ሶሪያ ለዓለም ስጋት አይደለችም ሲል የአማጺ ቡድን መሪው ተናገረ

አሕመድ አል-ሻራ
የምስሉ መግለጫ, አሕመድ አል-ሻራ

በሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው አማጺ ቡድን መሪና አሁን ሶሪያ እያስተዳደረ ያለው አሕመድ አል-ሻራ ሶሪያ ለጎረቤቶቿም ሆነ ለምዕራቡ አገራት ስጋት እንደማትሆን ለቢቢሲ ገለጸ።

ሶሪያ በጦርነት የተዳከመች አገር ስለሆነች ስጋት የምትፈጥር እንዳልሆነች ከቢቢሲ ጋር በደማስቆ ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

"ያ ሁሉ ከሆነ በኋላ አሁን ማዕቀቦች መነሳት አለባቸው። ማዕቀቦቹ ዒላማ ያደረጉት የቀድሞውን ሥርዓት ነበር። ጨቋኙና ተጎጂዎቹ እኩል መታየት የለባቸውም" ብሏል።

ሻራ የሚመራው ኤችቲኤስ (ሐያት ታሕሪር አል-ሻም) አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

ከሶሪያ አማጺ ቡድኖች ጠንካራው ኤችቲኤስ ነው።

የአማጺ ቡድኑ መሪ ከዚህ ቀደም መሐመድ አል-ጆውላኒ በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር።

ኤችቲኤስ ከአሸባሪ ቡድኖች ዝርዝር መውጣት እንዳለበት አሳስቧል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የመንግሥታቱ ድርጅትና ሌሎችም አገራት ሽብርተኛ ብለው ቡድኑን ፈርጀዋል።

ቡድኑ ሲመሠረት ከአል-ቃይዳ ጋር ትስስር ቢኖረውም እአአ በ2016 ተለያይተዋል። ሻራም ቡድኑ አሸባሪ እንዳልሆነ ተናግሯል።

ንጹኃንን እንዲሁም ንጹኃን የሚኖሩባቸው አካባቢዎችን ዒላማ እንዳላደረጉ ገልጿል።

እንዲያውም ቡድኑ የአሳድ መንግሥት በፈፀማቸው ወንጀሎች እንደተጎዳ አክሏል።

ሶሪያን እንደ አፍጋኒስታን ያለች አገር የማድረግ ዕቅድ እንደሌለው ተናግሯል። ሁለቱ አገራት የተለያየ ባህል እንዳላቸውም ጠቅሷል።

በአፍጋኒስታን ያለው በቡድን መከፋፈል በሶሪያ እንደሌለ ተናግሯል።

ሴቶች መማር አለባቸው ብሎ እንደሚያስብ ገልጿል።

"ኢድሊብ ውስጥ ከስምንት ዓመታት በላይ ዩኒቨርስቲዎች አሉን" ብሏል።

ይህ የሶሪያ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ከ2011 ጀምሮ በአማጺያኑ የሚተዳደር ነበር።

"ዩኒቨርስቲ የገቡ ሴቶች ቁጥር ከ60% በላይ ነው" ብሏል ሻራ።

አልኮል መጠጣት መፍቀድን በተመለከተ ተጠይቆ "በሕግ ምክንያት አስተያየት መስጠት የማልችልባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ" ሲል መልሷል።

"ሕገ መንግሥት የሚያረቅ የሶሪያ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ይኖራል። እነሱ ይወስናሉ። ማንኛውም መሪ ወይም ፕሬዝዳንት ሕጉን የሚከተል ይሆናል" ሲልም አክሏል።

ሻራ ከቢቢሲ ጋር ቃል ምልልስ ሲያደርግ የሲቪል ልብስ ለብሶና ዘና ብሎ ነበር።

አማጺ ቡድኑ መነሻው ላይ አክራሪ አካሄድ ነበረው በሚል የተፈጠረውን ስጋት በተመለከተም ቡድኑ እንደተለወጠ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ብዙ ሶሪያውያን ግን አያምኑትም።

ሶሪያ ምን ዓይነት አመራር እንደሚኖራትና ምን ዓይነት አገር እንደምትመስል የሚወስኑት አዲሶቹ የሶሪያ አስተዳዳሪዎች በቀጣይ ወራት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ይሆናሉ።