ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞቹን ፎቶ በቅርንጫፎቹ በር ላይ ይፋ ማድረግ ጀመረ
አጋጥሞት በነበረው የሲስተም ችግር ምክንያት በመቶ ሚሊዮኖች የመቆጠር ተወስዶበት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡን ያልመለሱ ሰዎችን ፎቶ እና መረጃ በትላልቅ ፖስተሮች ይፋ እያደረገ ነው።
ባለፉት ቀናት ገንዘቡን ያልመለሱ ሰዎችን በበይነ መረብ አማካይነት ያፋ ያደረገው ባንኩ አሁን ደግሞ በቅርንፎቹ አማካይነት የደንበኞቹን ስም እና ፎቶዎች በትልቅ ፖስተር በመለጠፍ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
ባንኩ ከተወሰደበት 800.1 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ የቻለ ሲሆን፣ አሁንም ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል የወሰዱትን ገንዘብ ያልመለሱ ሰዎች እንዳሉ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡን ያልመለሱለትን ደንበኞቹን ማንነት ይፋ እንደሚያደርግ እና በሕግም እንደሚጠይቃቸው ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ተፈጥሮ በነበረው ችግር፣ ደንበኞች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ወጪ ወይም ወደ ሌላ አስተላልፈዋል ሲል ማሳወቁ ይታወሳል።
ባንኩ ላይ ችግሩ በተከሰተበት ጊዜ ከፍተኛውን ገንዘብ መውሰዳቸው የተነገረላቸው በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማናሪዎች መሆናቸውም ተገልጾ ነበር።
ባንኩ ብሩ እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ ዝውውር የተደረገባቸውን የሂሳብ ቁጥሮች እንዳይንቀሳቀሱ አስከ ማድረግ የሚደርስ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል።
የወሰዱትን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ በሚመልሱ ደንበኞቹ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደማይወስድ የገለጸው ባንኩ፣ አብዛኛውን ብር ለማስመለስ ቢችልም አሁንም ያልመለሱ እንዳሉ አሳውቋል።
የራሳቸው ያለሆነ ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ ተመላሽ እንዲያደርጉ ያስጠነቀቀው ባንኩ፣ ባለፈው ሳምንት የግለሰቦቹን ስም ይፋ ካደረገ በኋላ በዚህ ሳምንት ደግሞ ምስላቸውን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች እንዲሰራጭ አድርጓል።
ክስተቱ ካጋጠመ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ደግሞ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ወስደዋል የተባሉትን ደንበኞቹን ስም እና ፎቶ ሂሳብ በከፈቱባቸው ቅርንጫፎች በር ላይ እና በሚገኙባቸው ስፍራዎች በጉልህ እንዲለጠፍ እያደረገ ነው።
መሐል አዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የባንኩ ቅድስት ማሪያም ቅርንጫፍ በር ላይ የተሰቀለው ትልቅ ፖስተር የ28 ሰዎች ስምና ፎቶን የያዘ ሲሆን፣ “ያለግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ ያላደረጉ” የሚል ጽሁፍ በጉልህ ሰፍሮበታል።
በተጨማሪም በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ በር ላይ የተማሪዎችን ፎቶ እና ስም ያያዙ ሰፋፊ ማስታወቂያዎች መለጠፋቸውን የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወሩ ነው።
ባለፈው ሳምንት ባንኩ የተለያየ መጠን ያለውን ብር ያለግባብ ወስደዋል ያላቸውን ደንበኞቹን ማንነት የሚገልጹ መረጃዎችን በድረ ገጹ ላይ በማውጣት ገንዘቡን እንዲመለልሱ ጥሪ እያቀረበ ነበር።
ባንኩ እስካሁን ገንዘቡን ለማስመለስ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተከትሎ ብሩን ሳይመለሱ የሚቀሩ ደንበኞቹን ጉዳይ ወደ ፖሊስ በመውሰድ ሕጋዊ መንገድን እንደሚከተል አስጠንቅቋል።
በአገሪቱ ትልቁ ባንክ እንዲሁም በአፍሪካ ካሉት ትልልቅ ባንኮች መካከል የሚመደበው ከ80 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች እንዳሉት ይነገራል።