በኢራን አዲስ ተቃውሞ መቀስቀሱን እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመለከቱ

በምዕራባዊ ኢራን ተቃውሞ እንደ አዲስ እንደተቀሰቀሰ የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' አረጋገጠ።
በዚህም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ በምዕራብ ኢራን የተቀረጹ ሁለት ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ተችሏል።
አብዳናን በተባለች ከተማ ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ. ም. የተቀረጹት እና ምሽት ላይ የተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በተወሰነ መጠን ተቃውሞ በድጋሚ መነሳቱን ይጠቁማሉ።
የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' በይፋ የሚገኙ የመረጃ ክምችቶችን፣ የሳተላይት ምሥሎችን እንዲሁም መረጃዎችን መተንተን እና ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው መንገዶችን ይከተላል።
በዚህ መንገድ ፍተሻ የተደረገባቸው የኢራን ተንቀሳቃሽ ምሥሎች አዲስ መሆናቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።
ከሳምንታት በፊት በኢራን በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ የአገሪቱ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከ6,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።
ኢራናውያን የተገደሉባቸውን ወዳጅ ዘመዶች ሐዘን በተወጡ በ40 ቀናት ውስጥ አዲስ ተቃውሞ መነሳቱን ከተንቀሳቃሽ ምሥሎቹ ለመረዳት ተችሏል።
'ቢቢሲ ቬሪፋይ' የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በኢራን አቅራቢያ እንደሚገኝ በሳተላይት ምሥል ማረጋገጡ ይታወሳል።
ከሦስት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ መድረሱ ከተዘገበ በኋላ ቢቢሲ ባለፈው እሑድ በተነሳ የሳተላይት ምሥል አማካኝነት መርከቡ የት እንደሚገኝ አረጋግጧል። መርከቡ እስከ እሑድ ድረስ ከሳተላይት ዕይታ ውጪ ሆኖ ቆይቶ ነበር።
በብዛት የመርከቦችን ቦታ ለመለየት ከሚውለው እና ዩሮፒያን ሴንቲኔል-2 ከተባለው ለሕዝብ ይፋ ከሆነውን ሳተላይት የተገኘ ምሥልን በመጠቀም ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት፤ አብረሃም ሊንከን የጦር መርከብ ከኢራን አቅራቢያ ከኦማን የባሕር ዳርቻ 240 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንዳለ አረጋግጧል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጄራርድ ፎርድ የተባለው ሁለተኛ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ አብረሃም ሊንከንን በመቀላቀል ከሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎች ጋር ወደ ቀጣናው መሰማራታቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምዕራብ ኢራን የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ተቃውሞው እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው በኢላም ግዛት፣ አብዳናን በተባለች ከተማ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
አካባቢው በኢራቅ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን፤ ወደ 100 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች መገኘታቸው ታውቋል።
ተቃዋሚዎቹ በከተማው ዋነኛ አደባባይ አቅራቢያ "ሞት ለኻሜኒ" ሲሉ ተደምጠዋል።
በምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት ምክንያት የተነሳው የኢራን ተቃውሞ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከሥልጣን ይውረዱ ወደሚለው ከተሸጋገረ በኋላ ቀጣናዊ ውጥረት ነግሧል።
ተቃውሞው የተነሳበት አካባቢ ኢስት ቫሊ አስር እና ሻህዲድ ሞታህሪ በሚባሎ ጎዳናዎች መካከል እንደሆነ ቢቢሲ አረጋግጧል።
ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ የተለጠፈው ቀን ትናንት ሰኞ መሆኑን ያሳያል። የምሥሉን 'ስክሪንሾት' በማየት ማወቅ የተቻለው ቪድዮው ከዚያ ቀን በፊት ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉ ነው።
ምሥሉ ላይ የሚታየው የአየር ሁኔታ ከአገሪቱ ይፋዊ የሆነ ደረቅ የአየር ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።
'ቢቢሲ ቬሪፋይ' ባጣራው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ ተቃዋሚዎች ፀረ መንግሥት መፈክር ሲያሰሙ በአጠገባቸው የሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ጡሩምባ ሲያደርጉ ይታያል።
ከኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በአገሪቱ ላይ ሊቃጣ የሚችል ወደታራዊ ጥቃትን ለመከላከል ያለውን ዝግጁነት ለመፈተሽ ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ ልምምድ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።
ኢራን እና አሜሪካ የመጀመሪያ ዙር ውይይታቸውን አጠናቀው ወደ ሁለተኛው አምርተዋል።
ኢራን፤ አሜሪካ የጣለችባትን ማዕቀቦች ለማንሳት ፈቃደኛ ከሆነች፤ ከአቋሟ ፈቀቅ ብላ የኒውክሌር ስምምነት ላይ የመድረስ ሐሳብን ለማጤን ዝግጁ መሆኗን ቴህራን ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ ታክት ራቫንቺ ከቀናት በፊት ገልጸዋል።
በቀጣናው ያላቸውን ወታደራዊ ኃይል እያጠናከሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለመግታት የሚያስችል ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ ቴህራን ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።
የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በበኩላቸው "የዓለም ኃያሉ ሠራዊት መልሶ እንዳይነሳ ሆኖ ሊመታ እንደሚችል" በመግለጽ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።















