"ፈተናው በጣም ቀሎ ነበር፤ ትንሽ ከተጠና ውጤት ይገኛል" በማትሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ

ተማሪ ካሊድ በሽር

የፎቶው ባለመብት, SM

በኦሮሚያ ክልል የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነው ካሊድ በሽር በ12ኛ ክፍል ፈተና 591 በማምጣት በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል።

ካሊድ ይፋ በሆነው ውጤት መሠረት ሒሳብ 100፣ ፊዚክስ 100፣ ባዮሎጂ 99፣ ኬሚስትሪ 98፣ አፕቲትዩድ 98 እና እንግሊዝኛ 96 ነጥብ በማስመዝገብ ከ600 ነጥብ ዘጠኝ ነጥብ ብቻ በማጣት ከፍተኛውን ውጤት አግኝቷል።

ካሊድ በሽር ለፈተኛው ስላደረገው ዝግጅት፣ ስለፈተናው እና ስላስመዘገበው ውጤት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ቢቢሲ አማርኛ- ለቅጽበት እንኳን ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ትልቁ ውጤት የእኔ ይሆናል ብለህ አስበህ ታውቃለህ?

እንደዚያ እንኳን አስቤ አላውቅም። አሪፍ ነጥብ እንደማመጣ፣ ጥሩ ነጥብ እንደማመጣ ተስፋ ነበረኝ። ብዙ ለፍቻለሁ፤ ብዙ ሠርቻለሁ። ግን እንደዚህ እንደ አገር ከፍተኛ ነጥብ ይመጣል ብዬ ብዙም አስቤ አላውቅም። ግን ያው ከልፋቴ ጋር ፈጣሪም ተደምሮ ይህንን ውጤት ላመጣ ችያለሁ። በጣም ደስ ብሎኛል።

ቢቢሲ አማርኛ- ከኢትዮጵያ አንደኛው ትልቁ ውጤት ያንተ ነው መባል ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?

ይህ ስሜት በጣም ደስ የሚል ነው። ብዙ ሰው ላያገኘው ይችላል። ለምን ልፋትህን ደግሞ ፈጣሪ ሲያሳክልህ ለፍተህ ደግሞ ሲሳካልህ በጣም ደስ ይላል። ለፍተህ ጠንክረህ የሆነ ሰዓት ላይ ሲሳካልህ በጣም ደስ ይላል። እና ይህ ነው ብዬ ልገልጸው የምችለው ደስታ አይደለም። በጣም ደስ የሚል ለመግለጽ የሚከብድ ደስታ ነው የተሰማኝ።

ቢቢሲ አማርኛ- መጀመሪያ ውጤትህን የሰማህበትን አጋጣሚ እስቲ ንገረን።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መጀመርያ ላይ የሰማሁበት አጋጣሚ ስለ 12ኛ ክፍል ውጤት እሁድ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቶ ነበር። እና እዚያ ላይ ከፍተኛው ውጤት 591 ከዶዶላ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው የሚል ዜና ሰማሁ። እና በዚያው ቅጽበት የእኛ ተማሪዎችም፣ መምህራኖቼም፣ ማኅበረሰቡም ከዚያ ትምሀርት ቤት አንተነህ የምታመጣው እያሉ ሁሉም መደወል ጀመሩ። እኔ ግን ጥርጣሬ ውስጥ ነበርኩኝ። እኔ ላልሆን እችላለሁ የሚል ስሜት ነበር። ሌሊቱን እንደዚያ አሳለፍኩ። ሰኞ ቀን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ስሜንም አብሮ ሲገልጸ ራሴን መቆጣጠር ራሱ ከበደኝ። በጣም ደስ ነው የሚለው ስሜቱ። ደስ ይላል።

ቢቢሲ አማርኛ- ካሊድ ሌሊቱን እንቅልፍ ወሰደህ?

ሌሊቱን ምን እተኛለሁ። ቁጭ ብሎ ማደር ማለት ይቻላል። (ሳቅ) አምስት ደቂቃ እየተኙ መነሳት. . . (ሳቅ)

ቢቢሲ አማርኛ- ምን ነበር የሚያሳስብህ? ብዙ ሰው ስለጠበቀህ እኔ ባልሆንስ የሚለው ያሳስብህ ነበር?

