የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በ96 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አምስተኛ ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ለአጭር ጊዜ ከታመሙ በኋላ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገለጸ።
የአዲ ቀይህ አገረ ስብከት ፓትሪያርክ የነበሩት ቀዳማዊ አቡነ ቄርሎስ፣ አምስተኛው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ሆነው የተቀቡት ከአንድ ዓመት በፊት ግንቦት 2013 ዓ.ም. ነበር።
የሲመት ሥነ ሥርዓታቸው አሥመራ ውስጥ በምትገኘው የቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመው አቡነ ቄርሎስ፣ ቤተክርስቲያኗን በመሩበት አንድ ዓመት ውስጥ ወደ ተለያዩ አገራት ተጉዘው ነበር።
ከአቡነ ቄርሎስ በፊት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሦስተኛው ፓትሪያርክ የነበሩት አቡነ እንጦኒዮስ አስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ቤተክርስቲያኒቱን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ ከሃይማኖቱ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ያራምዳሉ ተብለው ሲከሰሱ ነበር።
ከዚያም በኋላ የኤርትራ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ፓትሪያርኩን አውግዘው ከመንበራቸው በማንሳት የእምነቱ ተከታዮች “እውቅና እንዳይሰቷቸው እና ስማቸውንም እንዳያነሱ” አዘው ነበር።
በዚህም ሳቢያ ሦስተኛው ጳጳስ አቡነ እንጦኒዮስ ውግዘት ደርሶባቸው በቁም አስር በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ ያለ ተተኪ ጳጳስ ለረጅም ጊዜያት ቆይታለች።
አቡነ እንጦኒዮስ ለረጅም ጊዜ የአገሪቱ መንግሥትን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ለ15 ዓመታት ከመንበራቸው ተነስተው በቁም አስር ላይ መቆየታቸው ይነገራል።
ቤተክርስቲያኗ አሁን ያረፉትን አቡነ ቄርሎስን አዲስ ጳጳስ አድርጋ በቀባችበት ወቅት በወጣችው መግለጫ “የፓትሪያርክነት ሹመቱ የተከናወነው በቤተክርስቲያኗ እና በቅዱስ ሲኖዶሱ ሕግ እና ሥርዓት መሠረት” መሆኑን አመልክቷል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ ነጻ አገር መሆኗን ተከትሎ ላለፉት ከ30 ዓመታት በላይ የቆየ የእራሷን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁማ ፓትሪያርክ ስትሰይም አምስተኛው ጳጳስ ላይ ደርሳለች።
የአገሪቱ መንግሥት በመላው አገሪቱ ባሉ የእምነት ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ሃይማኖት በኤርትራ
ኤርትራ ውስጥ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ዋነኛ ከሚባሉት ሃይማኖቶች መካከል አንዷ ናት። በአገሪቱ ውስጥ በሕጋዊነት እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው የእምነት ተቋማት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የሉተራን ቤተክርስቲያን እና የሱኒ አስልምና ናቸው።
ኤርትራ የእምንት ነጻነትን በመገደብ በኩል በተደጋጋሚ ስትወቀስ የቆየች ሲሆን በዚህም በርካቶች ለእስር መዳረጋቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
የኤርትራ መንግሥት የጴንጤኮስታል እና የኢቫንጀሊካን እምነቶች የውጭ መንግሥታት መጠቀሚያ ናቸው በሚል ይከሳል።
ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን ኤርትራ በእምንት ነጻነት ላይ በምታደርሰው ጭቆና ምክንያት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በተለየ ሁኔታ እንዲመለከታት ጠይቆ ነበር።
ከ30 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች በኋላ ኤርትራ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባት አገር ሆና ቆይታለች።












