የቻይና አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ስለወታደራዊ ጥንካሬዋ ለዓለም ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ቻይና በወታደራዊ ትርዒቷ ላይ የተለያዩ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎችን ይፋ አድርጋለች። አንዳንዶች ይህ ለአሜሪካ እና ለአጋሮቿ ግልፅ መልዕክት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በዝግጅቱ ላይ ከ20 በላይ የውጭ አገራት መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቻይና ላይ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ድጋፎች ጥገኛ የሆኑት የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ይገኙበታል።

ትርዒቱ በዓለም መድረክ ላይ የዢ ጂንፒንግን ኃያልነት እና የቻይናን ወታደራዊ ብቃት ማሳያ ነበር።

በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ ከታዩት የጦር መሳርያዎች መካከል "ጉዋም ኪለር" የተሰኘ ሚሳዔል፣ "ሎያል ዊንግማን" የተሰኘ ሰው አልባ አውሮፕላን እና 'ሮቦት ዎልቭስ' የተባለው ሮቦት ለዕይታ ቀርበዋል።

ግዙፍ እና ደማቅ ከሆነው አስደናቂ ወታደራዊ ትርዒት እና አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ባሻገር ዓለም ስለ ቻይና ምን ተረዳ?

ቻይና የጦር መሳሪያቿን እንዴት ትጠቀማለች?

ረቡዕ ዕለት በነበረው ወታደራዊ ትርዒት ላይ ግልጽ የሆነው ነገር ቻይና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በፍጥነት ማምረት እንደምትችል ነው።

ከአሥር ዓመታት በፊት ቻይና ለዕይታ ያቀረበቻቸው ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የአሜሪካ የላቁ መሳሪያዎች ቅጂ እንደነበሩ በሲንጋፖር ናንያንግ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመከላከያ ፕሮግራሞች ልማት ረዳት ፕሮፌሰር ሚካኤል ራስካ ተናግረዋል።

ነገር ግን ይህ ትርዒት የበለጠ ፈጠራ እና ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች የታዩበት፣ በተለይም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳዔሎችን በማምረት ረገድ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋ ምን ያህል የላቀ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

የፓስፊክ ፎረም ተባባሪ አጥኚ አሌክሳንደር ኒል ደግሞ ቻይና ከከፍተኛ አመራር እስከ ታችኛው ካድሬ ድረስ ያላት መዋቅር እና ጉልህ ሃብት ከሌሎች አገራት በበለጠ ፍጥነት አዳዲስ መሳሪያዎችን ለማምረት ያስችላታል ሲሉ ያስረዳሉ።

እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን በከፍተኛ መጠን በማምረት ጠላትን የምታሸንፍበት የጦር ሜዳ የበላይነትን ሊሰጣት ይችላል።

ኒል "ቻይና ጥይቶችን፣ መርከቦችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በፍጥነት ማምረት ትችላለች።…ምክንያቱም ያላት መዋቅር መሳሪያዎቹ እንዲመረቱ በቀጥታ መመሪያዎች እና ትዕዛዞችን መስጠት ይችላል" ብለዋል።

ነገር ግን ቻይና እነዚህን የጦር መሳሪያ ሥርዓቶች ከጦሯ ጋር እንዴት አድርጋ ታቀናጃቸዋለች?

"እነዚህን የላቁ መሳሪያዎች ለዕይታ ማቅረብ ትችላለች፣ ነገር ግን በፈለጉት መንገድ ለመጠቀም ድርጅታዊ ቅልጥፍና አላቸው ወይ?" ሲሉ ዶ/ር ራስካ ይጠይቃሉ።

የቻይና መከላከያ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጉልህ የሆነ ጦርነት ውስጥ ባለመግባቱ፣ ጦሩ ግዙፍ እና ያልተፈተነ በመሆኑ ቀላል እንደማይሆን ጨምረው ያስረዳሉ።

ቻይና ለምን ሚሳዔሎች ላይ አተኮረች?

ቻይና አንዳንድ አዳዲስ ምርቶችን ጨምሮ ብዙ ሚሳዔሎችን ለዕይታ አቅርባለች።

እነዚህም በሚሳዔሉ ጫፍ ላይ ብዙ አረሮችን መያዝ የሚችለው ዶንግፌንግ-61፣ ከሰሜናዊ ቻይና ተነስቶ አሜሪካን ሊመታ የሚችለው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ዶንግፌንግ-5ሲን ይጨምራል።

እንዲሁም በጉዋም የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮችን ሊመታ የሚችል ዶንግፌንግ-26ዲ እና መካከለኛ ርቀት የሚተኮስ ሚሳዔል የሆነው "ጉአም ኪለር" ናቸው።

እንዲሁም በፍጥነት የሚምዘገዘጉ እና ፀረ ሚሳዔሎችን ማምለጥ የሚችሉት እንደ ዋይጄ-17 እና ዋይጄ-19 ያሉ በርካታ ሃይፐርሶኒክ ፀረ መርከብ ሚሳዔሎች ለዕይታ በቅተዋል።

ቻይና በሚሳዔሎች ምርት ላይ እንድታተኩር የሚያደርጋት ምክንያት ምንድን ነው?

