ዜሌንስኪ የሩሲያን የሚሳኤል ጥቃቶች ተከትሎ ምዕራባውያን ረዥም ርቀት መሳሪያዎችን እንዲሰጡ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት ረዥም ርቀት መሳሪያዎችን እና የአየር ክልል ደኅንነት መጠበቂያ ሰርዓት እንዲሰጧቸው ዳግም ጠየቁ።
የሩሲያ ጦር በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ቪላኒያስክ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 7 ሰዎች ተገድለዋል።
ከዛፖሬዢያ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ከተማ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሌሎች 31 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የሩሲያ ጦር ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም. በመላው ዩክሬን በፈጸማቸው የሚሳኤል ጥቃቶች በአጠቃላይ 11 ሰዎች ሲገደሉ 37 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
“በዚህ መሰል የሩሲያ ጥቃት ከተሞቻችን እና የማኅብረሰብ አባላቶቻችን በየቀኑ ለስቃይ እየታደረጉ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ “ይህን ጥቃት ማስቆም የሚቻልበት መንግድ አለ” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸው ላይ ለምዕራባውያኑ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ሰርዓትን በመጠቀም እና በረዥም ርቀት ሚሳኤሎች የሩሲያን ሚሳኤል ማስወንጨፊያ በማውደም” የሞስኮን ጥቃቶች ማስቆም ይቻላል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ጽሑፍ ጋር በደቡብ ምስራቅ ከተማዋ በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን አስክሬን እና ጥቃቱ በንብረት ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምስሎችን አያያዘው አውጥተዋል።
የዩክሬን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አንድሪ ኮስቲን ሁለት ሚሳኤሎች በቪላኒያስክ ከተማ ላይ ሲያርፉ መሠረተ ልማት፣ ሱቆች እና መኖሪያ ሕንጻ ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።
ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ስለተባለው ጥቃት የሩሲያ ጦር እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።
ይሁን እንጂ ጦሩ ከቪላኒያስክ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ እና የዩክሬን ሠራዊት ጦር መሳሪያ ማከማቻ ስፍራን በሚሳኤል መምታቱን ገልጿል።
እንደ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ያሉ አገራት ቀደም ሲል ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን አቅርበዋል። ዋሽንግተን እንዲሁ ፓትሮዮት የተባለ የአየር መቃወሚያ ስርዓት ለኪዬቭ ሰጥታለች።
ይሁን እንጂ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ምዕራባውያኑ አገራት ወሳኝ በሆነ ጊዜ እና በፍጥነት ወታደራዊ ቁሶቹን ማቅረብ ባለመቻላቸው ሩሲያ በጦር ሜዳዎች ላይ የበላይነትን በመያዝ የዩክሬን ግዛቶችን መቆጣጠሯን ይገልጻሉ።
ዜሌንስኪ ትናንት በቴሌግራም ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አጋር አገራትን ለድጋፋቸው አመስግነው ወታደራዊ ድጋፎች “መፍጠን” እንዳለባቸው ገልጸው መዘግየቶች “የሰው ሕይወት እያሳጠን ነው” ብለዋል።