እኔ ባልሆንስ ሳይሆን፣ ብዙ ሰው ጠብቆኛል እየነገሩኝም ነበር። ያው ሶሻል ሚዲያም ላይ ካሊድ በሺር ነው እየተባለ እየተወራ ነበር። እና ይህ ነገር የተሳሳተ መረጃ እንዳይሆን በሚል . . . ሰዉ በጣም ተማምኖብኝ ነበር። ገና ስሜን ሳይሰማ እርሱ ነው በሚል ትላልቅ ሚዲያዎች ሁላ እየዘገቡት ነበር። እኔ ደግሞ ይህ ነገር ከትምህርት ሚኒስቴር ሳይሰማ እንዴት ነው በማለት ትንሽ ሰጋሁ። ግን ደግሞ እነርሱም አንደተማመኑብኝ እኔም ማምጣት ችያለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ - ፈተናውን ስትፈተን በጣም ቀላል ፈተና ነበር እንዴ?

በአንጻራዊነት የዛሬ አምሰት ዓመት የነበረውን ብናይ ፈተናው በጣም ይከብድ ነበር። በየዓመቱ የመግቢያ ፈተናው እየቀለለ እየቀለለ ነው የሚሄደው። እና ተማሪዎች የከዚህ በፊቱን ከሠሩ እንዴት ነው ፈተና ሊወጣ የሚችለው የሚለውን፣ እንዴት ነው ያንን ፈተና መመለስ የምንችለው የሚለውን፣ ሁሉም ፈተና የራሱ ሲስተም አለው። እንዴት ነው ከዚህ በፊት የነበሩት ፈተናዎች የወጡት፣ ዘንድሮስ እንዴት ሊወጣ ይችላል የሚለውን እያየሁ ሳጠና ነበር። እና ፈተናውም ቀሏል። እኔም በደንብ ተዘጋጅቼበታለሁ። ፈጣሪም ረድቶኝ ይህንን ውጤት ማምጣት ችያለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ - ፈተናው ግን ቀሎህ ነበር የምር? በመትፈተንባቸው ቀናት?

አዎ። እኛ አሁን ግቢው ውስጥ የምንፈተናቸውን ፈተናዎች ሒሳብ እና ፊዚክስ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ከበድ ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ነበሩ። ከቴስት ጀምሮ ስንወስድ የነበረው የሚያዘጋጁን [ከበድ ባሉ ጥያቄዎች ናቸው]። በሁለተኛው ሴሚስተር ውስጥ ብቻ ሰባት ሞዴል ፈተናዎች ወስደናል። የ12ኛ ክፍል እና ሌሎች ሞዴሎች ጠንከር ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች እንድንሞክር እያደረጉ መምህራኖቻችን እያበረታቱን ነበር ያዘጋጁን። እና እነዚያን ጠንካራ ጥያቄዎች እየሠራን ስለነበር ዋናው ፈተና ቀላል ሆኖልኝ ነበር።

ቢቢሲ አማርኛ - ከዚያ ወደ ፈተናው ክፍል ስትገባ በጣም ቀለለህ?

አዎ በጣም! በፊት እንዳሰብኩት አይደለም። ይከብዳል ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ሁሉም ሲደርስበት ነው የሚያውቀው። ሁሉም የሚዘጋጀው ይከብዳል በሚል ስሜት ነው። እንደዚህ 5 ፐርሰንት አለፈ ሲባል ምን ሆኖ ነው ተማሪው? እኔም ውጤት አለመጣ ይሆን የሚል ስሜት ሁሉ አለው። እኛ ግን ቀደም ሲል ከፍ አድርገን ነው የምትዘጋጀው። ፈተናው ላይ ስቀመጥ ያየሁት ነገር ከጠበቅሁት ትንሽ ወረድ ያለ ስለነበረ ጥሩ ነገር መሥራት ችያለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ - ከትምህርት ውጪ ምንድን ነው የሚያዝናናህ?

ከትምህርት ውጪ እግር ኳስ እከታተላለሁ።. . .አዎ እንዲሁ አንዳንዴ ፕሪሚየር ሊግ ምናምን አያለሁ። (ሳቅ)

ቢቢሲ አማርኛ - የማን ደጋፊ ነህ?

(ሳቅ) የአርሰናል።

ቢቢሲ አማርኛ - በአንተ ውጤት ማንችስተሮች የሚደሰቱ አይመስለኝም?

(ሳቅ) አዎ ግድ ነው።

ቢቢሲ አማርኛ - ከአርሰናል የምትወደው ተጫዋች ማንን ነው?