ኒል ቻይና የመከላከያ ስልቷ ቁልፍ አካል እንዲሁም የአሜሪካን የባሕር ኃይል የበላይነት ለመመከት ሚሳዔሎችን እና ሮኬቶችን በማምረት ላይ ትገኛለች ይላሉ።

ቻይናን የአሜሪካ የባሕር ኃይል በዓለም ላይ ካሉት የአውሮፕላን ተሸካሚዎች እና ማስወንጨፍያዎች ጋር ማወዳደር የማይታሰብ ነው።

ቻይና አሁንም በዚህ ረገድ በእጅጉ ወደ ኋላ ቀርታለች።

ነገር ግን ኒል እንዳስረዱት፣ በምዕራቡ ዓለም የመከላከያ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች እነዚህ ማስወንጨፊያዎች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው ብለው ይከራከራሉ።

ምክንያቱም ለማንኛውም የሚሳዔል ጥቃት "ተጋላጭ ሆነው ተቀምጠዋል።"

ቤይጂንግ የመከላከል አቅሟን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን "የመልሶ ማጥቃት አቅሟን" እየፈጠረች ነው ብለዋል።

አክለውም አንድ አገር ጥቃት ካደረሰባት የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ የሚያስችላትን አቅም እየገነባች ነው ብለዋል።

ሌሎች ለዕይታ ከቀረቡት መካከል ብዙ ከተነገረላቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል ኤልዋይ-1 የተሰኘው የጨረር ጦር መሳሪያ ይገኝበታል።

ይህ የጦር መሳሪያ ኤሌክትሮኒክሶችን ወይንም ከዕይታ የተሰወሩ የጦር ጄቶችን ሊያቃጥል ወይም ሊያስተጓጉል የሚችል ግዙፍ የጨረር መሳሪያ ነው።

እነዚህ የጨረር ጦር መሳሪያዎች ጄ-20 እና ጄ-35 አውሮፕላኖችን ጨምሮ የአምስተኛው ትውልድ ስውር ተዋጊ ጄቶችን ያካተቱ ናቸው።

ቻይና ጦር መሳሪያዎች እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት

በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ነበሩ።

ግን የበርካቶችን ቀልብ የሳበው ኤጄኤክስ-002 (AJX-002) ግዙፉ የባሕር ሰርጓጅ ሰው አልባ አውሮፕላን ነው።

እስከ 20 ሜትር ርዝመት ያለው እጅግ ግዙፍ ሰው አልባ የውሃ ውስጥ ተሽከርካሪ (XLUUV) በመባልም ይታወቃል።

ምናልባት የቅኝት እና የስለላ ተልዕኮዎችን ሊያከናውን ይችላል።

ቻይና "ሎያል ዊንግማን" የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጂጄ-11 በስውር ጥቃት የሚፈጽም ሰው አልባ አውሮፕላኗንም ለዕይታ አቅርባለች።

ይህም ድሮን ሰው ከሚያበረው የጦር አውሮፕላን ጎን ለጎን በመብረር ለጥቃቱ እገዛ ያደርጋል።

ከተለመዱት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጨማሪ "ሮቦቲክ ዎልቭስ" በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ ለዕይታ ቀርበው ነበር።

እነዚህም ሮቦቶች ከስለላ እና ፈንጂዎችን ከመጥረግ ጀምሮ የጠላት ወታደሮችን እስከ ማደን ድረስ ለተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ሊውሉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ቻይና ለዕይታ ያቀረበቻቸው ድሮኖች በወታደራዊ ስልቷ ልትከተል የምትፈልገውን ግልፅ አቅጣጫ ያሳያል።

ይህም የመከላከያ መሳሪያዎቿን ቁጥር "ለመጨመር ብቻ ሳይሆን የተለመደውን የጦር ሠራዊቷን መዋቅር በአዲስ ለመተካት" ትፈልጋለች።

ዶ/ር ራስካ ቻይና ከዩክሬን ጦርነት ትምህርት ወስዳለች ይላሉ። ይህም አንድ አገር "በጠላት ላይ ድሮኖችን ብቻ በመልቀቅ" የመከላከያ አቅሟን ለማዳከም እንደሚችል ተገንዝባለች ሲሉ ያብራራሉ።

