የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት የሞተ ሰው ከሾሙ በኋላ ሁለት ረዳቶቻቸውን ከሥልጣን አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር በሚመጣው ታሥሣሥ ለሚደረገው ምርጫ ውይይት ለመምራት የሞተ ግለሰብ ከሾሙ በኋላ ሁለት ከፍተኛ ረዳቶቻቸውን ከሥልጣን አባረሩ።
ስቴዋርድ ሶሮባ ቡዲያ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በፕሬዝደንት ትዕዛዝ ቢሾሙም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተቃዋሚው ዩናይትድ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ዩዲፒ) አባል ከሞቱ አምስት ዓመት እንደሆናቸው ዘግበዋል።
ይህን ተከትሎ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ሁኔታውን ሲያብጠለጥሉ ተስተውለዋል።
የፕሬዝደንቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ዴቪድ አሞር እና የፕሬዝደንታዊ ጉዳዮች ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ቫሌንቲኖ ዴል ሙሌት ከሥልጣን መነሳታቸውን የሚገልፅ መግለጫ ቢለቀቅም የተባረሩበትን ምክንያት አይጠቅስም።
ኪር ሁለቱ ግለሰቦች ከሥልጣን መነሳታቸውን አስታውቀው ላበረከቱት አስተዋፅዖ "ታላቅ ምስጋና" አቅርበዋል ይላል በፕሬዝደንቱ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተለጠፈው መግለጫ።
ሰኞ ፕሬስ ሴክሬታሪው አሞር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፕሬዝደንቱ ቢሮ በፓኔል ውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ የመረጧቸውን ሰዎች የመረጡት "ተጣርተው ከቀረቡላቸው ሰዎች" መካከል ነው ብለዋል።
"አሁን እንደገባን ከሆነ ትክክለኛውን ማጣራት ሳናደርግ በማስረከባችን ይህ ያልታሰበ አስተዳደራዊ ችግር ተፈጥሯል" ብለዋል አሞር።
አሞር ሰዎችን የመረጡት እነማን እንደሆኑ ያላሳወቁ ሲሆን ዩዲፒ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።
ሰውዬው የለቀቁት መግለጫ ከሥልጣን እንዲወርዱ ምክንያት መሆኑ ግልፅ ባይሆንም ከመግለጫው በፊት ከሥልጣን ሊወርዱ እንደሚችሉ ሲነገር ነበር።
ሟቹ ቡዲያ ደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ 2011 ነፃ ሀገርነቷን ካወጀች በኋላ በሀገሪቱ የተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት እንዲቆም በ2018 ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል።
ፕሬዝደንት ኪር ለሚመጣው ምርጫ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በሚል ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሰዎች የተካተቱበት የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል።
ነገር ግን በሚመጣው ታኅሣሥ ይደረጋል የተባለው ምርጫ በሀገሪቱ አሁንም ባለው ግጭት ምክንያት እንዳይራዘም ስጋት አለ።
ከዚህ ቀደም ይካሄዳሉ ተብለው የተጠበቁ ምርጫዎች የተሰረዙ ሲሆን ሳልቫ ኪር ከነፃነት በኋላ ደቡብ ሱዳንን ያስተዳደሩ ብቸኛው መሪ እንደሆኑ ቀጥለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ በተነሱ ግጭቶች ምክንያት 180 ሺህ ገደማ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተፈናቀሉ ይገልጻል።
በተለይ ከሥልጣን በታገዱት ምክትል ፕሬዝደንቱ ሪዬክ ማቻር የሚደገፈው ታጣቂ ቡድን በሚገኝባት ጆንግሌይ ግዛት በርካታ ጥፋት እንደተፈፀመ ይነገራል።
ማቻር በአሁኑ ወቅት በቁም እስር ላይ ያሉ ሲሆን በግድያ፣ በሀገር ክህደት እና ሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ተከሰው ፍርዳቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በ2018 የተፈረመው የአዲስ አበባው የሰላም ስምምነት ኪር እና ማቻር ጥምር ፓርቲ መሥርተው መንግሥት እንዲያቋቁሙ ይመክራል።