ያው ብዙ ሰው ከአርሰናል ተጫዋቾች መካከል የሚደግፈው ሳካን ነው። የሳካ አድናቂ ነኝ።

ቢቢሲ አማርኛ - ሳካ ያንተን ውጤት ቢሰማ በእርግጠኝነት የሆነ ስጦታ ይዞልህ የሚመጣ እመስለኛል።

(ሳቅ) እንግዲህ ከሰማ አዎ።

ቢቢሲ አማርኛ - ከሳይንስ ትምህርቶች በጣም የሚቀልህ ትምህርት የትኛው ነው? የሚያዝናናህ?

በጣም የሚቀሉኝ እና የምወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ማትስ እና ፊዚክስ ናቸው። በተለይ ማትስ በጣም ደስ ይለኛል። አንድን ነገር ካልኩሌት አድርጎ በብዙ መንገድ ሠርቶ አስተማሪ ትንሽ መንገድ ያሳይሃል አንተ ደግሞ ገባ ብለህበት ቁጭ ብለህ ሠርተህ ሌላ መንገድ ስታገኝ ፈጠራ ነው በቃ ማትስ እና ፊዚክስ። በራስህ የምትሠራቸው ነገሮች ናቸው። እና በጣም ደስ ይሉኛል። እነርሱንም መቶ መቶ ማምጣት ችያለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ - በማትሪክ አንድ መቶ ማምጣት በጣም ከባድ ነገር ይመስለኛል ሳስበው. . .

እንደዚያ ነው የሚታሰበው። ኢንትራንስ ፈተና ላይ ግን ከሌሎቹ እንደውም ቀለል የማለት ሁኔታ አለው። እንዲያውም ማትስ ሲባል ሰው ይፈራዋል። በተፈጥሮ ሰው የመፍራት ነገር ይኖረዋል እንጂ አምኖበት ከሠራው ማትስ ቀለል ያለ ፈተና ነው። ከሌሎቹ አንጻር መሥራት የሚቻል ፈተና ነው። . . . ከተዘጋጁበት ሁሉም ቀላል ነው ለማለት እፈልጋለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ- በመቶ ሺህ የሚቆጠር ተማሪ አላለፈም። አንተ ደግሞ አንደኛ ሆነህ አልፈሃል በመቶ ሺህ የሚቆጠር አለማለፉን ስትሰማ ምንድን ነው የሚሰማህ?

የሚሰማኝ ነገር ፈተናውም ከብዶ አይደለም። ተማሪውም አቅቶት አይደለም። ሁሉም መሥራት የሚችል ነው። ግን ያለው አመለካከት ነው። ከማኅበረሰብ ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲባል ያለው አመለካከት በጣም ከባድ ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ማለፍ በጣም ከባድ እንደሆነ አድርጎ ነው ብዙ ሰው የሚያስበው። ግን ችሎታም አጥተው አይደለም። አሁን በጣም ፈተናው ቀሏል፤ ማንም መሥራት ይችላል። ትንሽ ያጠና ራሱ 300 ማምጣት ቀላል ነው። መምከር የምፈልገውም ከባድ ነው ብሎ አለማሰብ ነው። የፈለገ ከባድ ቢሆን እንኳን ጠንክረው ከሠሩ ማሳካት የማይቻል ነገር የለም ለማለት እገፈልጋለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ - ወላጆችህ ምን አሉ?

ያው ወላጆቼ በጣም ነው ደስ ያላቸው። በጣም ደስተኞች ናቸው።

ቢቢሲ አማርኛ - ምንድን ነው የሚሠሩት?

አባቴ ዳኛ ነበሩ። ከአምስት ዓመት በፊት ነው ጡረታ የወጡት። የተማሩ ሰው ናቸው። ስለትምህርት ዋጋ ያውቃሉ። ያበረታቱኝ ነበር ከበፊት ጀምሮ። ይህንን ውጤት ሲሰሙ ደስ ነው ያላቸው። እናቴም እንዲሁ የተማረች ነች። ሁለቱም በጣም ነው ደስ ያላቸው።

ቢቢሲ አማርኛ - እስካሁን ሽልማት አልተሰጠህም?

እስካሁን ምንም የለም።

ቢቢሲ አማርኛ - ምንድን ነው መማር የምትፈልገው? ወደፊትስ ምን መሆን ነው የምትፈልገው?

ወደፊት መማር የምፈልገው ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ነው። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ ፍላጎቱም አለኝ። ዓለም ላይ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ ያሉት በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ነው። በየሰከንዱ ለውጥ የምናየው በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው። እኔም እዚህ ዘርፍ ላይ ተቀላቅዬ ለራሴም፣ ለቤተሰቤም፣ ለማኅበረሰቤም የበኩሌን መሥራት እፈልጋለሁ።