የሴት ልጃቸውን ገዳይ በኬንያ በመፈለግ 35 ዓመታትን ያሳለፉት አባት አረፉ

በኬንያ ህይወቷ የጠፋውን ልጃቸውን ገዳይ በመፈለግ 35 ዓመታትን ያሳለፉት አባት አረፉ።

የዱር እንስሳት ፎቶ አንሺ የሆነችው የ28 ዓመቷ ጁሊ ዋርድ አስከሬን በኬንያ ማሳይ ማራ በሚገኘው ፓርክ የተገኘው በአውሮፓውያኑ 1988 ነበር።

የእንግሊዝ ተወላጅ በሆነችው ጁሊ ግድያ እስካሁን የተከሰሰ ሰው የለም።

አባቷ ጆን ዋርድ ገዳይዋን ለመፈለግና ለመርመር በሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ 2 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ አውጥተዋል።

ባለቤታቸው ህይወቷ ያለፈው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

ቀሪዎቹ ልጆቻቸው ቦብ እና ቲም የአባታቸውን ተልዕኮ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በ89 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈው አባት እስከ ሁለት ሳምንታት በፊትም ድረስ የልጃቸውን ገዳይ መረጃ እየተከታተሉ እንደነበር ልጃቸው ቦብ ዋርድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከወንድሙ ጋር በመሆን የአባታቸውን ስራ እንደሚቀጥሉ የተናገረው ቦብ በጉዳዩ ላይ መጽሃፍ ለማሳተም እና ዘጋቢ ፊልምም ለመስራት ማቀዳቸውን አስረድቷል።

“አባታችን ላለፉት 35 ዓመታት ሲያደርግ የነበረውን ነገር ዓለም መረዳት ይችላል” ሲልም ቦብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በጣም የሚያስደንቅ ታሪክ እና በርካቶች የሚያውቁት ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲልም አክሏል።

ጁሊ ፎቶግራፍ ለማንሳት በፓርኩ ውስጥ ብቻዋን ከሄደች በኋላ ነው ደብዛዋ የጠፈው።

ለመጨረሻ ጊዜም በህይወት የታየችው በአውሮፓውያኑ መስከረም 6/ 1988 ዓ.ም ነበር።

ከሳምንት በኋላ የተቃጠለ እና የተቆራረጠው ሬሳዋ በአባቷ ተገኘ።

በወቅቱም የኬንያ ባለስልጣናት በእንስሳት ጥቃት ተፈጽሞባት እንደተገደለች ተናግረው ነበር።

በኋላ ግን አባትየው ተጨማሪ ማስረጃዎችን ማግኘታቸውን ተከትሎ በሰው እጅ መገደሏን ተቀበሉ።

በጁሊ ግድያ ሁለት የፓርኩ ጠባቂዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 1992 በቂ ማስረጃ ባለመኖሩ በነጻ ተለቀቁ።

የኬንያ ፖሊስ አዲስ ቡድንም ምርመራውን እንደገና በአውሮፓውያኑ 1997 ከፈተ።

ከሁለት ዓመት በኋላም የፓርክ ጠባቂ ቢወነጀልም በኋላ ነጻ ወጥቷል።

አባትየው ጆን ዋርድ የልጃቸውን ገዳይ ለመፈለግ ከ100 በላይ ወደ ኬንያ ጉዞ አድርገዋል።

ቀደም ሲል የልጃቸው ሞት አደጋ ቢሆን እንደሚቀበሉት ተናግረው ነገር ግን ተገድላ በመሆኑ በምርመራው ተስፋ አልቆርጥም ሲሉም ተናግረዋል።