ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ቀዳማዊት እመቤት ሴት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለፍርድ ቤት ሊያቀርቡ ነው
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ባለቤታቸው ብሪጂት ማክሮን ቀዳማዊት እመቤቷ ሴት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የፎቶግራፍ እና ሳይንሳዊ ማስረጃ ለአሜሪካ ፍርድ ቤት ሊያቀርቡ ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት እና ባለቤታቸው እነዚህን ማስረጃዎች የሚያርቡት ቀኝ ዘመም ተጽእኖ ፈጣሪዋ ካንዳስ ኦዌንስ፤ ብሪጂት ማክሮን ሲወለዱ ወንድ ነበሩ በማለት ያሠራጨችው መረጃ ስም ማጥፋት ነው በሚል ለከፈቱት ክስ ማስረጃ መሆኑን ጠበቃቸው ተናግረዋል።
የቀዳማዊቷ እመቤት ጠበቃ ቶም ክሌር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የገጠማቸው ስም ማጥፋት "በከፍተኛ ሁኔታ የሚያበሳጭ" መሆኑን እና በፕሬዝዳንቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤቷ እርጉዝ ሳሉ እና ልጆችን ሲያሳድጉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ያቀርቡ እንደሆነ የተጠየቁት ጠበቃው፣ ፎቶዎቹ እንዳሉ እና ለፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል ።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏት የወግ አጥባቂው 'ዴይሊ ዋየር' የቀድሞ አባል ተንታኝ የነበረችው ካንዳስ ኦዌንስ በተደጋጋሚ ቀዳማዊት እመቤት ብሪጂት ማክሮን ወንድ ናቸው ስትል ስትናገር ተሰምታለች።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ባለቤት ፆታ ጉዳይ መነጋገሪያ መሆን የጀመረው ከዓመታት በፊት ነበር። በተለይ በ2021 ፈረንሳያውያኑ ዩቲዩበሮች አማንዲን ሮይ እና ናታሻ ሬይ ይህንን ጉዳይ አንስተውት ነበር።
ፕሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው በዩቲዩበሮቹ ላይ የስም ማጥፋት ክስ በ2024 ለፍርድ ቤት አቅርበው አሸንፈዋል። ነገር ግን ይህ ውሳኔ ማስረጃን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ሳይሆን ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ ውሳኔው ቢቀለበስም ጥንዶቹ ይግባኝ ጠይቀዋል።
ባለፈው ሐምሌ ጥንዶቹ "ያቀረበችውን ሐሳብ ውድቅ በሚያደርግ ሁኔታ የቀረቡ ተአማኒ ማስረጃዎችን በመተው፣ የታወቁ ስም አጥፊዎችን እና የሴራ ተንታኞችን ሃሳብ አራምዳለች" በማለት በካንዳስ ኦዌንስ ላይ ተመሳሳይ ክስ አሜሪካ ውስጥ ከፍተዋል።
በአሜሪካ ውስጥ በታዋቂ ሰዎች ላይ የስም ማጥፋት ተፈጽሟል የሚል ክስ ከቀረበ ከሳሽ፣ ተከሳሽ 'ሆን ብሎ በክፋት ሐሰተኛ መረጃን ማሠራጨቱን ወይም ለእውነት ግድየለሽ በሆነ ሁኔታ መፈጸሙን ማረጋገጥ አለበት።
ባለፈው ነሐሴ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑአኤል ማክሮን 'ፓሪስ ማች' ለተባለው መጽሔት በካንዳስ ኦዌንስ ላይ ሕጋዊ መንገድን ለመከተል መምረጣቸውን አስረድተዋል።
"ይህ ጉዳይ ክብሬን ስለመከላከል ነው! ምክንያቱም የቀረበው የማይረባ ነገር ነው። ያሠራጨችው መረጃ ሐሰት መሆኑን እያወቀች ለፖለቲካዊ ዓላማ ጉዳት ለማድረስ የተፈጸመ ድርጊት ነው" በማለት ተናግረዋል።
የካንዲስ ኦዌንስ ጠበቆች ክሱን ውድቅ አድርገው፤ በዴላዌር ግዛት ክስ መመሥረቱ ራሷን መከላከልን አስቸጋሪ ለማድረግ ታስቦ ነው በማለት ተቃውመውታል።
ቢቢሲ ከካንዲስ ኦዌንስ ጠበቆች ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም ተከሳሿ በፕሬዝዳንቱ ሚስት ላይ እየተናገረችው ያለው ነገር እውነት መሆኑን በመግለጽ በአቋሟ ጸንታለች።