እንግሊዝ በዓለማችን የመጀመርያ ነው የተባለውን የጨብጥ መከላከያ ክትባት ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝ በወሲባዊ ግንኙነት የሚተላለፈውን ጨብጥ መከላከል የሚያስችል ክትባት በመስጠት በዓለም ላይ የመጀመርያዋ አገር ልትሆን ነው።
ክትባቱ ለሁሉም ተደራሽ እንደማይሆን ተገልጿል።
ክትባቱ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያን እና ከሁለቱም ጾታ ጋር የወሲብ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደረግ ተገልጿል።
ክትባቱ ከ30 እስከ 40 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለ ሲሆን የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት እየጨመረ የመጣውን የጨብጥ ሕሙማን ቁጥር ይቀንሳል ብሎ ተስፋ ጥሎበታል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ከ85 ሺህ በላይ ሰዎች በጨብጥ መያዛቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም ከ1918 ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ጨብጥ ብዙ ጊዜ ምልክቶችን የማያሳይ ሲሆን ነገር ግን ሕመም፣ ያልተለመደ ፈሳሽ፣ የመራብያ አካል አካባቢ ማቃጠል እና መውለድ አለመቻልን ያስከትላል።
እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ክትባቱን ይወስዳሉ የሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
ነገር ግን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን በሰራው ግምት ክትባቱ ተቀባይነት ካገኘ የ100 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የሚታደግ ሲሆን የብሔራዊ ጤና አገልግሎትንም በሚቀጥሉት አስርታት 8 ሚሊዮን ፓውንድ ማዳን ይችላል።
የስነ ተዋልዶ ጤና ለሁሉም እንዲዳረስ የሚወተውተው ማክስ ለቢቢሲ ኒውስ ቢት እንደተናገረው "በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ በጨብጥ መያዜን በምርመራ ማረጋገጤን ተከትሎ ክትባቱን ለመውሰድ መቶ በመቶ ዝግጁ ነኝ" ብሏል።
"ይህ ነገር እንደሚጀመር መገለፁ በጣም ትልቅ ነገር ነው" ካለ በኋላ፣ "በክሊኒኮች ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል፥ በሁሉም ረገድ ትልቅ ድል ነው" ብሏል።
ክትባቱ በነሐሴ ወር በስለ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አቅራቢዎች በኩል መሰጠት ይጀምራል ተብሏል።
የስኮትላንድ የማኅበረሰብ ጤና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ግለሰቦች የራሱን ፕሮግራም ለመጀመር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ቢቢሲ ኒውስ ቢት በዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ የሚገኙ የጤና አገልግሎት አቅራቢዎች ተመሳሳይ ዕቅድ ካላቸው በሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ክትባቱ ለጨብጥ የተሰራ አይደለም። ክትባቱ በአሁኑ ወቅት ለሕጻናት እየተሰጠ ያለው የመንጋጋ ቆልፍ ቢ ክትባት ነው።
ነገር ግን ሁለቱን ሕመሞች የሚያስከትሉት ባክቴርያዎች ተመሳሳይ በመሆናቸው የመንጋጋ ቆልፍ ቢ ክትባት የጨብጥ ኢንፌክሽንን በአንድ ሦስተኛ ይቀንሳል።
ክትባቱ በጨብጥ መያዝን ስለማያስቀር ከስነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒኮች ጋር ጥንቃቄ የተሞላበት ንግግር ማድረግ ይጠይቃል።
ጨብጥ ከኮንዶም ውጪ በሚደረግ የወሲባዊ ግንኙነት ወቅት የሚተላለፍ ነው።
ክትባቱ እንዲሰጥ ሃሳብ ያቀረቡት ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ ምንም እንኳ 30 በመቶ ብቻ ውጤታማ ቢሆንም "መውሰድ የተሻለ ሲሆን" እንደ አጠቃላይም "ትልቅ አስተዋጽኦ" ይኖረዋል ብለዋል።
ውሳኔው የመጣው ከፍተኛ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ብቻ አይደለም። ጨብጥ ለማከም አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ በሽታ መሆኑንም ነው።
አብዛኛዎቹ የጨብጥ ሕሙማን ፀረ ባክቴርያ በመውሰድ ቢድኑም ባለፉት 80 ዓመታት ጨብጥን የሚያስከትለው ባክቴርያ በተደጋጋሚ መድሃኒትን የመቋቋም ችሎታ እያዳበረ መምጣቱ ታይቷል።
አሁን ለመስጠት ለታሰበው ክትባትም ባክቴርያው የመቋቋም ችሎታ እንዳለው በመታወቁ የተወሰኑ የሕክምና ባለሙያዎች ጨብጥ በአንድ ወቅት መታከም የማይችል ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።












