አንድ ለጋሽ ለአሜሪካ ወታደሮች ደሞዝ 130 ሚሊዮን ዶላር መስጠቱ ጥያቄ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፖለቲከኞች ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው የአሜሪካ መንግሥት ለሠራተኞቹ ደሞዝ መክፍል ባለመቻሉ በተፈጠረው ክፍተት አንድ ለጋሽ ለአሜሪካ ወታደሮች የሚከፈል 130 ሚሊዮን ዶላር መስጠቱ ጥያቄ አስነሳ።
ማንነቱ ያልተገለጸው ለጋሽ ለወታደሮች የሚከፈለውን 130 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታጎን በመስጠት መንግሥት ሥራ ባቆመበት ጊዜ እንዲከፈል መስጠቱ የሥነ ምግባር ጥያቄን አስነስቷል።
የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን የገንዘብ ሥጦታው መደረጉን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕም ልገሳው ለአገሪቱ ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሠራዊት አባላት ክፍያ የሚፈጠረውን ጉድለት የሚሸፍን ነው በማለት የለጋሹን ግለሰብ ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ለጋሹ የአሜሪካ ዜጋ መሆኑን እና "ትልቁ ደጋፊዬ ነው" በማለት ግልጽ ያልሆነ ፍንጭ ቅዳሜ ዕለት ሰጥተዋል።
የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች በገንዘብ አወጣጥ ላይ ከስምምነት መድረስ ባለመቻላቸው የአሜሪካ መንግሥት አገልግሎቶች ከተዘጉ ከሦስት ሳምንት በላይ ሆኗቸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ባላፈው ሳምንት ለአገሪቱ ወታደሮች የሚያስፈልገውን ክፍያ ከወታደራዊ ምርምር ወጪ ላይ 8 ቢሊዮን ዶላር በማዞር የፈጸመ ሲሆን፣ ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ በዚህ ወር ማብቂያ ላይ የሚያስፈልገው ክፍያ ከየት እንደሚመጣ ግልጽ አይደለም።
ከ25 ቀናት በላይ የቆየው የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት መዘጋት በአገሪቱ ታሪክ ካጋጠመው ተመሳሳይ ሁኔታ ረጅሙ ለመሆን ተቃርቧል።
የአሜሪካ መከላከያ አባላት ክፍያን ጉድለት ለመሙላት በሚል የተሰጠው ልገሳ ጥያቄ ቢያስነሳም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ግን ሥጦታው ሕግን የተከተለ መሆኑን በመጥቀስ ተከላክለዋል።
ባለፈው ሐሙስ የሥጦታ ገንዘቡ እንደሚሰጥ ጠቅሰው የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ለጋሹ "ማንነቱ እንዲገለጽ አይፈለግም" በማለት ግልጽ ከማድረግ ተቆጥበዋል።
ነገር ግን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የገንዘብ ሥጦታውን ያበረከተው ግለሰብ ከትራምፕ የገንዘብ ደጋፊዎች መካከል ዋነኛ የሆነው ቲሞቲ ሜሎን መሆኑን እንደደረሰበት ይፋ አድርጓል።
ፎርብስ እንደሚለው ባለፀጋው ቲሞቲ የባለ 15 ቢሊዮን ዶላር ባለሀብት የሆነው ቤተሰብ ወራሽ ሲሆን፣ በአሜሪካ የባቡር ኢንዱስትሪ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተሳታፊ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፈ ሲሆን ለትራምፕ ደጋፊ ቡድን 50 ሚሊዮን ዶላር መስጠቱ ተነግሯል።
ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ወደ እስያ አገራት ከማቅናታቸው በፊት ዋይት ሐውስ ውስጥ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ለጋሹን ግለሰብ "ታላቅ ሰው፣ ለጋሽ፣ አርበኛ" እና "ማንነቱ እንዲገለጽ የማይፈልግ ድንቅ ሰው" ሲሉ ገልጸውታል።
"እኔ ከመጣሁበት ዓለም በተለየ ሁኔታ ከልገሳው ጋር ስሙ እንዲገለጽ አልፈለገም" ያሉት ትራምፕ "በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ስምህ እንዲጠቀስ ትፈልጋለህ።"
ትራምፕ አክለውም "ሠራዊቱ ክፍያውን እንዲያገኝ 130 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል፤ ብዙ ገንዘብ ነው። የእኔም ትልቁ ደጋፊ ነው" ብለዋል።
ነገር ግን ተቺዎች የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማንነቱ ካልተገለጸ ምንጭ ለምን የገንዘብ ድጋፍ ይቀበላል በማለት ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው።
በአሜሪካ ምክር ቤት የመከላከያ ኮሚቴ ውስጥ አባል የሆኑት ዲሞክራቱ ክሪስ ኩንስ "ለሠራዊቱን ማንነቱ ካልተገለጸ ወገን የሚሰጥ ድጋፍ በውጭ ኃይሎች የተገዛ ወይም የሚከፈለው ያህል የሚረብሽ ጥያቄን ያስነሳል" በማለት በተሰጠው ልገሳ ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ አስተዳደር በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት ባለፈው ሳምንት ለመከላከያ ሠራዊቱ መክፈል የሚያስፈልገውን ገንዘብ መመደብ ሳይችል ቀርቷል። በሚቀጥለው ሳምንት ከየት አምጥቶ እንደሚከፍልም የታወቀ ነገር የለም።
የአሜሪካ ምክር ቤት ለአገሪቱ ወታደሮች እና ለሌሎችም የመንግሥት ሠራተኞች ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችለውን የበጀት ሕግ ተስማምቶ ማጽደቅ ባለመቻሉ ነው ክፍተቱ የተፈጠረው።
በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች ለጊዜው ሥራ እንዲያቆሙ ወይም አንዳንዶች ደግሞ የተዘጋው የመንግሥት በጀት እስኪለቀቅ ድረስ ያለ ክፍያ እንዲሠሩ ተነግሯቸዋል።
በአሜሪካ የመከለካከያ መሥሪያ ቤት መመሪያ መሠረት ከ10 ሺህ ዶላር በላይ የሚበረከቱ ሥጦታዎች ለሥነ ምግባር ባለሥልጣናት ቀርቦ ምንም ዓይነት የጥቅም ግጭት ወይም ፍላጎት አለመኖሩ ከመሰጠቱ በፊት መመርመር እና መረጋገጥ አለበት።
እንዲሁም የአሜሪካ ዜግነት ከሌላቸው ሰዎች የሚበረከቱ ሥጦታዎች ደግሞ ተጨማሪም ምርመራ ይደረግባቸዋል።
ምንም እንኳን የተለመደ ባይሆንም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር አንዳንድ ጊዜ ለትምህርት ቤት፣ ለሆስፒታል፣ ለቤተ መጽሐፍት፣ ለሙዚየም ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ሥጦታዎችን ይቀበላል።















