ኢራን የኒውክሌር ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲባል ከአቋሟ ፈቀቅ ብላ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ ታክት ራቫንቺ
የምስሉ መግለጫ, የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ ታክት ራቫንቺ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢራን፤ አሜሪካ የጣለችባትን ማዕቀቦች ለማንሳት ፈቃደኛ ከሆነች፤ ከአቋሟ ፈቀቅ ብላ የኒውክሌር ስምምነት ላይ የመድረስ ሐሳብን ለማጤን ዝግጁ መሆኗን አንድ የኢራን ሚኒስትር ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ቴህራን እና ዋሽንግተን የሚያደርጉት ድርድር ለመጓተቱ ተጠያቂዋ ኢራን እንጂ አሜሪካ እንዳልሆነች በተደጋጋሚ በአጽንኦት ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ላይ መድረስን እንደሚመርጡ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከኢራን ጋር መስማማት "ለመፈጸም እጅግ አስቸጋሪ ነገር" እንደሆነ በማንሳት ወቅሰዋል።

ቴህራን ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ ታክት ራቫንቺ ግን ኳሱ "አሜሪካ ሜዳ ላይ" ነው ብለዋል። ይህም "ስምምነት መፈጸም እንደሚፈልጉ የማረጋገጥ" ኃላፊነትን እንደሚጥልባቸው ተናግረዋል።

"ቅን ከሆኑ፤ ወደ ስምምነት የሚያደርሰውን መንገድ እንደምንወስድ እርግጠኛ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።

በቀጣናው ያላቸውን ወታደራዊ ኃይል እያጠናከሩ ያሉት ትራምፕ፤ የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለመግታት የሚያስችል ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ ቴህራን ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ባለፈው ወር በመላው ኢራን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ከተካሄደ በኋላ ነው። የአገሪቱ መንግሥት ተቃውሞውን ለማፈን በወሰደው እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች ገልጸዋል።

አሜሪካ እና ኢራን ከሳምንት በፊት በባሕረ ሰላጤዋ አገር ኦማን ውስጥ ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር አድርገዋል። የዚህ ድርድር ሁለተኛ ዙር በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ጄኔቫ ውስጥ እንደሚካሄድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ንግግሩ "ከሞላ ጎደል በአዎንታዊ አቅጣጫ እየተጓዘ ነው፤ ለመደምደም ግን ገና ነው" ብለዋል። በዚህ ድርድር ቴህራን አቋሟን እንደምታስተካክል ማረጋገጫ ለመስጠት ስትል 60% የበለጸገውን ዩራኒየሟን ጥራት ለመቀነስ ሐሳብ ማቅረቧን ጠቁመዋል።

የኢራን ዩራኒየም አሁን ያለበት የጥራት ደረጃ ወደ ጦር መሣሪያነት ለመቀየር የቀረበ መሆኑ፤ የአገሪቱ መንግሥት የኒውክሌር መሣሪያ ወደ ማምረት እያመራ ነው የሚለው ጥርጣሬ እንዲጠናከር አድርጓል። ኢራን ግን ይህንን ውንጀላ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ "ስለ ማዕቀቦቹ ለመነጋገር ዝግጁ ከሆኑ እኛም ይህንን እና [ከኒውክሌር] ፕሮግራማችን ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ ነን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ኢራን ይህንን የምታደርገው ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ ሲነሱ ነው ወይስ በከፊል የሚለውን ግን በግልጽ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ኢራን በአውሮፓውያኑ 2015 በተፈጸመው የኒውክሌር ስምምነት ወቅት እንዳደረገችው ሁሉ፤ አሁንም ከ400 ኪሎ ግራም በላይ የሆነውን በከፍተኛ የደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም ክምችቷን ወደ ሌላ አገር ለማጓጓዝ ትስማማ እንደሆነ ለታክት ራቫንቺ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ "በድርድሩ ሂደት ምን እንደሚፈጠር ለመናገር ጊዜው ገና ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከአሥር ዓመት በፊት በተፈጸመው ባለ ብዙ ወገን ስምምነት አማካኝነት ኢራን 11,000 ኪሎ ግራም ያህል ብዛት ያለውን በዝቅተኛ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም ወደ ሩሲያ ልካ ነበር። ይሁን እንጂ ድርድሩ ከተፈጸመ ከሦስት ዓመት በኋላ ትራምፕ አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጥተዋል።

ሩሲያ አሁንም ከኢራን የሚመጣ የበለጸገ ዩራኒየምን ለመቀበል ጥያቄ አቅርባለች።

ከዚህ ቀደም የወጡ ዘገባዎች፤ ቴህራን የኒውክሌር ማበልጸግ ተግባሯን በጊዜያዊነት ለማገድ ጥያቄ እንዳቀረበች ጠቁመዋል። ትራምፕም አርብ ዕለት በሰጡት አስተያየት "ምንም አይነት [ዩራኒየም] የማበልጸግ ተግባር አንፈልግም" ብለው ነበር።

ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታክት ራቫንቺ ግን ዩራኒየም "የማበልጸግ ጉዳይን ዜሮ ላይ ማድረግ የሚለው አሁን አጀንዳ አይደለም። እኛን እስከጠየቃችሁን ድረስ ጉዳዩ አሁን ጠረጴዛው ላይ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።