ኒል በበኩላቸው "በጦርነት ውስጥ ፈጣን ውሳኔ ሰጪነት ወሳኝ ተግባር ነው" ካሉ በኋላ፣ በፍጥነት በሚካሄድ ጦርነት መካከል ጠላትን ለማሸነፍ እና የበላይነቱን ለመያዝ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ማድረግ እንደሚችለው በ"ቅጽበት" ውሳኔዎች መሰጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ብዙ አገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በወታደራዊ ሥርዓታቸው ውስጥ ስለማሰማራት እና "ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በውጊያ ውስጥ ለማስገባት ምን ያህል ዝግጁ ነን" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ቻይና ግን በዚህ ረገድ "በጣም ተዘጋጅታለች" ይላሉ ዶ/ር ራስካ። "ኤአይን መቆጣጠር እንደሚችሉ ያምናሉ። በሥርዓታቸው ውስጥ ለማካተትም እስከ መጨረሻው ርቀት ድረስ እየሄዱ ነው።"

ቻይና በቴክኖሎጂ፣ አሜሪካ በብቃቱ

ወታደራዊ ትርዒቱ ቻይና በቴክኖሎጂ አሜሪካ ላይ ለመድረስ በፍጥነት እየተጓዘች መሆኗን እና ግዙፍ የጦር መሳሪያ የመገንባት አቅም እንዳላት ያሳየ ነው።

ነገር ግን አሜሪካ አሁንም በወታደራዊ ግዳጆች በኩል የበላይነት እንዳላት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ዶ/ር ራስካ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል "የላቀ" የሆነበት ምክንያት በግዳጅ ላይ ያሉ ሠራዊቶች ውሳኔ በመስጠት እና በመዋጋት ረገድ "ከታች ወደ ላይ" የሆነን የዕዝ ሰንሰለት የመከተል ባሕልን ስላዳበሩ ነው ብለዋል።

ይህ በጦርነት ውስጥ የበለጠ ፈጣን እና ቀልጣፋ ያደርጋቸዋል።

በሌላ በኩል ቻይና "ከላይ ወደ ታች" የሚወርድ አመራርን የምትከተል ሲሆን "ውድ እና ዘመናዊ የሆኑ መሳሪያዎች እና ሥርዓቶች ሊኖራቸው ቢችልም ከላይ ትዕዛዝ እስኪቀበሉ ድረስ ምንም ነገር ማንቀሳቀስ አይችሉም" ብለዋል።

ዶ/ር ራስካ ባለፈው ወር የቻይና የጦር መርከብ የፊሊፒንስ የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎችን ሲገጥም የተፈጠረውን በማስታወስ የሚገጥሟቸውን ታግዳሮቶች ይጠቅሳሉ።

"ቻይናውያን ቴክኖሎጂያችን የሚከላከል ነው ብለው ያስባሉ። ይህ አሜሪካን እንደሚገዳደር ያምናሉ...ነገር ግን በውጊያ ወቅት፣ እነሱ እንደሚሉት ብቁ ቁመና ላይ ላይሆኑ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ" ብለዋል።

ለአሜሪካ መልዕክት ለማስተላለፍ እና ገበያ ፍለጋ

ኒል በቻይና ግዙፍ ወታደራዊ ትርዒት ላይ የበርካታ አገራት መሪዎች መታደማቸውን ላስተዋለ፣ የጦር መሳሪያዎቹ እና ታንኮቹ ለዕይታ መቅረብ የቻይና የጦር መሳሪያ ገዥዎችን ለማማለል መሆኑን አያጣውም ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ምያንማር ያሉ አንዳንድ አገራት የቻይና ጦር መሳሪያን በብዛት እንደሚገዙ ይታወቃል።

ዶ/ር ራስካ ለቻይና አዳዲስ ደንበኞች ማፍራት ወይንም ትዕዛዞችን መጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተፅዕኖ እንዴት ማስፋት እንደምትችል ያሳያል ብለዋል።

ከዋና ደንበኞቻቸው መካከል ከዢ ጂንፒንግ ፊት እና መካከል የቆሙት ቭላድሚር ፑቲን እንዲሁም ኪም ጆንግ ኡን ይገኙበታል።

ሦስቱም በአንድነት ወደ ወታደራዊ ትርዒቱ ሲሄዱ እና መድረክ ላይ ሲቆሙ የጋራ ግንባር መፍጠራቸውን ያሳያል።

ኒል እንደሚሉት ከሆነ ይህ ለአሜሪካ የተላለፈ መልዕክት ነበር።

አሜሪካ በእውነት ቻይናን ለመገዳደር ከፈለገች "በተመሳሳይ ጊዜ በበርካታ ስፍራዎች በኮሪያ፣ በታይዋን ሰርጥ እና በዩክሬን እነርሱን መዋጋት ማለት ነው።"

"እና ይህንን ግምት ውስጥ ካስገባን በሦስቱም ጎራዎች አሜሪካ ውጊያ ውስጥ ከገባች፣ ከእነዚህ በአንዱ ዐውደ ውጊያ ላይሳካላት ይችላል።"