የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣን ላይ እንደሚቆዩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጃፓን ገዢ ጥምረት በሀገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት የነበረውን አብላጫ ድምጽ ቢያጣም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ ከስልጣን ለመልቀቅ ምንም እቅድ እንደሌላቸው ተናገሩ።
እሁድ ዕለት ዜጎች ጠንካራ ፉክክር ለታየበት ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አምርተዋል። ይህ ምርጫ የተካሄደው በዋጋ ንረት እና በአሜሪካ ታሪፍ ስጋት ምክንያት በሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና አጋሩ በሆነው ኮሜቶ ፓርቲ ላይ ቅሬታዎች እየተሰሙ ባሉበት ጊዜ ላይ ነው።
የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር እሁድ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ካበቃ በኋላ ባደረጉት ንግግር ይህንን "አስከፊ ውጤቱን"፤ "በማክበር" እንደሚቀበሉት ገልጸው፤ ነገር ግን ትኩረታቸው የንግድ ድርድር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥምረቱ፤ ባለፈው ዓመት በጃፓን ከፍተኛ ስልጣን ባለው የታችኛው ምክር ቤት ውስጥ አብዛኛውን ድምጽ ያጣ ሲሆን ይህ ሽንፈት ያለውን ተጽዕኖ ያዳክማል።
ገዢው ጥምረት፤ 248 መቀመጫዎች ባሉት የላይኛው ምክር ቤት አብዛኛውን ወንበር መቆጣጠር እንዲችል 50 መቀመጫዎች ያስፈልጉት ነበር።
አሁን በተጠናቀቀው ምርጫ ጥምረቱ ማግኘት የቻለው ግን 47 መቀመጫዎችን ብቻ ነው።
ዋነኛው ተቃዋሚ ኮንስቲትዩሽናል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ 22 መቀመጫዎችን በመያዝ ሁለተኛ ሆኗል።
ባለፈው እሁድ በተካሄደው ምርጫ የላይኛው ምክር ቤት ካሉት መቀመጫዎች ውስጥ ግማሾቹ ላይ ድምጽ የተሰጠ ሲሆን ተመራጮቹም ለስድስት ዓመት ያገለግላሉ።
በካናዳ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የጃፓን ጥናቶች መምህር የሆኑት ጄፍሪ ሀል ለቢቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት፤ ለተጨማሪ የቀኝ ክንፍ ፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ የሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በወግ አጥባቂዎች ዘንድ ያለውን የድጋፍ መሰረት አሳስቷል።
"የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር [ሺንዞ] አቤ ደጋፊዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሺባ በበቂ ደረጃ ወግ አጥባቂ እንዳልሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸዋል" ብለዋል።
"በታሪክ ላይ ብሄራዊ አመለካከት እንደሌላቸው፣ እንደ አቤ በቻይና ላይ ጠንካራ አመለካከት እንደሌለው ያስባሉ" ሲሉም አክለዋል።
ከዚህ ቀደም የፓርቲው መሪ የነበሩት ሺንዞ አቤ፤ እ.አ.አ ከ2006 እስከ 2007 እና ከ2012 እስከ 2020 ድረስ ሁለት ጊዜ ስልጣን በማግኘት ጃፓንን ለረጅም ጊዜ የመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሀል የተወሰነው የፓርቲው ድጋፍ "ከዚህ በፊት በላይኛው ምክር ቤት አባላት በይፋ የማይነገሩ" ነገሮችን ወደሚያነሳው ሳንሴቶ ፓርቲ እንደሄደ ያስረዳሉ።
ሳንሴቶ ፓርቲ፤ "ሴራ ትንተና፣ ፀረ ባዕዳን መግለጫዎች፣ [ እና] በጣም ጠንካራ የታሪክ ክለሳ አመለካከቶች" ማተኮሩን ይናገራሉ።
መካከለኛ ቀኝ ዘመም የሆነው የአሺባ ፓርቲ፤ ከ1955 ጀምሮ በተደጋጋሚ የአመራር ለውጥ እያደረገ ጃፓንን ያለማቋረጥ አስተዳድሯል።
የአሁኑ ምርጫ ውጤት መራጮች፤ በኢኮኖሚ መዳከም፣ በኑሮ ውድነት ቀውስ እና ከአሜሪካ ጋር ባለው የንግድ ድርድር ውስጥ ሆነው የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት ሲጥሩ በነበሩት ኢሺባ ላይ የተፈጠረባቸውን ብስጭት አጉልቶ ያሳያል።
ብዙዎች፤ በተለይም የሩዝ ዋጋ እንዲንር ባደረገው በዋጋ ግሽበት እንዲሁም የሊቢራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በገባባቸው ተከታታይ የፖለቲካ ቅሌቶች ደስተኛ አይደሉም።
በላይኛው ምክር ቤት ከፍተኛውን ድምጽ ማግኘት ያልቻሉት ያለፉት ሶስት የፓርቲው መሪዎች በሁለት ወራት ውስጥ ስልጣናቸውን ለቅቀዋል።
ፓርቲው በዚህ ምርጫ ያስተናገደው ሽንፈትም ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያስከትል ተንታኞች ግምታቸውን ገምተዋል።
ይህም ሌሎች ታዋቂ የፓርቲው አባላት ለምርጫ እንዲወዳደሩ እድል ሊከፍት ይችላል።
ይህንን እድል ያገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአመራር ምርጫ ከኢሺባ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ያገኙት ሳናይ ታካይቺን ይገኙበታል።
የቀድሞው የኢኮኖሚ ደህንነት ሚኒስትር ታካዩኪ ኮባያሺ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጁኒቺሮ ኮይዙሚ ልጅ ሺንጂሮ ኮይዙሚም ተጠቃሽ ናቸው።












