ሕንድ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮቼ ጥቃት ደረሶባቸዋል ብትልም ፓኪስታን እጇ እንደሌለበት ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፓኪስታን ሦስት የጦር ሰፈሮቼ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ጥቃት አድርሳለች ስትል ሕንድ ብትከስም ኢዝላማባድ ግን ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።
የሕንድ ጦር አገሪቱ በምታስተዳደረው የካሽሚር ግዛት በሚገኘው በጃሙ እና በፑንጃብ ግዛት በሚገኘው ፓታንኮት የጦር ሰፈሮቿ ፓኪስታን የሞከረችውን ጥቃት ማክሸፉን ገልጿል።
በሕንድ ቁጥጥር ስር በምትገኘው የካሽሚሯ በጃምሙ ከተማ ሐሙስ አመሻሹ ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን እና መብራት መቋረጡ ተዘግቧል።
የፓኪስታን የመከላከያ ሚኒስትር ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው እንደሌለበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"እስካሁን ጥቃት አልፈጸምንም። ምንም አላደረግንም። ጥቃት አድርሰን ደግሞ አንክድም" ሲሉ ካዋጃ አሲፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቀደም ሲል ሐሙስ ዕለት ሕንድ የፓኪስታንን የአየር መከላከያ መምታቷን እና ኢዝላማባድ ረቡዕ ምሽት ሕንድ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለመምታት ያደረገችውን ሙከራ "ማክሸፏን" አሳውቃለች።
ሕንድ ረቡዕ ዕለት በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ፓኪስታን ድርጊቱን ሌላ "የጥቃት አባባሽ ድርጊት" ስትል ጠርታዋለች።
ሕንድ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለም መሪዎች መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።
በድንበር አካባቢ የሚፈጸመው ጥቃት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤቶቹን ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያመራቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ይህም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሁለቱ አገራት መካከል የከፋው ግጭት ተደርጎ ተወስዷል።
ሕንድ ባለፈው ወር በግዛቷ ስር ባለው ካሽሚር በሚንቀሳቀሱ ቱሪስቶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለመበቀል ረቡዕ ዕለት ዘጠኝ "የአሸባሪዎች መሠረተ ልማት" ጣቢያዎችን መምታቷን ተናግራለች።
ፓኪስታን በፓሃልጋም ከተማ 26 ንጹሃን ዜጎችን የገደሉትን ታጣቂዎች ትደግፋለች የሚለውን የሕንድ ውንጀላ በፅኑ አስተባብላለች።
ጥቃቱ ለዓመታት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጥቃት ሲሆን ይህም ውጥረቱ እንዲባባስ አድርጓል። አብዛኞቹ ሰለባዎች ሕንዳዊያን ጎብኚዎች ናቸው።
በሕንድ በሚተዳደረው ካሽሚር ግዛት በአገሪቱ አገዛዝ ላይ ላለፉት አስርት ዓመታት የዘለቀ አመጽ ከመካሄዱም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ሁለቱ አገራት ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡበት እአአ ከ1947 በኋላ በካሽሚር ላይ የይገባኛል ጥያቄ ከማንሳት ባለፈ ሁለት ጦርነቶች አካሂደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሕንድ ረቡዕ ዕለት "ዘመቻ ሲንዶር" ስትል የጠራችውነ ጥቃት ከጀመረች በኋላ ከዓለም ዙሪያ ነገሮች እንዲረግቡ ጥሪዎች ቀርበዋል።
ሐሙስ ዕለት ግን ሁለቱም ወገኖች ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ወስዷል በሚል አንዳቸው ሌላኛቸውን ከስሰዋል።
የፓኪስታን ወታደራዊ ቃል አቀባይ በሕንድ የተላኩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተናግረዋል።
"ትናንት ምሽት ሕንድ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ብዙ ቦታዎች በመላክ ሌላ የጥቃት ድርጊት አሳይታለች። እነዚህ ቦታዎች ላሆር፣ ጉጅራንዋላ፣ ቻዋል፣ ራዋልፒንዲ፣ አቶክ፣ ባሃዋልፑር፣ ሚያኖ፣ ቾር እና ካራቺ ዙሪያ ናቸው" ሲሉ ሌተናት ጄኔራል አህመድ ሸሪፍ ቻውድሪ ገልጸዋል።
በሲንድ ግዛት አንድ ሲቪል መሞቱን እና በላሆር አራት ወታደሮች ቆስለዋል ብለዋል።
በላሆር የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ሠራተኞቹ በሕንፃው እንዲጠለሉ ነግሯቸዋል።
ሕንድ እርምጃ የወሰደችው ፓኪስታን "በሰሜን እና በምዕራብ ሕንድ በርካታ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለማጥቃት" ለምታደርገው ሙከራ ምላሽ መሆኑን ገልጻለች።
"በላሆር የሚገኝ የአየር መከላከያ ስርዓት ከጥቅም ውጭ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል" ሲል የመከላከያ ሚኒስቴሩ መግለጫ አሳውቋል። ፓኪስታን ግን አስተባብላለች።
የሁለቱ አገራት መረጃ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚሲሪ ደልሂ ውስጥ እንደተናገሩት "ዓላማችን ጉዳዮችን ማባባስ አልነበረም። እኛ ለዋናው ጥቃት ምላሽ መስጠት ብቻ ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጎጂዎች ቁጥር ማሻቀቡን ቀጥሏል። ፓኪስታን ረቡዕ ማለዳ ጀምሮ በሕንድ የአየር ጥቃት በፓኪስታን እና በፓኪስታን በሚተዳደረው ካሽሚር 31 ሰዎች ሲገደሉ 57 ቆስለዋል ብላለች።
የሕንድ ጦር በበኩሉ በፓኪስታን ጥቃት በካሽሚር ክልል የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 16 ሲደርስ ከእነዚህም መካከል 3 ሴቶች እና አምስት ሕጻናት ይገኙበታል ብሏል።
ሕንድ መጀመሪያ ላይ በፓሃልጋም ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ አለ ብላ የምታምነው ቡድን ስም አልጠቀሰችም ነበር።
ከቀናት በፊት ግን በፓኪስታን መቀመጫውን ያደረገውን የላሽካር ኢ-ታይባ ታጣቂ ቡድን ፈጽሟል በማለት ከሳለች።
የሕንድ ፖሊስ ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ሁለቱ የፓኪስታን ዜጎች ናቸው ቢልም ኢዝላማባድ ውድቅ አድርጋዋለች።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ረቡዕ እለት ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር በሕንድ ጥቃት የተገደሉትን ለመበቀል ቃል ገብተዋል።
ፓኪስታን አምስት የሕንድ ተዋጊ ጄቶች መምታቷን ደጋግማ ገልጻለች። ሕንድ በዚህ ዙሪያ አስተያየት አልሰጠችም።












