የአሪታ ፍራንክሊን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ኑዛዜ ሶፋ ውስጥ ተገኘ

አሪታ ፍራንክሊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሶል ሙዚቃ ንግሥት አሪታ ፍራንክሊን በ2018 ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረቷን በተመለከተ ያስቀመጠችው ኑዛዜ እንዳልነበር ነበር የታሰበው።

ከወራት በኋላ ግን ሃብቷን የተናዘዘችበት ወረቀት ሚቺጋን በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ መደርደሪያ ውስጥ እና ከሶፋ ሥር ተደብቆ ተገኝቷል።

የትኛው ወረቀት ትክክለኛ ነው የሚለው ፍርድ ቤት እንዲወስነው ልጆቿ ጉዳዩን ለፍርድ አቅርበውታል። የፍርድ ሂደቱ ትናንት [ሰኞ] የተጀመረ ሲሆን ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በስድስት ዳኞች የተሰየመው ፍርድ ቤቱ ቤተሰቦቿን፣ ልጆቿን፣ እና የእጅ ጽሁፍ ሙያተኛን ያካተተ ምስክርነት ይሰማል።

የ18 ጊዜ የግራሚ አዋርድ አሸናፊዋ ፍራንክሊን በርካታ የስኬት ዘመናትን አሳልፋለች። ለዓመታት የዘለቀ ሕመም ቢኖርባትም በበግልጽ የሚታወቅ ኑዛዜ ሳትፈጽም ቆይታለች።

በ76 ዓመቷ ያለምንም ኑዛዜ ሕይወቷ ሲያልፍ፣ የነበረው እሳቤ አራቱ ልጆቿ ሃብቷን እኩል እንደሚካፈሉ ነው። ነገር ግን ከሞተች ከዘጠኝ ወር በኋላ በእጇ የተጻፈ ኑዛዜ ተገኘ።

አንደኛው ልጇ ትክክለኛው ኑዛዜ በ2010 የተጻፈው እና መደርደሪያ ውስጥ ተቆልፎ የነበረው ነው የሚል ኑዛዜ ይዞ መጣ።

በሌላ በኩል ሁለቱ ልጆቿ ደግሞ በ2014 የተጻፈው እና ሶፋ ውስጥ ተደብቆ የነበረው ኑዛዜ ትክክለኛ መሆኑን ተናገሩ።

ሰኞ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ዳኛዋ “የ2014ቱ ኑዛዜ ትክክለኛ ስለመሆኑ ብቻ ነው የምንወስነው” ብለዋል።

ሁለቱም ኑዛዜዎች በሃብት አከፋፈል ዙሪያ ልዩነት ቢኖራቸውም ልጆቹ በእናታቸው ሙዚቃ እና ኮፒራይት ላይ መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

የአሪታ ሦስተኛ ልጅ የሆነው ቴዎዶር ዋይት ትክክለኛው ኑዛዜ በ2010 የተጻፈው ነው ይላል። ያ ኑዛዜ እርሱ የግል ወኪሏ እንደሆነ የሚያትትበት ነው። በእዚህ ኑዛዜ መሰረት እርሱ እና ልጆቹ የ1.2 ሚሊዮን ዶላር ቤት ይወርሳሉ።

በሌላ በኩል ሁለተኛና አራተኛ ልጆች ደግሞ ትክክለኛው እና የእናታቸው የመጨረሻ ኑዛዜ የ2014 ኑዛዜ ነው ይላሉ።

ትልቁ ልጇ ክላረንስ ፍራንክሊን ውዝግቡ ውስጥ ከመግባት ተቆጥቧል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ሚችጋን ፍርድ ቤት ሦሰት የድምሥ ቅጅዎች ደርሰውታል።

ፍራንክሊን ከመሞቷ ከወራት በፊት በተደረገው የድምጽ ቅጅ፣ ከሕግ ባለሙያ ጋር በመነገጋገር አዲስ የኑዛዜ ሰነድ ለማዘጋጀት እየሰራች መሆኑን ይገልጻል።

ቢሆንም ግን ፍርድ ቤቱ ይህንን ሰነድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

አሪታ ስትሞት አጠቃላይ ሃብቷ 80 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር። ነገር ግን ብዙ ያልተከፈሉ የታክስ እዳዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመጨመራቸው የገንዘብ መጠኑ ቀንሶ ሊሆን ይችላል።

ፍርድ ቤቱ ጋ የደረሰው እና ቢቢሲ የተመለከተው መረጃ እንደሚያሳየው የድምጻዊቷ አጠቃላይ ሃብት በአሁኑ ወቅት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በታች ወርዷል።