ኢትዮጵያ ነዳጅ የሚጠቀሙ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አገደች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነዳጅ የሚጠቀሙ ከባድ መኪኖችን ከመስከረም 22/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ማስገባት መከልከሉን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት በትናንትናው ዕለት ሲመረቅ፤ 1.3 ቢሊዮን ሊትር በዓመት ያመርታል የተባለውን የፕሮጀክቱን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ ማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም በአነስተኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ በከባድ ተሽከርካሪዎች ላይም መጣሉን ገልፀዋል።

"ትላልቅ መኪና ወይም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ስታስገቡ የነበራችሁ ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ ልክ ትናንሽ መኪኖች ከኤሌትሪክ ውጪ ማስገባት ታግዶ እንደቆየው ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአንጻሩ ጋዝ የሚጠቀሙ ከባድ ተሽከርካሪዎች ለሚያስገቡ ባለሃብቶች ከሆነ ከቀረጥ ነጻን ጨምሮ መንግሥታቸው አስተማማኝ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ዓመት ውስጥ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶቡሶች "ከነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን" ብለዋል።

"ቢበዛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ ባሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን "።

እነዚህ ሁለት ሺህ አውቶብሶች ሲቀየሩ በሚቀጥለው ዓመት የትራንስፖርት ዋጋ ቢያንስ በ50 በመቶ እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለግል ጥቅም የሚውሉ ነዳጅ የሚጠቀሙ አውቶሞቢሎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አግዳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት ባሰሙት ንግግር የፈሳሽ ጋዝ ፕሮጀክቱ ለኃይል ማመንጫ እና ለክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ጭምር የሚያቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሮጀክቱ የጋዝ ማምረቻ ብቻ ሳይሆን ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት ያቀርባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ከዳንጎቴ ድርጅር ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰበትን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የግንባታ መሠረተ ድንጋይ ትናንት መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ/ም በሶማሌ ክልል አስቀምጠዋል።