በሞዛምቢክ ጀልባ ሰጥማ አብዛኞቹ ሕጻናት የሆኑ 90 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ሞዛምቢክ የመጓጓዣ አገልግሎት እየሰጠች የነበረች ጀልባ ሰጥማ አብዛኞቹ ሕጻናት የሆኑ ቢያንስ የ90 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
አደጋው ያጋጠመባት የናምፑላ ግዛት ኃላፊዎች በመርከቧ ተሳፍረው ከነበሩት 130 ሰዎች እስካሁን በሕይወት የተገኙ ሰዎች አምስት ናቸው ብለዋል።
የናፑላ ግዛት ዋና ፀሐፊ ጄይሚ ኔቶ ተጓዦቹ አደጋው የገጠማቸው በአካባቢያቸው የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ሲሸሹ ነው ብለዋል።
ኔቶ “ጀልባዋ ከአቅሟ በላይ በመጫኗ እንዲሁም ሰዎችን ለማጓጓዝ የተሠራች ባለመሆኗ ሰጥማለች” ብለዋል።
ቢቢሲ ማረጋገጥ ያልቻለው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተጋራ ተንቀሳቃሽ ምስል በጀልባዋ መስመጥ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ናቸው የተባሉ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ከባሕር ዳርቻ ጎን ተደርድሮ ያሳያል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ካረጋገጡት የ90 ሰዎች ሞት በተጨማሪ የደረሱበት ያልታቁ ሰዎች ከ30 በላይ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩት ተጓዦች በናምፑላ ግዛት በምትገኘው ሉንጋ የተቀሰቀሰውን ወረርሽኝ በመሸሽ ወደ ሞዛምቢክ ደሴት እየተጓዙ ነበር።
ናምፑላ ግዛት በተደጋጋሚ የኮሌራ በሽታ የሚቀሰቀስባት ግዛት ነች።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ከ25 ዓመታት ወዲህ የከፋው ነው ብሏል።
ሞዛምቢክ እስካሁን 13ሺህ 700 በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 30 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን እንቅስቃሴ ምክንያት በሞዛምቢክ የበርካታ ንጹሐን ሕይወት እያለፈ ነው።
የናምፑላ ጎረቤት በሆነችው ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ባለፉት ስድስት ዓመታት በጽንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ቢያንስ የ4 ሺህ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ደግሞ ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።
ለ400 ዓመታት ያህል በፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ስር የቆየችው ሞዛምቢክ ደሴት በቅኝ ግዛት ወቅት በተገነቡ ሥነ ሕንጻዎች እና ታሪካዊ ቅርሶች የዓለም ቅርስ ተደርጋ ተመዝግባለች።












