የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ አዲስ አበባ ገቡ

የፎቶው ባለመብት, MFAEthiopia
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ በ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ አርብ የካቲት 8/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገቡ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አዲስ አበባ የመጡት ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ ከተፈጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታዋ ብርቱካን አያኖ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጽህፈት ቤታቸው ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንት ሐሰን በጉባኤው ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ጥቆማ ሰጥቷል። በንግግራቸውም “በሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ዋና መርህ ላይ የሶማሊያን የማይናወጥ አቋም በማሳየት ለአህጉራዊ አንድነት፣ ለሰላም እና ለልማት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያሉ” ብሏል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እና በምላሹም ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና ለመስጠት ስምምነት መፈረሟ ሉዓላዊነቱን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ሶማሊያ ተቃውሞዋን ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተባበሩት መንግሥታት መቅረቧ ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪም “ፕሬዚዳንቱ የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚነኩ ስምምነቶች ዓለም አቀፍ ሕግን እና የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚያከብሩ መሆን አለባቸው የሚለውን [ሶማሊያን] አቋም ደግመው ይናገራሉ” ሲል ጽህፈት ቤታቸው አክሏል።
የፀጥታ ስጋቶችን በመዋጋት ረገድ ያሉ ትብብሮች፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የአየር ንብረት ቀውስ እና የአህጉሪቱ ዘላቂ ልማትም በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ንግግር የሚያደርጉባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ከ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ መንግሥታት መሪዎች እና ከሌሎች የልዑካን ቡድን መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ በጽህፈት ቤታቸው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ወር 15 ቀን ገደማ በፊት ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ውጥረት ነግሷል። ሶማሊያ ስምምነቱ የግዛት እንድነቷን የሚጥስ መሆኑን በማንሳት ውድቅ እንዲሆን ስትጠይቅ ቆይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአስር ቀናት በፊት በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ባደረጉት ንግግር መንግሥታው ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸው ነበር።
ዐቢይ አክለውም በስም ያልጠቀሷቸው “ኃይሎች” ኢትዮጵያን ከሶማሊያ ጋር ለማጋጨት እየሰሩ ነው ሲሉም መክሰሳቸው ይታወሳል።












