ለብሔራዊ ባንክ ገዢነት እና ለኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትርነት የተሾሙት ዶ/ር ኢዮብ እና እናታለም ማናቸው?

የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር እናታለም መለሰ እና የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ, የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር እናታለም መለሰ እና የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአገሪቱ ብሔራዊ ባንክን እና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን የሚመሩ ሁለት ባለሥልጣናትን መሾማቸውን አስታወቁ።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢነት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ባሳወቁት አቶ ማሞ ምህረቱ ቦታ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩትን ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከመስከረም 9/2018 ዓ.ም. ጀምሮ መሾማቸውን ይፋ አድርገዋል።

እንዲሁም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ሳሉ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው መሾማቸው በተገለጸው በለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ እናታለም መለሰ ተሹመዋል።

በአገሪቱ የረዥም ዘመን የመዋዕለ ነዋይ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ለውጦች እንደተወሰደ የሚነገርበትን ያለፉትን ሁለት ዓመታት በብሔራዊ ባንክ ገዢነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ማሞ ምህረቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ መሾማቸው ተነግሯል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን ለአምስት ዓመታት ያህል የመሩት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት በፕሬዝዳንቱ ከመሾማቸው ውጪ አስካሁን ምድባቸው የት እንደሆነ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

ኢዮብ ተካልኝ

በ1992 ዓ.ም. ከመቀለ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ተደርገው የተሾሙት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት ጋር የቀረበ ትስስር አላቸው።

አሁን በባንኩ የገዢነት ቦታ ላይ ከመሾማቸው በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባል የነበሩ ሲሆን፣ በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታነት በመሥራት ላይ ሳሉ ነው ወደ አዲሱ ሹመት የተሸጋገሩት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ኢዮብ (ዶ/ር) ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ከመዘዋወራቸው ቀደም ብሎ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል።

በፖለቲካል ኢኮኖሚ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን እንዲሁን ማስተርስ ዲግሪያቸውን በኢተርናሽናል ፖሊሲ ከአሜሪካ የሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ እና ጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካሪ በመሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በአይኤምኤፍ እና በዓለም ባንክ ጉዳዮች በማማከር፣ እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ውስጥ በአማካሪነት ሠርተዋል።

በተጨማሪም በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ውስጥ ኃላፊነት የሠሩ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል።

ለተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ ማኅበር፣ በተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ እንዲሁም በሌሎች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ሠርተዋል።

እናታለም መለሰ

ወይዘሮ እናታለም መለሰ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ እዚህም ከሪፖርተርነት አንስቶ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች በማለፍ በምክትል ዋና ዳይሬክተር የትምህርታዊ ፕሮግራሞች ኃላፊ እና የዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ወ/ሮ እናታለም በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ የኃላፊ ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ እናታለም በከተማው አስተዳደር የማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ።

ከዚያ በኋላም የከተማው ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ጋዜጣን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ሲባል የነበረው እና አሁን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሚባለው ተቋም ምክትል እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለተወሰነ ጊዜ ሠርተዋል።

አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ሆነው እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የአዲስ አበባ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል።