ፈረንሳይ በኒጀር ለሚገኘው ኤምባሲዋ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት ጠየቀች

 በኒጀር በፈረንሳይ ላይ የተካሄደው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደባት ኒጀር መዲና ኒያሚ የሚገኘው ኤምባሲ ደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መፈንቅለ መንግሥቱን ላካሄዱ አመራሮችም በመደወል የኤምባሲው ሙሉ ደህንነት እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

ፈረንሳይ ይህንን ጥያቄ ያቀረበችው በዛሬው ዕለት በመዲናዋ ሊታቀድ ከታሰበው ሰልፍ ስጋት ጋር በተያያዘ ነው።

ባለፈው ዕሁድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አደባባይ በወጡበት ተቃውሞ የፈረንሳይ ኤምባሲ ጥቃት ደርሶበታል ። የቀድሞዋ ቅዢ ገዢ ፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ በኒጀር አደባባዮች ሲቃጠል ታይቷል።

ይህንንም ተከትሎ ፈረንሳይ ዜጎቿን ከኒጀር እንድታስወጣም ተገድዳለች።

ኒጀር የፈረንሳይ የጦር ሰፈር መቀመጫ ስትሆን፣ በዓለምም ሰባተኛ የዩራኒየም ማዕድን አምራች አገር ናት።

የዩራኒየም ማዕድን ለኒውክሌር ኃይል በጣም አስፈላጊ ግብዓት ነው። ሩብ የሚሆነው ይህ የኒጀር ማዕድን ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ቀድሞዋ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ያቀናል።

የፕሬዚዳንቱ የክብር ዘብ መሪ የነበሩት ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ሥልጣንን በመፈንቅለ መንግሥት ከተቆጣጠሩ በኋላ በጎዳናዎች ላይ የሩሲያ ሰንደቅ አላማ መታየቱን ቀጥሏል።

በምዕራብ አፍሪካ የተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥቱን የሚደግፉ ተሟጋቾች በአገራቱ ውስጥ ያሉ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ወታደሮች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እየጠየቁ ይገኛሉ።

አሜሪካ በመዲናዋ በሚገኘው ኤምባሲዋ ውስጥ የአደጋ ጊዜ ያልሆኑ ሰራኞች በሙሉ እንዲወጡ ያዘዘች ሲሆን ዜጎቿም ወደ ኒጀር እንዳይሄዱ መክራለች።

በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተገረሰሱት ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አውሮፓውያኑ 1960 ነጻ ከወጣች በኋላ፣ የአገሪቷን መሪ እንዲተኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ ዴምክራሲያው ምርጫ በ2021 የተመረጡ መሪ ናቸው።