ሕንድ እና ፓኪስታን አንዳቸው ሌላኛቸውን የደረሱበትን "የተኩስ አቁም በመጣስ" ወነጀሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሕንድ እና ፓኪስታን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን ከገለፁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን "በመጣስ" ወነጀሉ።
በሕንድ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ካሽሚር ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ የሕንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚስሪ " ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተደጋጋሚ ጥሰት ተፈጽሟል" ብለዋል።
የፓኪስታን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "በተወሰኑ ስፍራዎች በሕንድ የተፈጸሙ ጥሰቶች እያሉም ቢሆን. . . ለተኩስ አቁሙ ትግበራ ቁርጠኞች ነን" ብለዋል።
ባለፉት አራት ቀናት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ግጭት ባለፉት አስርት ዓመታት በመካከላቸው ከታየው ወታደራዊ ፍጥጫ ሁሉ የከፋ ነበር ተብሏል።
ሕንድ ባለፈው ወር በፓልጋም ለደረሰው ጥቃት ምላሽ በሚል በፓኪስታን እና ፓኪስታን በምታስተዳደርው ካሽሚር ግዛት ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን፣ ሚሳዔሎች እና ሌሎች ተተኳሾች የታገዘ ድብደባ አድርጋለች።
ፓኪስታን የ26 ሂንዱዎችን ሕይወት በቀጠፈው ጥቃት ላይ እጄ የለበትም ብላ ብታስተባብልም ሕንድ ግን በመንግሥት በሚደገፉ አማፂያን የተፈጸመ ነው ስትል ትሞግታለች።
ለአራት ቀን ከቆየው ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት በኋላ ፓኪስታን እና ሕንድ ሙሉ እና ወድያውኑ ተፈጻሚ የሚሆን የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል።
ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል።
አክለውም በአሜሪካ ሸምጋይነት በሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ አገራት መካከል ተኩስ ለማቆም ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።
የፓኪስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር አገራቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን አረጋግጠዋል።
ሚኒስተሩ ለአገራቸው የመገናኛ ብዙኃን በዲፕሎማቲክ ጥረቱ ውስጥ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊን ጨምሮ "በርካታ አገራት" መሳተፋቸው ተናግረዋል።
የሕንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚስሪም በበኩላቸው "በምድር፣ በአየር እና በባሕር" አገራቸው የምትወስደው እርምጃን ለማቆም መስማማቷን አረጋግጠዋል። ጨምረውም ተኩስ አቁሙ በሰዓታት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ብለው ነበር።
ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ ከጥቂት ሰዓት በኋላ በሕንድ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት የሚገኙ ነዋሪዎች እና የቢቢሲ ሪፖርተር ፍንዳታዎችን መስማታቸውን እና በሰማይ ላይ ፍንጥቅጣቂዎችን ማየታቸውን ተናግረዋል።
የሕንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚስሪ "ላለፉት ጥቂት ሰዓታት ከደረስነው ስምምነት በተቃራኒ ተደጋጋሚ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ይህ አስቀድሞ የተስማማንበትን የጣሰ ነው" ብለዋል።
ሚስሪ የሕንድ መከላከያ ኃይል "ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ" ትዕዛዝ መተላለፉን ተናግረዋል። አክለውም "ፓኪስታን ስለተፈጸመው ጥሰት ማብራርያ እንድትሰጥ እጠይቃለሁ" ብለዋል።
የፓኪስታን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ፓኪስታን ቀደም ብሎ በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ለተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጽ እፈልጋለሁ። ምንም እንኳ በተወሰኑ አካባቢዎች በሕንድ የተኩስ አቁሙ ቢጣስም የጦር ኃይላችን ጉዳዩን በኃላፊነት እና በመታቀብ ተቆጣጥሮታል።
"የተኩስ አቁምን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስፈጸም ማንኛቸውም የሚኖሩ ጉዳዮች በተገቢው ደረጃ በመግባባት ሊፈቱ ይገባል ብለን እናምናለን። የተሰማሩ ጦር ኃይሎችም ቢሆኑ ከማንኛውም ነገር መታቀብ አለባቸው" ብለዋል።
ካሽሚር በሕንድ እና በፓኪስታን የይገባኛል ጥያቄ የሚቀርብባት ግዛት ስትሆን ነገር ግን ሁለቱም አገራት ከብሪታንያ ነጻነታቸውን ካገኙበት እአአ 1947 ጀምሮ በከፊል ብቻ እያስተዳደሯት ይገኛል።
የይገባኛል ጥያቄው ለሁለቱ ኒውክሌር ለታጠቁ አገራት ምንጊዜም የፍጥጫ ምክንያት ሲሆን ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ያህል ወደ ጦርነት ገብተዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ያረጋገጡት የሕንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለቱ አገራት " ተኩስ ለማቆም እና ወታደራዊ ተግባራትን ለመግታት" መስማማታቸውን ተናግረዋል።
"ሕንድ በሁሉም መልኩ እና መገለጫዎች በሽብርተኝነት ላይ ያለማቋረጥ ጠንካራ እና የማያወላዳ አቋሟን ቀጥላለች። ይህንንም አጠናክራ ትቀጥላለች" ብለዋል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም ስምምነት "ለሁሉም ሰው ጥቅም" ሲባል መደረሱን ተናግረዋል።
የተኩስ አቁም ይፋ መደረጉን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሕንድ እና ፓኪስታን በገለልተኛ ቦታ በሰፊው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለመጀመር ተስማምተዋል ብለዋል።
አክለውም እርሳቸው እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከሕንድ እና የፓኪስታን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የአገራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ናሬንድራ ሞዲ እና ሼህባዝ ሻሪፍን ጨምሮ ለ48 ሰዓታት ያህል ንግግር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ግጭቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ" በደስታ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ብሪታንያ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በኩል ከሁለቱም ወገኖች ጋር "ለተወሰኑ ቀናት" በውይይት ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ሰር ኪር "ዛሬ የተኩስ አቁም ስምምተን ተደርሶ በማየቴ ደስተኛ ነኝ" ካሉ በኋላ "አሁን የሚኖረው ተግባር ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ነው" ብለዋል።












