ስፔን በጎርፍ መጥለቅለቅ ክፉኛ ወደተጎዳችው ቫሌንስያ 500 ተጨማሪ ወታደሮችን ላከች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስፔን በቫሌንስያ ግዛት ለደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰጠችው ምላሽ አነስተኛ ነው እየተባለ ትችት መቅረቡን ተከትሎ ተጨማሪ 500 ወታደሮች ወደ ግዛቲቷ አሰማራች።
በቫሌንስያ እና አካባቢው በደረሰው ጎርፍ መጥለቅለቅ እስካሁን ድረስ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
በሕይወት የተረፉ ካሉ በሚል ፍለጋው በቀጠለበት በዚህ ሰዓት የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ሰኞ ዕለት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ድልድዮች የወደሙ ሲሆን፣ ከተሞች በጭቃ በመሸፈናቸው ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መብራት እና የሚመገቡት መቸገራቸው ተገልጿል።
በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች መንግሥት እያካሄደ ያለውን የነፍስ አድን እና የጽዳት ሥራ ለመርዳት ወደ ገጠር አካባቢዎች ተጉዘዋል።
አርብ ዕለት ግን የአካባቢው ባለስልጣናት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በክልሉ ያለው የትራፊክ ፍሰት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እንደሚገደብ አስታውቀዋል።
በሰሜን ምሥራቅ እና በደቡባዊ ስፔን እስከ እሁድ ድረስ የሚቆይ እንዲሁም በባሊያሪክ ደሴቶች ደግሞ ለቅዳሜ ብቻ የአየር ጠባይ ሁኔታ ማስጠንቀቅያዎች ተሰጥተዋል።
ምንም እንኳ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ይገኛሉ የሚለው ተስፋ የመነመነ ቢሆንም፣ በቫሌንሲያ ወደ 1,700 የሚጠጉ ወታደሮች የነፍስ አድን ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በስፔን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለዓመታት ታይቶ የማይታወቅ እጅግ አስከፊ በተባለው የጎርፍ አደጋ የጠፉ በርካታ ሰዎችን ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
እስካሁን በጎርፍ አደጋው ከ200 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሞቱት በቫሌንሲያ ግዛት ነው ተብሏል።
ከአካባቢው አንደሚወጡት መረጃዎች ከሆነ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
አንዳንድ ነዋሪዎች የአካባቢው ባለስልጣናት ስለ ጎርፉ ስጋት ቀድመው ማስጠንቀቅያ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ በርካታ ሕይወት ማትረፍ ይቻል ነበር ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በቫሌንሺያ በአልዳያ ከተማ የሚኖረው ጁዋን ጎንዛሌዝ ለቢቢሲ እንደተናገረው በከተማዋ የደረሰው ኪሳራ ከባድ ነው።
“ይህ አካባቢ ለድንገተኛ ጎርፍ የተጋለጠ ነው። የአካባቢው አስተዳደር ይህ እንደሚመጣ እያወቀ ምንም ነገር አለማድረጉ አስነዋሪ ነው” ብሏል።
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አውጉስቲን ከባለቤቱ እና ልጆቹ ጋር ይኖሩበት የነበረው አፓርታማ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ በመጥለቅለቁ ወደ ወላጆቹ ቤት ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጿል።
አስከፊው የአየር ሁኔታ ከቫሌንሲያ እና ከሜዲትራኒያን የባህር ዳርቻዎች ቢያልፍም፣ በደቡባዊ ስፔን ግን አሁንም እስከ ቅዳሜ ድረስ ተጨማሪ ከባድ ዝናብ ሊኖር ይችላል በሚል የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።
ይህ ቀደም ሲል በሀይለኛ ዝናብ ክፉኛ የተጠቃው የሁዌልቫን ይጨምራል ተብሏል።
የካርታያ ከተማ በበኩሏ በ10 ሰዓታት ውስጥ የሁለት ወር ያህል ዝናብ አግኝታለች ሲሉ ተናግረዋል።
በስተደቡብ፣ በጄሬዝ ከተማ፣ በከባድ ዝናብ የተነሳ የወንዞችን ከፍታ በመጨመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ቤታቸውን ለቅቀው መውጣት ነበረባቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ስፔን ለተፈጥሮ አደጋዎች በቂ የማስጠንቀቂያ ሥርዓት እያላት ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ጥያቄ እየቀረበ ሲሆን፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም ምላሽ በጣም ዘገምተኛ ነው የሚል ትችት ቀርቦበታል።
የአካባቢው አስተዳደር ማክሰኞ ምሽት ከአንድ ሰዓት በኋላ በቫሌንሲያ ከተማ እና አካባቢው ላሉ ሰዎች በስልክ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ያደረሰ ቢሆንም በዚህ ጊዜ ጎርፉ በፍጥነት መጠኑ እየጨመረ በአንዳንድ አካባቢዎችም ውድመት ማድረስ ጀምሮ ነበር ተብሏል።
በቫሌንሲያ ስለደረሰው ውድመት በአካባቢው የምትኖረው ሚሬያ ስትናገር፣ ሰዎች “በፍፁም ዝግጁ አልነበሩም” ትላለች።
"ብዙ ሰዎች በመኪናቸው ውስጥ ቢገቡም፣ ሊወጡ ግን አልቻሉም" ያለችው ሚሬያ "በጎርፉ ውስጥ ሰጥመው ነው የሞቱት።”
በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች የስፔን መከላከያ እና የድንገተኛ አደጋ አገልግሎቶችን በሕይወት የተረፉትን በማፈላለግ እንዲሁም አደጋው ያደረሰውን ውድመት በማጽዳት ዘመቻ እየረዱ ሲሆን የቫሌንሲያ ክልል ፕሬዝዳንት ካርሎስ ማዞን ተጨማሪ ወታደሮች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ለበጎ ፈቃደኞች ያላቸውን ምስጋና በማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ገልጸው፤ ሲገልጹ “የአንድነት እና የስፔን ማኅበረሰብ ገደብ የለሽ ቁርጠኝነት ምሳሌዎች” ሲሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል።
አክለውም መንግሥታቸው በአደጋው የተጎዱትን ለመርዳት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስካሁን ከ60 በላይ ሰዎች መሞታቸው በተዘገበባት የፔይፖርታ ከተማ እርዳታ እየደረሰ ያለው በዝግታ ነው በሚል ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል።
የ33 ዓመቱ ፋርማሲስት ፓኮ ክሌሜንቴ በጎርፍ ውድመት የደረሰበትን የጓደኞቹን ቤት እያጸዳ "በቂ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች በስፍራው የሉም፤ ውድመቱ ያደረሰውን ለማጽዳት የሚረዱ መሳርያዎችም እስካሁን አልደረሱም" ሲል ለኤኤፍፒ በምሬት ተናግሯል።
በርካታ ሰዎች በዝርፊያ ላይ በመሰማራታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል። አንድ የአልዳይያ ነዋሪ ለኤኤፍፒ እንደገለጸው ከገበያ ማዕከል ሌቦች እቃዎችን ሲወስዱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጾ "ሰዎች ትንሽ ተስፋ ቆርጠዋል" በማለት አስረድቷል።












