርስትያኒቱ የትዳር መመሪያ ላይ አሁንም ጥብቅ ነው” ብለዋል።
ካርዲናሉ አክለው ሊቀ ጳጳሱ ካለሳቸው የቤተ-ክርስትያኗን ተቀባይነትን “የማስፋት” ዓላማ ጋር በተያያዘ ቄሶች አሁን ለወትሮው ኃጥያት ተብለው የሚቆጠሩ ግንኙነቶችን መባረክ ይችላሉ ብለዋል።
አዲሱ መመሪያ እንደሚለው “ቡራኬ የሚቀበሉ ሰዎች ከዚህ ቀደም ፍፁም የሆነ ሞራል እንዲኖራቸው አይጠበቅም።”
በካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን መሠረት ቡራኬ ማለት ፀሎት አሊያም ተማፅኖ ሲሆን ቄሶች ፈጣሪ አንድን ግለሰብ አሊያም ሕዝብን እንዲያስብ የሚማፀኑበት ሥነ-ሥርዓት ነው።
አዲሱ መመሪያ ምንም እንኳ ቫቲካን ከዚህ ቀደም ካለው አተያይ ሲነፃፀር ላላ ያለ ቢሆንም አሁንም የቤተ-ክርስትያኗ አቋም እንዳልተቀየረ የሚያሳይ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2021 “ፈጣሪ ኃጥያትን ስለማይባርክ” ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ቄሶች አይባርኩም ብለው ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ጥቅምት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን መባረክ በተመለከተ ሐሳባቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር።
በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ሊቃነ-ጳጳሳት ከዚህ ቀደም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ቄሶች እንዲባርኩ ፈቃድ ሰጥተው ነበር።












