ኢትዮጵያዊቷ ጸሐፊ ሃና ጊዮርጊስ ለታዋቂው የኬን ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ታጨች

የፎቶው ባለመብት, Hanna Giorgis
ዘ አትላንቲክ የተሰኘው ታዋቂው የአሜሪካ መጽሔት ጸሐፊ የሆነችው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊቷ ሃና ጊዮርጊስ አኮ ኬይን ለተሰኘው ስመ ጥሩ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ታጨች።
ሃናን ጨምሮ አምስት ደራሲዎች ለዚህ ሽልማት ታጭተዋል።
ጋርዲያንን ጨምሮ ኒውዮርክ ታይምስና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ላይ ጥልቀት ባላቸው የፖለቲካ፣ የባህልና ማኅበራዊ ጽሑፎቿ የምትታወቀው ሃና፣ ለዚህ ሽልማት የታጨው ሥራዋ ‘ኤ ደብል ኤጅድ ኢንኸሪታንስ’ የተሰኘው አጭር ልብ ወለድ ጽሑፏ ነው።
ባለፈው ዓመት ሜሮን ሐደሮ የኬን የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ደራሲመሆኗ ይታወሳል።
ያሸነፈችበት አጭር ጽሑፍ ጌቱ ስለተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ የሚተርክ ነው።
ታዳጊው በአዲስ አበባ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የውጭ ዕርዳታዎች ያላቸውን የኃይል ጫና ለማለፍ የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳይ ታሪክ ነው።
ለዚህ ሽልማት ከታጩት ሌሎች ደራሲዎችመካከል ከናይጄሪያ ጆሹዋ ቺዞማ፣ ከጋና ናና አማ ዳንኳህ፣ ከኬንያ ኢድዛ ሉሃምዮ እና ከጋና ቢሊ ማክተርናን ይገኙበታል።
በዚህ ዓመት ለውድድሩ የመጡት ሥራዎች በርካታዎች ሲሆኑ “በአፍሪካውያን ተወላጅ ጸሐፊዎች መካከል ያለውን የፈጠራ ችሎታ፣ ልዩነት እና ድምቀት የሚያሳይ ነበር” ሲሉ የውድድሩ ዳኞች ሊቀ መንበር ናይጄሪያዊው ደራሲ እና ተሸላሚ ጋዜጠኛ ኦኪ ንዲቤ ይናገራሉ።
አዘጋጆቹ በተጨማሪም ከቀረቡት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል አንድ አሳታሚ በዚህ ዓመት ጎልቶ መውጣቱን ጠቅሰዋል።
አሜሪካ ተቀማጭነቱን ያደረገው አካሺክ አሳታሚ ከታጩት ሥራዎች መካከል ሦስቱን ያተመው መሆኑ ተገልጿል።
በእጩነት ለቀረቡት ጸሐፊዎች ለእያንዳንዳቸው 630 ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን፣ አሸናፊው ሀምሌ መጀመሪያ ላይ በለንደን በሚገኘው ቪ ኤንድ ኤ ሙዚየም በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ ይሆናል።
አሸናፊውም የ10 ሺህ ፓውንድ ሽልማት አሸናፊ ይሆናል።
የኬን ሽልማት በአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ስም የተመዘገበ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን አላማውም ዓመታዊውን የሥነ ጽሑፍ ሽልማትን በመጠቀም የአፍሪካን ጽሑፍ ወደ ሰፊ ተመልካቾች ማድረስ ነው።












