ኢትዮጵያ "ሶማሊላንድ ያወጣችውን መግለጫ እንደምትቀበል" የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አመለከቱ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

የፎቶው ባለመብት, ETH mfa

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

ራስ ገዟ ሶማሊላንድ እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን “ዓለማ አቀፋዊ ዕውቅና” ከኢትዮጵያ ለማግኘት ከስምምነት ላይ መድረሷን በመግለጽ ያወጣችውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አስታወቁ።

አምባሳደር ምስጋኑ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "የሶማሊላንድን መግለጫ እንቀበላለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለወታደራዊ እና ለባሕር ንግድ አገልግሎት የሚውል የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር መድረሷን ያስታወቀችው ሰኞ ታህሳስ 23፤ 2016 ዓ.ም. ነበር።

በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ይህንን የተመለከተ የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈራረሙ በሁለቱ መንግሥታት ይፋ ተደርጓል።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳዮች እና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የሰጠውን መገለጫ በቲውተር ገጻቸው ያጋሩት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ከመግለጫው ጋር ባያያዙት መልዕክት “በሱማሌላንድ መንግሥት የተሰጠውን መግለጫ እንቀበላለን” ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው ላይ የተነሱትን ጉዳዮች ሊስማማባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል ተደርጓል የተባለው ይህ ስምምነት ግን ሱማሊላንድን የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ በምትቆጥረው ሶማሊያ በኩል ቁጣን ቀስቅሷል።

የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ ማክሰኞ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ብሏል።

የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሩን አቡድላሂ ዋርፋንም ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመግባቢያ ሠነዱ መሠረት ኢትዮጵያ ለ50 ዓመት የሚቆይ የባሕር ጠረፍ ሊዝ ስምምነት እንደምታገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአንጻሩ የኢትዮ ቴሌኮምን ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ድርሻ ለሶማሊላንድ እንደምትሰጥ ሬድዋን አስታውቀዋል።

በስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ግን ሀገራቸው በሊዝ ለምትሰጠው 20 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የባሕር ጠረፍ ተጨማሪ ጥቅም ከኢትዮጵያ እንደምታገኝ አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ “ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ በይፋ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ትሆናለች” ብለዋል።

ከ32 ዓመታት ገደማ በፊት ራሷን ከሶማሊያ ገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ እስካሁን ደረስ ከየትኛው ሀገር እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋም እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን እውቅና አላገኘችም።

ከትላንቱ ስምምነት በኋላ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳዮች እና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይም የእውቅና ጉዳይ በተመሳሳይ ተስተጋብቷል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመችው በምላሹ “ዓለም አቀፋዊ እውቅና” ለማግኘት መሆኑን አስታውቋል።

“ይሄ ታሪካዊ ስምምነት ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ መደበኛ እውቅና በመስጠት ለባሕር ኃይሏ የባሕር በር እንደምታገኝ ያረጋግጣል” ሲል በመግለጫው የስምምነቱን ጭብጥ ያስረዳል።

የሱማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴም በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ “በመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እውቅና ስትሰጥ፤ ሱማሊላንድ ደግሞ ለ50 ዓመት በሚቆይ ሊዝ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እና ለንግድ አገልግሎት የሚውል ባህር ትሰጣለች” ሲሉ ይህንን ሀሳብ አጠናክረዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት መስማማቷ ከሀርጌሳ በኩል በተደጋጋሚ ቢነሳም ከአዲስ አበባ በኩል በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ ማረጋገጫ አልነበረም።